ዩኬ በአነስተኛ ጀልባ የገቡ ስደተኞችን በሳምንታት ውስጥ ወደ ፈረንሳይ ልትመልስ ነው

ዩናይትድ ኪንግደም ከፈረንሳይ በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን በሳምንታት ጊዜ ውስጥ አዲስ በተወጠነ እቅድ መሰረት መመለስ እንምትጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታመር ተናገሩ።

በእቅዱ መሰረት አገር ውስጥ የሚገቡ አንዳንድ ስደተኞች ወደ ፈረንሳይ ሲመለሱ፤ ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸውን ጥገኛ ጠያቂዎች የደኅንነት ፍተሻ አድርጋ ትቀበላለች።

ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለንደን ከተገኙት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአነስተኛ ጀልባዎች ለመሻገር የሚደረጉ ሙከራዎች "ከንቱ" ይሆናሉ ብለዋል።

እቅዱ በሳምንት እስከ 50 የሚደርሱ ሰዎች እንዲመለሱ እንደሚያደርግ የተዘገበ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን አሃዙን አላረጋገጡም።

"ለውጥ አምጪው" እቅድ የሰዎች ዝውውር ላይ የተመለደውን አካሄድ ለመስበር የሚያግዝ እና ውጤታማ ከሆነ በስፋት የሚሰራበት ነውም ብለዋል።

ሕገ-ወጥ ስደት "ዓለም አቀፍ ቀውስ፣ የአውሮፓ ሕብረት ቀውስ እና የሁለቱ አገሮቻችን ቀውስ" ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ በተሰበሰበ መረጃ በአነስተኛ ጀልባዎች 170 ሺህ ሰዎች ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል።

በዚህ ዓመት ቁጥሮች ከየትኛውም ዓመት በላይ የጨመሩ ሲሆን፤ በ2025 መጀመሪያ ስድስት ወራት 20 ሺህ ስደተኞች ዩኬን ተሻግረው ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እቅዱ ከተመላሾች ቁጥር በዘለለ "መከላከያ ውጤት" ይኖረዋል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት መነጠል (ብሬግዚት) ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ለመከላከል ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል።

የአነስተኛ ጀልባ ስምምነቱ አፈፃፀምን በሚመለከት ዝርዝሩ ግልፅ ያልሆነ ሲሆን፤ ለአብነትም ዩኬ ወደ ፈረንሳይ የምትመልሳቸውን ስደተኞች እንዴት እንደምትወስን እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ይሁን እንጂ እቅዱ በአዋቂ ሰዎች እንደሚጀመር መረዳት ተችሏል።

ፈረንሳይ የሚኖሩ እና ዩኬ መምጣት የሚፈልጉ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በኦንላይን መድረክ ማሳወቅ አለባቸው።

በሰዎች ዝውውር በጣም ከተጋለጡ አገራት የሚመጡ እና ከዩኬ ጋር ትስስር ያላቸው ሰዎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።

የመሪዎቹ መግለጫ ከተጠናቀቀ በኋላ በወጣ መግለጫ ስምምነቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ሕጋዊ ውዝግቦች በመውጣት ከአውሮፓ ሕብረት እና አባል አገራት ጋር ሙሉ ለሙሉ በግልፅነት እና በመረዳዳት ለመስራት ምልክት መሆኑ ተገልጿል።

እቅዱ የአውሮፓ ሕብረት አባል የሆኑት ስፔን እና ጣሊያን ወደ ፈረንሳይ እንዲመለሱ የተደረጉት ስደተኞች ወደ አገሮቻቸው እንዲገቡ ይደረጋል የሚል ስጋት ሊኖራቸው ይችላል።

በአውሮፓ ሕብረት ሕግ መሰረት ወደ ፈረንሳይ የተላኩ ሰዎች መጀመሪያ በገቡበት የአውሮፓ አገር ጥገኝነት መጠየቅ ይችላሉ። ስደተኞቹ ጥገኝነት የሚጠይቁባቸው አገራት በአብዛኛው የሜድትራኒያን ባሕር ድንበር ያደረጉ ናቸው