"ሞት ለእስራኤል ጦር" በሚል መፈክር የዓለም መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ የሆኑት ሙዚቀኞች

በሙዚቃው ዘርፍ አሉ ከሚባሉት አንዱ የሆነው የዩናይትዱ ኪንግደም ግላስተንበሪ ፌስቲቫል የዘንድሮው ዝግጅት አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው።

ቦብ ቪላን በመባል የሚታወቁት ፓንክ እና ራፕን አጣምረው የሚጫወቱት ሙዚቀኞች በመድረክ ላይ "ሞት ለእስራኤል ጦር" በሚል ማውገዛቸው እንዲሁም ይህ መልዕክት በቀጥታ በቢቢሲ መተላለፉ ነው የዓለማችን ታላላቅ መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ዜና ያደረገው።

የባንዱ መሪ ቦቢ ቪላን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት ግላስተንበሪ ፌስቲቫል ላይ "ፍልስጤም ነጻ እንደምትወጣ" እና ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ምዕራቡ ዓለም በፍልስጤማውያን ላይ በሚፈጸመው ግድያ ተባባሪ ናቸው ብሏል።

ከዚያም በመቀጠል "ሞት ለእስራኤል መከላከያ ኃይል" ሲል መድረክ ላይ የተሰማው ቦቢ ቪላን ታዳሚዎችንም በመጋበዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች "ሞት ለእስራኤል መከላከያ ኃይል" በማለት መፈክር አሰምተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የፌስቲቫሉ አዘጋጆች ሙዚቀኛው "ሞት ለእስራኤል ጦር" በሚል መፈክር ታዳሚዎችን መምራቱን "አስደንግጦናል" ብለዋል።

ይህንን ክስተት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር "ሰቅጣጭ የጥላቻ ንግግር" ሲሉ አውግዘውታል።

በተጨማሪም የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ በቦብ ቪላን ባንድ ላይ እንዲሁም በሌላኛው በፍልስጤም ድጋፋቸው በሚታወቁት የአየርላንድ ባንድ ኒካፕ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የወንጀል ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል።

የግላስተንበሪ ፌስቲቫልን በቀጥታ እያሠራጨ የነበረው ቢቢሲ የቦብ ቪላንን የሙዚቃ ዝግጅት እንዲሁም "ሞት ለእስራኤል ጦር" የሚለውን መፈክር በቀጥታ አስተላልፏል።

ይህንንም ተከትሎ ቢቢሲ የቀጥታ ሥርጭቱን ማቋረጥ ነበረበት የተባለ ሲሆን፣ መገናኛ ብዙኃንን በበላይነት የሚቆጣጠረው ኦፍኮም የተባለው ተቋም ቃለ አቀባይ "የዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ቀጥታ መተላለፉ በጣም አሳሳቢ ነው፤ ቢቢሲ መመለስ የሚገባው ጥያቄዎች አሉ" ብለዋል።

ውዝግቡን ተከትሎ ቦቢ ወይም በትክክለኛ ስሙ ፓስካል ሮቢንሰን ፎስተር በአቋሙ በመጽናት "ያልኩትን ብያለሁ" ሲል በኢንስታግራም ገጹ ምላሽ ሰጥቷል።

የድጋፍ እንዲሁም የጥላቻ መልዕክቶች እንዳጥለቀለቀው በዚህ ምላሹ ጠቅሶ ዩናይትድ ኪንግደም "የውጭ ፖሊሲዋን እንድትቀይር" ጥሪ አቅርቧል።

ሙዚቀኛ፣ ጊታሪስት እና ገጣሚ የሆነው ቦቢ እንዲሁም ከበሮ ተጫዋቹ ሌላኛው ቦብ በመጣመር 'ቦብ ቪላን' የተሰኘውን ባንድ የመሠረቱት በአውሮፓውያኑ 2017 ነው። 'ቦብስ' በመባል የሚታወቁት ሁለቱ ሙዚቀኞች ተመሳሳይ የመድረክ ስም ነው ያላቸው።

ሙዚቀኞቹ ፓንክ፣ የዩኬ ግራይም (ሂፕሆፕን) እንዲሁም የሮቢንሰን ፎስተር የጃማይካ ዘር ሐረግን የሚያንጸባርቀው ሬጌ፣ ዳንስ ሆል የሙዚቃ ዓይነቶችን በማጣመር ይጫወታሉ።

የዘፈኖቻቸው ግጥሞች ዘረኝነት፣ የፖሊስ ጭካኔ፣ ጭቆና፣ ካፒታሊዝም፣ አባትነት እንዲሁም መርዛማ ወንድነት (ቶክሲክ ማስኩሊኒቲ) በተሰኙ ርዕሶች ዙሪያ ያጠነጥናሉ።

በርካታ ነጠላ ዜማዎችን የለቀቁት ሙዚቀኞች የመጀመሪያ አልበማቸውን ያወጡት በአውሮፓውያኑ 2020 ነው።

ከአልበማቸው መውጣት በኋላ እንደ ኦፍ ስፕሪንግ፣ ዘ ሃይቭስ እና ቢፊ ክላይሮ ከተሰኙ ሙዚቀኞች እና ባንዶች ጋር አብረው የሙዚቃ ጉዞ አድርገዋል።

በተጨማሪም ከአራት ዓመት በፊት ሬዲንግ ኤንድ ሊድስ በተሰኘው የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ተጫውተዋል። ከለቀቋቸው አምስት አልበሞች መካከል ሁለተኛው እና 'ፕራይስ ኦፍ ላይፍ' [የሕይወት ዋጋ] የተሰኘው አልበማቸው በዩናይትድ ኪንግደም የሙዚቃ ሰንጠረዥ 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ኬራንግ የተሰኘውን የመጽሔት ሽልማት በምርጥ አልበምነት ዘርፍ በአውሮፓውያኑ 2022 አሸንፎ ነበር።

በዚያው ወቅት ዓመታዊው ሞቦ ሽልማት ምርጥ አማራጭ ሙዚቀኞች በሚል ሌላ ሽልማት አሸንፈዋል።

"በሃሳባችን አለመስማማት ይቻላል"

የ34 ዓመቱ ሮቢንሰን ፎስተር ገና ታዳጊ የ13 ዓመት ልጅ እያለ ነው ግጥም መጻፍ የጀመረው። ኒ ሃይ በሚል ስም በግጥሞቹ ታዋቂነትን አትርፏል።

የ14 ዓመት ልጅ እያለ በአውሮፓውያኑ 2005 በማንችስተር በተካሄደው የጥቁር እና እስያውያን የፖሊስ ማኅበር ጉባኤ ላይ ተጋብዞ ግጥሙን አቅርቧል።

እንዲሁም በትውልድ ስፍራው በለንደኗ ኢፕስዊች ለታዳጊዎች አርዓያ በመሆን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

ሙዚቀኛው ቦብ ቪላን የተሰኘውን ባንድ የጀመረው "ሰዎች ጥያቄ እንዲጠይቁ ለማነሳሳት" እንደሆነ በአንድ ወቅት ከትሪቡን መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጾ ነበር።.

ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የዳውንሎድ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ሙዚቃቸው በከፍተኛ ሁኔታ ፖለቲካዊ ዕይታ ለምን እንደሚንጸባረቅበት ተናግሮ ነበር።

"በዚህች አገር ባለው ተዋረድ ያሉ የኃይል አወቃቀሮች በሆነ ቦታ ብቻ እንዲወሰን ካደረገን የሕይወት ልምድ የመጣ ነው" ሲል ጥቁሩ ሙዚቀኛ ቦቢ ቪላን ያብራራል።

"እነዚህን ግጥሞች በበርካታ ታዳሚዎች ዘንድ ፊት ስንጫወት እንዲሁም ስለ እኛ ተሞክሮ ስናጋራ እፎይታን የሚፈጥር ሊሆን ይችላል።"

ሆኖም "በሌላ መንገድ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ስሜታዊ የሚያደርግ ነው" ይላል።

ሆኖም "ተጋላጭ ነን፤ እራሳችንን አውጥተን ስለ ራሳችን እና ስለ ማኅበረሰባችን እናወራለን፤ እንዘፍናለን። ታዳሚዎች መደሰት የሚችሉትን ያህል ከእኛ ሃሳብ ጋር አለመስማማት፣ መጮህ ወይም በፈለጉት መንገድ መቃወም" ይችላሉ ሲል ቦቢ ያስረዳል።

ቦቢ ሰዎች የማይስማሙበትን ጉዳዮች ላይ በነጻነት ሃሳቡን ለመወርወር አይፈራም።

ባንዱ ከሦስት ዓመት በፊት በግላስተንበሪ ፌስቲቫል ተጫውቷል።

ግላስተንበሪ ጋር የሚዲያ አጋርነት ላለው ቢቢሲ ሙዚቀኞቹ 'ዊክድ ኤንድ ባድ' የሚል ዘፈናቸውን የተጫወቱ ሲሆን፣ በዚህም ሙዚቃ ላይ የቀድሞዋ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬን ታቸርን የሚያወግዝ እንዲሁም "ሃብታሞችን እንብላ" የሚሉ መልዕክቶች ተካተውበታል።

ከዚህ ቀደም በትልቁ የሙዚቃ ትዕይነት 'ኮቼላ' እንዲሁም ከታዋቂዎቹ የዩኬ ሙዚቀኞች ኤሚል ኤንድ ዘ ስኒፈርስ፣ ላውሪ ቪንሰንት እና ሮክ ባንድ ኪድ ካፒቺ ጋር ተጣምሮ የተጫወተው ራፐሩ በዘንድሮው የግላስተንበሪ ፌስቲቫል ላይ ልጁን 'ድሪም ቢገር' በሚለው ዘፈን ላይ እንድታጅበው መድረክ ላይ አምጥቷት ነበር።

ቅዳሜ ዕለት በዌስት ሆልትስ መድረክ ላይ የነበረው የራፐሮቹ የሙዚቃ ዝግጅት በፍልስጤም ከፍተኛ ድጋፋቸው ከሚታወቁት የአየርላንዱ ኒካፕ ባንድ ቀጥሎ ነበር።

የዩኬን ጠቅላይ ሚኒስትር እና እስራኤልን በመድረክ ላይ ያወገዙት እና የሰደቡት የኒካፕ ሙዚቃ በቢቢሲ በቀጥታ ያልተላለፈ ሲሆን፣ በኋላ ግን አርትዖት ተደርጎለት በቢቢሲ አይ ፕለየር ላይ ተጭኗል።

ኒካፕ የአሜሪካ ቪዛቸው በቅርቡ እንዲሰረዝ ተደርጓል። ቦብ ቪላን በቅርቡ በአሜሪካ የሙዚቃ ጉዞ ለማድረግ አቅደው የነበሩ ቢሆንም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ ክርስቶፈር ላንዱ ቪዛቸው እንደሚሰረዝ አረጋግጠዋል።

ቦቢ ቪላን ለቪዛቸው መሰረዝ በሰጡት የቪዲዮ መግለጫ ምላሽ ፖለቲከኞች ታማኝነታቸው ለማን እንደሆነ የሚያሳይ፤ "እጅግ ሊያፍሩ" ይገባል በሚል ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው አውጥተዋል።

"መጀመሪያ ኒካፕ ነበሩ፤ አሁን እኛ ሁለታችን ነን" ብሏል ቦቢ።

አክሎም "በምንም መንገድ ይባል በምን የንጹሃን እልቂት ይቁም መባሉ መቼም ቢሆን ስህተት አይደለም" ሲል መልሷል።

የዓለም ሚዲያዎች መነጋገሪያ የሆነው ቦቢ ቪላን ልክ እንደ ኒካፕ ስማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ናኝቷል።