ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩኬ መንግሥት ቢቢሲ የእስራኤልን ጦር የሚያወግዝ መልዕክት በቀጥታ ስርጭት ወቅት በማስተላለፉ አወገዘ
የዩኬ መንግሥት በግላስተንበሪ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ራፐሮቹ ጥንዶች ቦብ ቪላን "ሞት" ለእስራኤል ጦር እያሉ ሲዘፍኑ በቢቢሲ ቀጥታ ስርጭት መተላለፉን "በጽኑ አወገዘ"።
ራፐሮቹ ቦቢ ቪላን በቤልፋስት ከራፐሮቹ ኒካፕ በፊት የሙዚቃ ሥራቸውን ሲያቀርቡ "ነፃ፣ ነፃ ፍልስጤም" እና "ሞት፣ ሞት ለአይዲኤፍ [የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት]" እያሉ ሲዘፍኑ ተሰምተዋል።
የቢቢሲ ቃል አቀባይ አንዳንድ አስተያየቶች "በጣም ፀያፍ ናቸው" ካሉ በኋላ፣ በቴሌቪዥን ስክሪኑ ላይ "በጣም ጠንካራ የሆኑ እና አግላይ ቋንቋዎች" ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
የሙዚቃ ዝግጅቱ በቢቢሲ አይፕሌየር ላይ ለዳግም ዕይታ እንደማይጫኑም አስታውቀዋል።
ፖሊስ ጥፋት መፈጸም አለመፈፀሙን ለመወሰን በቦብ ቪላን እና በኒካፕ የተሰጡ አስተያየቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን እየመረመረ መሆኑን ተናግሯል።
የፌስቲቫሉ አዘጋጆች ባወጡት መግለጫ ላይ "የግላስተንበሪ ፌስቲቫል የተሳታፊዎችን የጥላቻ ንግግሮች ወይም የአመፅ ድርጊቶችን አያስተናግድም" ብለዋል።
እነ ቦብ ቪላን የሙዚቃ ሥራቸውን ካቀረቡ በኋላ የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ሊዛ ናንዲ የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪን ማነጋገራቸው ተሰምቷል።
በዚህ ውይይታቸውም ወቅት ቢቢሲ የድምጻውያኑን ሥራዎች "ከማስተላለፉ በፊት ስላደረገው ጥንቃቄ" አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲፈልጉ ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል ።
መንግሥት የድምጻውያኑን ዘፈኖች ለድጋሚ ዕይታ በቢቢሲ አይፕሌየር ላይ ላለመጫን መወሰኑን በደስታ እንደሚቀበል ተናግሯል።
በሙዚቃ ድግሱ ላይ እነ ቦብ ቪላን ሥራቸውን ያቀረቡት በአይሪሽ ቋንቋ ከሚዘፍኑት የራፕ ቡድን አባላት ኒካፕ በፊት ነበር።
ቡድኑ ከቅርብ ወራት ወዲህ የበርካታ ዜና አውታሮች መነጋገርያ የሆነው፣ ሞ ቻራ በሚል ስም የሙዚቃ ሥራዎቹን የሚያቀርበው ሊም ኦግ ኦ ሃአናይድ ባለፈው ዓመት በአንድ መድረክ ላይ የተከለከለ የአሸባሪ ድርጅት ባንዲራ፣የሂዝቦላን፣ አሳይቷል በሚል የሽብር ወንጀል ከተከሰሰ ወዲህ ነው።
ራፐሩ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
ኒካፕ የራፐር ቡድን አባላት ቅዳሜ ዕለት ያቀረቡት የሙዚቃ ሥራ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች የተከታተሉት ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ላይ ጠንከር ያሉ ትችቶችን በመዘንዘር አቀንቅነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ከዚህ ቀደም ቡድኑን ለግላስተንበሪ ገጽታ "ተገቢ ያልሆኑ" ብለዋቸው ነበር።
ሊም ኦግ ኦ ሃአናይድ ከሁለት ሳምንት በፊት በለንደን ፍርድ ቤት ቀርቦ በዋስ ተለቅቋል።
የቦብ ቪላን እና የኒካፕ ሥራዎችን ተከትሎ ፖሊስ በመድረኩ ላይ የቀረቡ ሥራዎችን እና የተሰጡ አስተያየቶችን እንደሚመረምር ተናግሯል።
ፖሊስ "የወንጀል ምርመራ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥፋቶች ተፈጽመዋል ወይስ አልተፈጸሙን የሚለውን ለማረጋገጥ የተቀረጹ ምስሎች በባለሙያዎቻችን ይገመገማሉ" ብሏል።