የቻይና መንግሥት የመረጃ ሰርሳሪዎች በአሜሪካ መሠረተ ልማት ላይ አነጣጥረዋል - ኤፍቢአይ

በቻይና መንግሥት የሚደገፍ የመረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድን እንድ ኃይል እና የውሃ መስመር ያሉ ቁልፍ የህዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረውን የጠለፋ ሙከራውን ማክሸፍ መቻሉን ኤፍቢአይ ተናግሯል።

የኤፍቢአይ ዳይሬክተር “ቮልት ታይፎን” የተሰኘውን ቡድን ለመዝጋት ዘመቻ መካሄዱን ለሕግ አውጭዎች ተናግረዋል።

ቡድኑ የአሜሪካ ንብረቶችን መረጃ ለማግኘት በመቶዎች የሚቆጠሩ የቆዩ የቢሮ ራውተሮችን ሰርጎ ገብቷል ሲሉ ክሪስቶፈር ራይ ተናግሯል።

የቻይና መንግስት ስለቀረበበት ክስ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ቻይና ቀደም ሲል በመንግስት የሚደገፍ የሳይበር ስለላ በሌሎች አገራት ላይ ታካሂዳለች መባሉን ውድቅ አድርጋዋለች። ከዚህ ባለፈም ዩናይትድ ስቴትስን "የዓለም ትልቋ የመረጃ ጠላፊ አገር እና የዓለም አቀፍ የሳይበር ቀማኛ" ስትል ከሳታለች።

ራይ ረቡዕ ዕለት ለአሜሪካ ኮንግረስ ኮሚቴ እንደተናገሩት ቻይና ሆን ብላ ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት የአሜሪካን ቁልፍ የመሠረተ ልማት ስርአቶችን ለማሽመድመድ ከወዲሁ መሠረት እየጣለች ነው።

"የቮልት ታይፉን" የጠለፋ ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው ባለፈው ግንቦት ወር በዩኤስ ውስጥ ሲሆን ቡድኑ የመንግስት ኢሜል አካውንቶችን ሰብሮ መግባትን ጨምሮ በርካታ የህዝብ መሠረተ ልማቶችን ኢላማ አድርጓል ሲል ማይክሮ ሶፍት አስጠንቅቆ ነበር።

ኤፍቢአይ ቡድኑ ያነጣጠረው እንደ የውሃ ማጣሪያ፣ የኃይል ማሰራጫ፣ የትራንስፖርት ሥርዓቶች፣ ነዳጅ እና ጋዝ ማስተላለፊያ እና ቴሌኮሙኒኬሽን አውታሮችን የመሳሰሉ የአገሪቱን ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ ነው።

ራይ አክለውም በቻይና መንግስት የሚደገፈው ቡድን ማልዌር (በመረጃ ሰርሳሪዎች የሚዘጋጅ መረጃ ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ የሚውል ሶፍት ዌር) በመጫን እና ከመሠረተ ልማቶች ጋር የተገናኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ አሮጌ እና ጊዜ ያለፈባቸው ራውተሮች ተቆጣጥሯል።

"የቮልት ታይፉን ማልዌር ቻይና በሌሎች አገሮች አሰሳ እና ወሳኝ በሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ የምትፈጽመውን የኔትወርክ ምዝበራ እንድትደብቅ አስችሏታል" ሲሉ በአሜሪካ-ቻይና ውድድር ዙሪያ ለኮንግረሱ ኮሚቴ ተናግረዋል።

ይህም መረጃ ሰርሳሪዎቹ "አደጋ ለመፍጠር እና በአሜሪካ ዜጎች ላይ ጉዳት ለማድረስ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ያሳያል" ብሏል።

“ቻይናጊዜ እንደደረሰ ከወሰነች በፖለቲካዊ ወይም በወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ አታተኩርም” ሲሉም አክለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ቻይና ግጭት ከተፈጠረ በሚል የግንኙነት መቆራረጥ ሊፈጠር የሚችል አቅም ለመገንባት መሠረተ ልማቶች ላይ ማነጣጠሯን ቀደም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በዩኤስ እና በቻይና መካከል የሚካሄደውን ውድድር የሚመለከተው ኮሚቴ ረቡዕ ዕለት ባካሄደው ስብሰባ ላይ ሊቀመንበሩ ይህ "በአሜሪካ ድልድዮች እና የኃይል ማመንጫዎች ላይ ቦምቦችን ከማስቀመጥ ጋር የሚመጣጠን የሳይበር ጥቃት" ነው ብለዋል።

የሳይበር ጥቃት ውንጀላውን በሙሉ ውድቅ በማድረግ ቤጂንግ ኮሚቴውን ወቅሳለች። የቻይና መንግስት ኮሚቴው “አድሎአዊ የሆነውን ርዕዮተ ዓለም እና የቀዝቃዛ ጦርነት አስተሳሰብን እንዲያስወግድ” ጠይቋል።

ለሳይበር ጥቃት የተዘጋጁ የቤጂንግ ሃብቶችን በዝርዝር የገለጹት ራይ፤ የቻይና መረጃ ምዝበራ ፕሮግራም "ከሌሎች ዋና ዋና አገራት ሁሉ የበለጠ" ነው ብለዋል ።

የኤፍቢአይ የሳይበር ባልደረቦች በቻይና አቻዎቻቸው 50 ለ 1 የሆነ ብልጫ እንደተወሰደባቸውም አክለው ተናግረዋል።