በዓለም አቀፍ የፋሽን መድረክ ተመራጭ የሆኑ ሞዴሎች መገኛዋ አገር

በዓለም አቀፉ የፋሽን ኢንዱስትሪ ከገነኑ እና ተመራጭ ከሆኑ አገራት መካከል ደቡብ ሱዳን አንዷ ናት።

ወዛሙ ጥቁር የቆዳ ቀለማቸው እና ጠምበለል ቁመታቸው ደቡብ ሱዳናውያን ሞዴሎችን ተመራጭ አድርጓቸዋል።

ምንም እንኳን አገሪቷ በእርስ በርስ ጦርነት ስሟ ቢነሳም በፋሽኑ ዘርፍ ደግሞ መድረኩን በሚያደምቁ ሞዴሎች አገርነት ትታወቃለች።

ከእነዚህ በፋሽኑ ዓለም ከሚያንጸባርቁ የደቡብ ሱዳን ፋሽን ሞዴሎች መካከል አሮፕ አኮል አንዷ ናት።

የፋሽን ከተሞች የሚባሉትን የለንደን እና የፓሪስ መድረኮችን ከሚያደምቁት መካከል ትጠቀሳለች።

አኮል ቅንጡ የልብስ አምራቾች አዳዲስ ምርቶቻቸውን በሚያስተዋውቁበት ወቅት በቀዳሚነት ለማሳያነት ከሚመርጧቸው ዓለም አቀፍ ሞዴሎች አንዷ መሆን ችላለች።

"ከአስራ አንድ ዓመቴ ጀምሮ ሞዴሊንግን በኢንተርኔት እከታተል ነበር" ትላለች በአሁኑ ወቅት በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው አኮል።

አኮል ባለፉት ሦስት ዓመታት ዝነኛ መሆን ችላለች።

በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስመ ጥር ከሆኑት ናኦሚ ካምፔል ጋር በአንድ መድረክ የፋሽን ትርዒት አሳይተዋል።

ምንም እንኳን ለሥራ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ብቸኛ የሚያደርግ ቢሆንም በዓለም አቀፉ የፋሽን ትርዒቶች ከትውልድ ሥፍራዋ ደቡብ ሱዳን የሚመጡ ሞዴሎችን ማግኘቷ ሁኔታውን ቀለል አድርጎላታል።

"ደቡብ ሱዳናውያን በውበታቸው በጣም ታዋቂ ሆነዋል" ትላለች ጥርት ያለ፣ ለስላሳ እና የሚያንጻበርቅ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላት 1 ሜትር ከ79 እርዝማኔ ያላት መለሎዋ አኮል።

በአውሮፕላን ጉዞዎች ላይ ባሉ የፋሽን መጽሔቶች ላይም አኮል አትታጣም።

አኮል ብቻ ሳትሆን ሌሎች ደቡብ ሱዳናውያን ሞዴሎችም ደምቀውበታል።

እንደ አኮል ካሉ ጀማሪዎች በተጨማሪ በፋሽን ዘርፉ ስማቸው ከናኘው መካከል አኖክ ያይ፣ አዱት አኬች እና አሌክ ዌክ ይጠቀሳሉ።

አሌክ ዌክ ከለንደን የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ተመልምላ በፋሽኑ መድረክ ዓለም አቀፍ ስኬትን የተጎናጻፈች የመጀመሪያዋ የደቡብ ሱዳን የፋሽን ሞዴል ናት።

ወቅቱም ከ30 ዓመታት በፊት ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታዋቂው ቮግ መጽሔት ሽፋን ላይ ፎቶዋ በተደጋጋሚ ወጥቷል፤ እንዲሁም ሽቶን ጨምሮ ታዋቂ የቅንጦት ዕቃዎችን በማምረት የሚታወቁት ዲዮር እና ሉቪ ቪቶን ሞዴል ናት።

ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ሞዴሎች ተመራጭነታቸው የመቀነስ አዝማሚያ አይታይበትም።

በፋሽን ኢንዱስትሪው መሪ የሚባለው እና ኤጀንሲዎችን፣ አምራቾችን እንዲሁም ሞዴሎችን የሚያገናኘው 'models.com' የተሰኘው መድረክ የሞዴሊንግ ምርጥ 50 'የወደፊት ከዋክብት' ዓመታዊ ዝርዝርን ያጠናቅራል። በቅርቡ ባደረገው ምርጫ ከአምስቱ ሞዴሎች አንዷ የደቡብ ሱዳን የዘር ሐረግ እንዳላት አሳይቷል።

ይህ ብቻ አይደለም ታዋቂው የፋሽን መጽሔት ቮግ "የፋሽን መድረኮችን ሊያስደምሙ የሚችሉ 11 ወጣት ሞዴሎች" በሚል ርዕስ በዚህ ዓመት ባወጣው ዝርዝሩ አራቱ የደቡብ ሱዳን ሞዴሎች ናቸው።

"ሞዴል ምን ሊሆን ይገባዋል ተብለው የሚጠበቁ መስፈርቶች አብዛኞቹ የደቡብ ሱዳን ሞዴሎች አሏቸው" በማለት በደቡብ ሱዳን የፋሽን ሳምንት አዘጋጅ የሆነው ዳውሰን ዴንግ ይናገራል።

"ምርጥ የሆነ ጥቁር ቆዳ አላቸው። ቁመታቸውም ረዥም ነው" ይላል።

የ'ፈርስት ሞዴል ማኔጅመንት' መልማይ የሆኑት ሉቺያ ጃኖሶቫ በበኩላቸው "በጣም ቆንጆ ናቸው፣ የሚያምር ቆዳ፣ ቁመታቸው" ሲሉ ስለ ደቡብ ሱዳናውያን ሞዴሎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ሆኖም የፋሽን አምራቾች ለምን ደቡብ ሱዳኖችን ከሌሎች አገራት አስበልጠው እንደሚፈልጉ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

"ምን እንደሆነ ልናገር አልችልም፤ ምክንያቱም ከሞዛምቢክ፣ ከናይጄሪያ ወይም ከሌሎች አገራት ቆንጆ ሴቶች አሉ" ሲሉ ያክላሉ።

እንደ ጊቨንቺ፣ አርማኒ ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ዲዛይነሮች ጋር የሠራችው ደቡብ ሱዳናዊቷ ሞዴል አኩር ጎይ፤ የደቡብ ሱዳን ሞዴሎች እንዲህ ተፈላጊ የሆኑት በአካላዊ ውበታቸው ብቻ ሳይሆን "በጽናታቸው" ጭምር እንደሆነ ታምናለች።

ጎይ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ነው የተወለደችው።

ጎይ በልጅነቷ፣ እንደ አኮል እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት አገር ኡጋንዳ ተሰደደች።

በርካቶች ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነጻ ከወጣችበት ከአውሮፓውያኑ 2011 በኋላ በነበሩት ዓመታት ነው የተሰደዱት።

ደቡብ ሱዳን እንደ አዲስ አገርነት ስትመሠረት ዓለም ትልቅ ተስፋ ተጥሎባት ነበር፤ ነገር ግን ልክ ከሁለት ዓመት በኋላ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ።

በዚህ ደም አፋሳሽ ጦርነት 400 ሺህ ደቡብ ሱዳናውያን ሲቀጠፉ 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ቀያቸውን ለቀው እንደ ኡጋንዳ ወዳሉ አጎራባች አገራት ተሰደዋል።

የእርስ በርስ ጦርነቱ ከአምስት ዓመታት በኋላ ቢቋጭም፣ ተጨማሪ ግጭቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ድህነት ለበርካቶች ስደት ምክንያት ሆኗል።

በቅርቡ በመንግሥት እና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ እየተባባሰ ሲሆን፤ ይህም አገሪቱ ተመልሳ ወደማትወጣበት የእርስ በርስ ጦርነት ትገባለች የሚል ስጋት ፈጥሯል።

በጦርነት የምትናጠውን አገሯን ትታ ወደ ሱዳን በልጅነቷ የተሰደደችው ጎይ ሞዴል መሆን "ትልቅ ህልሟ" ነበር።

ባለፈው ዓመት በአንድ ወኪል አማካይነት በፌስቡክ ተመልምላ ህልሟ እውን ሆነ።

የመጀመሪያ ሥራዋንም ለታዋቂው የጣሊያን ፋሽን ኩባንያ ሮበርቶ ካቫሊ የፋሽን ትርዒት አሳየች።

ምንም እንኳን ጎይ ጉዞዋ ቀለል ያለ ቢሆንም ለአንዳንድ ደቡብ ሱዳናውያን ሞዴሎች ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ መምጣት ፈታኝ ነው።

ታይምስ የተሰኘው የዩናይትድ ኪንግደም ጋዜጣ ባደረገው የምርመራ ዘገባ በኬንያ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች ወደ አውሮፓ ከተወሰዱ በኋላ የፋሽን ትርዒት ለማሳየት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።

በርካቶች ደግሞ የሞዴሊንግ ሥራዎችን ከጨረሱ በኋላ ለኤጀንሲዎቻቸው በሺዎች የሚቆጠር ዩሮ ዕዳ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።

እነዚህ ኤጀንሲዎች ሞዴሎቻቸውን በሚመለምሉበት ወቅት የሚያስፈርሟቸው ውሎች ከአገራቸው የመጡባቸውን በረራዎች እንዲሁም ቪዛዎች መክፈል እንዳለባቸው ያሰፍራሉ።

አኮል ተመሳሳይ ጉዳይ እንዳጋጠማት ትናገራለች። በአውሮፓውያኑ 2019 ሊመለምላት የነበረው ኤጀንሲ በርካታ ክፍያዎችን እንድትከፍል ጠይቋት ነበር።

ከዚያም ከሦስት ዓመታት በኋላ በኡጋንዳ እየኖረች የነበረችው አኮል ሌላ ስመ ጥር ኤጀንሲ ጠራት።

ወጣት ደቡብ ሱዳናውያን ልምዶቻቸውን በተቀናጀ መልኩ እንዲያዘጋጁ የሚያግዘው ዴንግ በበኩሉ አንዳንድ ሞዴሎች ክፍያቸው በገንዘብ ሳይሆን በልብሶች እንደሚከፈላቸው ቅሬታቸውን መናገራቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሌሎች ደግሞ ቤተሰቦቻቸው የሞዴሎቹን የሙያ ምርጫ ጥያቄ ውስጥ ስለሚከቱት ሌላ ፈተና ይገጥማቸዋል። ነዋሪነቷን በለንደን ያደረገችው አኮል ስለ ቤተቦቿ ስትናገር ሙያውን "አልደገፉትም፤ አሁንም አይደግፉትም" ትላለች።

ዴንግ በበኩሉ በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ነገሮችን ቢረዱም አንዳንዶች ደግሞ ሞዴሊንግን ከወሲብ ንግድ ጋር ያመሳስሉታል ይላል።

ወላጆች ሴት ልጆቻቸው "በሰዎች ፊት ለምን እንደሚራመዱ" ግራ ያጋባቸዋል ይላል።

በአንድ ወቅትም አንዲት ሞዴል ለመጀመሪያ ጊዜ ሌላ አገር ዝግጅት ልታቀርብ በረራ ልታደርግ በነበረበት ወቅት ቤተሰቦቿ አየር ማረፊያ ተከትለው ሄደው እንደከለከሏት ይናገራል። ዴንግ ይህችን ሞዴል እያገዛት የነበረ ሲሆን በኋላም ቆይተው ቤተሰቦቿ እንደተቀበሏት ያስረዳል።

በአሁኑ ወቅት ይህችው ሞዴል እነዚህን ቤተሰቦቿን እንደምታስዳድር እና እህት እና ወንድሞቿን እንደምታስተምር ገልጿል።

ምንም እንኳን ዓለም አቀፉ የፋሽን መድረክ ተለዋዋጭ ቢሆንም የደቡብ ሱዳናውያን ሞዴሎች ተወዳጅነት መቼም እንደማይደበዝዝ ነው ሞዴሎቹ የሚናገሩት።