ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስዊድን ፖሊስ ስቶክሆልም የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ደጃፍ የተገኘን ዕቃ አወደመ
ስቶክሆልም በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ደጃፍ የተገኘ "አደገኛ ነገር" እንዲወድም መደረጉን የስዊድን ፖሊስ አስታወቀ።
የእስራኤል አምባሳደር "የጥቃት ሙከራ" ያሉትን ክስተት ለማጣራት ፖሊስ አካባቢውን ከቦ መቆየቱ ታውቋል።
ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ገና መሆኑን ፖሊስ ለቢቢሲ አስታውቋል።
ጉዳት የደረሰበት ሰው እንደሌለም ተናግሯል።
ቃል አቀባዩ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጹት የኤምባሲው ሠራተኛ ዕቃውን አይተው ለፖሊስ አሳውቀዋል።
ዕቃውን የመረመረው ብሔራዊ የቦምብ ቡድን መሆኑን እና ከጥቅም ውጭ እንዲሆን መወሰኑንም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን ሁኔታው በጣም ነው አሳሳቢ ከማለት ባለፈ የስዊድን የደህንነት አገልግሎት ተጠያቂው ማን እንደሆነ እያጣራ ነው ብለዋል።
ክሪስተርሰን አክለውም በኤምባሲው እና በአይሁድ ተቋማት ዙሪያ ቁጥጥር ተጠናክሯል ሲሉ ገልጸዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ለቲቪ 4 እንደተናገሩት መሳሪያው ክትትል እየተደረገበት እንዲፈነዳ ተደርጓል።
የስዊድን ጋዜጦች የሆኑት ኤክስፕረሰን እና አፍቶንባልድ ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጮችን በመጥቀስ የእጅ ቦምብ መገኘቱን ዘግበዋል።
ኤስቪቲ የተሰኘው የአገሪቱ ብሔራዊ ጣብያ በበኩሉ ዕቃው በሚወገድበት ወቅት በአሸዋ ተሞሉ ከረጢቶችን የያዙ የታጠቁ ፖሊሶች በቦታው ተገኝተው ነበር ብሏል።
በስዊድን የእስራኤል አምባሳደር በበኩላቸው በኤምባሲው እና በሠራተኞቹ ላይ “የተሞከረ ጥቃት” ነው ብለዋል።
"በሽብር አንበረከክም" ከማለት ባለፈ የስዊድን ባለስልጣናት ለነበራቸው “ፈጣን ምላሽ” አምባሳደር ዚቭ ኔቮ ኩልማን በኤክስ ገፃቸው አመስግነዋል።
የስዊድን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ኢባ ቡሽ በበኩላቸው “ደንግጫለሁ” ብለዋል፡ “በእስራኤል ላይ ያለው ጥላቻ አስፈሪ ነው። የጽንፈኝነት ጥቃት መቆም አለበት” ሲሉ አክለዋል።
ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ያለው ፖሊስ ዕቃውን ኤምባሲው ደጃፍ ማን እንዳስቀመጠው ግን አልገለጸም።