ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አስር ሴቶች፣ አንድ ወንድ፡ በኢትዮጵያ አነጋጋሪ የሆነው የመተጫጨት የቴሌቪዥን ሾው 'ላጤ'
አንድ ወንድ እና ሴት ይገናኛሉ። ሴቲቱ በወንዱ ፍቅር ትወድቃለች። በወንዱ ዙሪያ የሚያንዣብቡ እና በፍቅር ለመማረክ የሚሞክሩ ተቀናቃኞችን ትከላከላለች።
በስተመጨረሻም ወንዱ ለፍቅሯ እጁን ይሰጣል።
በቴሌቪዥን በተከታታይ የሚተላለፉ እውናዊ ትርዒቶችን የሚከታተሉ ከሆነ እንዲህ ዓይነት በርካታ ሾዎችን አይተው ሊሆን ይችላል።
በአሜሪካ እና በአውሮፓ ዝነኛ የሆኑት ላቭ አይላንድ፣ ላቭ ኢዝ ብላይንድ እና ዘ ባችለር የተሰኙ ዝነኛ የቴሌቪዥን ትርዒቶች ላይ የተለመደ የታሪክ እና የሴራ ፍሰት ነው።
በኢትዮጵያ እንደ አዲስ የተዋወቀው ይህ የፍቅር ማግኛ፣ የመተጫጨት መንገድ ከተለመደው መንገድ ያፈነገጠ ሆኖ ቀርቧል።
በኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ዘንድ ክርክር ባስነሳው "ላጤ እውናዊ ትርዒት" ላይ ቤተል ጌታሁን፣ የመሳያህ ኃይለሚካዔልን ልብ ማሸነፍ ችላለች።
ላጤ ከአሜሪካው 'ዘ ባችለር' የተቀዳ ነው።
በዚህ ሾው ላይ አስር ሴቶች አሜሪካ ያደገውን እና ዳላስ የሚኖረውን የ38 ዓመቱን መሳያህ ልብ ለማሸነፍ ይፎካከራሉ።
ትርዒቱ ባሉት የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ሴቶቹ በቦክስ ውድድሮች፣ በቅርጫት ኳስ ግጥሚያዎች እንዲሁም ለፍራሽ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ በሚያደርጉት ከተለመደው ወጣ ያለ ፉክክር ይጋጠማሉ።
ላጤ የተላለፈው በዩቲዩብ ላይ ሲሆን፣ በወግ አጥባቂ ማኅበረሰብ መካከል ያልተለመደ የመተጫጨት ሥርዓትን ተከትሏል።
የ25 ዓመቷ ቤተል ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፖድካስት እንደተናገረችው በዚህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የመተጫጨት ሾው ላይ አሸናፊ መሆኗ "ሕልም" ሆኖባታል።
በዩቲዩብ የተላለፈው የላጤ የመጨረሻው ክፍል ብቻ ከ620,000 በላይ ተመልካቾችን ያገኘ ሲሆን፣ እርሷ ማሸነፏን "እንደ ክብር ማዕረግ" እንደምትቆጥረው ትናገራለች።
ቤተል የሚሰማት ዓይነት ስሜት ግን ሁሉም አይሰማውም።
"የመተጫጨት ሾዎች ሙሉ በሙሉ የምዕራባውያን ሀሳብ ናቸው" የሚለው የቪዲዮ ብሎገሩ ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባርያው) ነው።
"በኢትዮጵያ ውስጥ መተጫጨት ምን ጊዜም የግለሰቦቹ ጉዳይ ነው። ቀስ በቀስ በመጠናናት ውስጥ አልፎ እርግጠኛ ሲኮን ቤተሰብ ወይንም ማኅበረሰቡ እንዲያውቀው ይደረጋል።"
የ41 ዓመቱ ሰመረ ይህ ትርዒት ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነ ያምናል። ልክ በሽልማት መልክ እንደሚቀርቡ ተደርገው ነው የተሳሉት በማለት ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ መሆኑን ያምናል።
በርካታ ተመልካቾች ተመሳሳይ የሆነ ሃሳብን አንጸባርቀዋል። በዩቲዩብ ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል "ሴቶች፣ እናንተ ማንም በገንዘቡ በቀላሉ የሚገዛችሁ እቃ አይደላችሁም" ይላል።
ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ "በርካታ ፈጠራዎች በፕሮዳክሽኑ ላይ ታይተዋል። ነገር ግን ከባህል ያፈነገጠ ከሆነ ነጥቡ ምን ላይ ነው?" ሲል ይጠይቃል።
ቤተል ሴቶች በግልጽ አንድ ወንድን የራሳቸው ለማድረግ መፋለማቸው ከኢትዮጵያውያን ባህል ያፈነገጠ መሆኑን ትስማማበታለች።
ነገር ግን ሾዉ ከማዕከላዊ ጭብጡ ያለፈ ነገር እንዳለው ትከራከራለች።
"የሾዉ አጠቃላይ ነጥብ የተለያዩ ዓይነት ሴቶችን መወከል ነው።"
"እያንዳንዱን ክፍሎች ካየህ፣ እያንዳንዷ ሴት የተለያዩ ዓይነት ፈተናዎች እንዳሉባት፣ ከተለያየ ዳራ መምጣታቸውን፣ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት የማይነገሩ ወይንም በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ውክልና ያልተሰጣቸው ነገሮች መኖራቸውን ታስተውላለህ።"
ምንም እንኳ አከራካሪ ቢሆንም በዚህ ረገድ ላጤ የተሳካለት ይመስላል። በትርዒቱ ላይ የተሳተፉት ሴቶች ከተለያየ ሙያ ዘርፍ የመጡ ናቸው።
የሆቴል ማናጀር፣ የበረራ አስተናጋጅ እንዲሁም የሂሳብ ባለሙያዎች ይገኙባቸዋል።
ሴቶቹ ወዲያው ሲቀራረቡ፣አንዳቸው ለሌላኛቸውም ሆነ ለተመልካች የግል ታሪካቸውን ሲያጋሩ ይታያል።
በአንድ ልብን በሚሰብር ክፍል ላይ ተዋናይቷ ቪቪያን ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ብሔራዊ አገልግሎት ከምታስገባው እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከምትከሰሰው ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በስደት መምጣቷን ትናገራለች።
ቪቪያን ወደ ኢትዮጵያ ብቻዋን የመጣች ሲሆን፣ እናቷን ለአምስት ዓመታት ያህል አላየቻቸውም።
በእንባ ታጅባ "በጣም ናፍቃኛለች" ትላለች።
ሞዴሏ ራሄል ደግሞ ቤተሰቧን እና እህት ወንድሞቿን ለመርዳት ስትል ትምህርቷን አቋርጣ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራቷን ትናገራለች።
ሌላ ሴቶች እንዲሁ ሐዘንን ስለመግለጽ እና ላሳደጓቸው ሰዎች ያላቸውን ክብር ስሜት በተቀላቀለበት መልኩ ሲወያዩ ይታያል።
የእነዚህን ሴቶች እውነታ እንዲሁም የፍቅር ፍላጎት በማሳየት ረገድ ላጤ "ጊዜውን የሚመጥን ሾው" መሆኑን ፕሮዲውሰሯ መታሰቢያ ዮሴፍ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የላጤ ሾው የተላለፈበት ድንቅ የዩቲዩብ ቲቪ መሥራቾች ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው መታሰቢያ ሾዉ "ያናወጠው ነገር አለ" ነገር ግን የኢትዮጵያን ባህል ከመጋፋት ረገድ በጣም ሩቅ ነው ስትል ትሞግታለች።
"በመጀመሪያ ሴቶቹን በጣም አማላይ አድርጎ አጋኖ ያቀረበ አይደለም" የምትለው መታሰቢያ "በጣም ሐቀኛ የሆነ፣ የእንተዋወቅ ዓይነት ደረጃ ላይ ያለ መተጫጨት እንዲሆን ነው ያደረግነው" ብላለች።
አክላም ተመልካቾችም ባህል የሚለውን ነገር አንዲሞግቱ ይጠይቃል "ባህል ምንድን ነው? እኛ የማንለወጥ ነን? የሚለው ላይ ውይይት እንዲፈጠር አድርገናል።"
ይህ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ዝነኛ የሆነው እውናዊ የቲቪ ትርዒትን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ የተደሰቱም በርካታ ናቸው።
"እንዲህ ዓይነት አደጋ ተጋፋጭነትን በጣም ነው የወደድኩት፣ እንደ ማኅበረሰብ ቁጥብ በመሆናችን . . . ሁሌም ሌሎች ትርዒቶችን በኢትዮጵያዊ መልክ ማየት እፈልግ ነበር። ይህ መንገድ ከፋች ነው" ይላል።
ሌላ ተመልካች በበኩሉ "ዘ ባችለርን በኢትዮጵያ አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ነገር ግን ይህንን ወደ ሕይወት በማምጣት ረገድ በጣም ምርጥ ሥራ ሠርታችኋል።"
የትርዒቱን ስኬት ተከትሎ ድንቅ ቲቪ ሁለተኛ ምዕራፍ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው።
አሁን ደግሞ አንዲት ሴት ከሚቀርቡላት 10 ወንዶች መካከል እንድትመርጥ ይሆናል ትላለች መታሰቢያ።
"ከተመልካቾቻችን በርካታ ግብረ መልሶችን እያገኘን ነው። ሰዎች ነገሮች ተቀይረው ማየት ይፈልጋሉ" ስትል ታስረዳለች።
ቤቴል እና መሳያህ የፍቅር ጉዟቸው በአጭሩ ተቀጭቷል።
"እርሱ አሁን አሜሪካ ከልጁ ጋር ነው ያለው። ስለዚህ በጣም አስቸጋሪ ነው። . . . እውነቱን ለመናገር ወዴት እንደሚሄድ እርግጠኛ አይደለሁም" ትላለች።
ቤተል በሾዉ ላይ ከተሳተፉት ጋር "በጣም የቅርብ ጓደኛሞች ነን" ስትል በመግለጽ አሁንም እንደሚገናኙ ትናገራለች።
ላጤ "የኢትዮጵያን የፍቅር መልክ" በማሳየቱ በጣም እንደምትኮራ የምትናገረው ቤተል፣ በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ሴቶችን የተሻለ ውክልና እንደሚሰጥ ያላትን እምነት ትናገራለች።
"ሴቶቸን የምናቀርብበት እና ራሳቸውን የሚገልጹበት አዲስ መንገድ ነው" በማለት ትርዒቱን "አዲስ የምናይበት መነጽር ነው" ስትል ሃሳቧን ትቋጫለች።