ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩቲዩብ የቲቢ ጆሽዋ ንብረት የሆነውን የኢማኑኤል ቲቪ ቻናልን ዘጋ
ዩቲዩብ፤ የጥላቻ ንግግር ደንብ ጥሷል በማለት በቅርቡ ፈጽሞታል በተባለው ከባድ በደል ክስ የቀረበበትን የሟቹ ናይጄሪያዊ ሰባኪ የቲቢ ጆሽዋ ቴሌቪዥን ታዋቂ የዩቲዩብ ቻናልን ዘጋ።
ይህ የዩቲዩብ ውሳኔ ይፋ የሆነው ቢቢሲ እና ኦፕንዴሞክራሲ ሟቹ ሰባኪ ቲቢ ጆሽዋ መጠነ ሰፊ የወሲብ ጥቃቶችን እና አካላዊ ሰቆቃዎችን መፈጸሙን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ያየዘ የምርመራ ዘገባ ካቀረቡ ከሳምንታት በኋላ ነው።
ቲቢ ጆሽዋ ከአካባቢ ፓስተርነት ወደ ዓለም አቀፍ ታዋቂነት እንዲሸጋገር ‘ኢማኑኤል ቲቪ’ የተባለው የራሱ የቴሌቪዥን ስርጭት ቁልፍ ሚና መጫወቱ ይነገራል።
ታዋቂው ናጄሪያዊ ሰባኪ ከሦስት ዓመት በፊት የሞተ ሲሆን፣ ሲናጎግ ቸርች ኦፍ ኦል ኔሽንስ የተባለው ቤተክርስቲያኑ በአሁኑ ጊዜ በባለቤቱ ኤቭሊን ጆሽዋ እየተመራ ይገኛል።
ቤተክርስቲያኑ እስካሁን የዩቲዩብ ቻናሉ ስለመዘጋቱ የሰጠው አስተያየት የለም፣ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በቲቢ ጆሽዋ ላይ የቀረቡት ክሶች “መሰረተቢስ” ናቸው ማለቱ ይታወቃል።
አሁን እንዲዘጋ የተወሰነበት የኢማኑኤል ቲቪ ዩቲዩብ ቻናል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች እና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዕይታን ያገኘ ነው።
ይህ ቻናል የዩቲዩብን የማኅበረሰብ መመሪያዎችን ጥሷል በሚል የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ ነው ዕግድ የተጣለበት።
ከቢቢሲ ጋር በመሆን ኦፕንዴሞክራሲ ባካሄደው ምርመራ ኢማኑኤል ቲቪ በበይነ መረብ በኩል ያሉትን ይዘቶች የፈተሸ ሲሆን፣ ዩቲዩብ ላይ ቢያንስ 50 “አዋራጅ/ስቃይ” የሚታይባቸው ቪዲዮዎችን አግኝተዋል።
የምርመራ ቡድኑ እነዚህን ቪዲዮዎች በተመለከተ ለዩቲዩብ በማሳወቃቸው ቻናሉ ከሰኞ ጥር 20/2016 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲታገድ ተደርጓል።
በጉግል ባለቤትነት ስር የሚገኘው የቪዲዮ ማጋሪያ መድረክ የሆነው ዩቲዩብ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት፣ ኢማኑኤል ቲቪ “የጥላቻ ንግግር ደንቦችን . . . በመጣሱ እንዲዘጋ ተደርጓል” ብሏል።
ቲቢ ጆሽዋ “በፈውስ” አገልግሎቱ ዝናን ያገኘ ሲሆን፣ የአካል ጉዳት ያለባቸው እና በጽኑ የታመሙ ሰዎች ተፈወሱባቸዋል የተባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፈውስ አገልግሎቶች በፊልም ተቀርጸዋል። ነገር ግን በርካታ የቀድሞ የቤተክርስቲያኗ አባላት ሐሰት መሆናቸውን አጋልጠዋል።
በኦፕንዴሞክራሲ በኩል የቀረበ ዘገባ በኢማኑኤል ቲቪ ምስሎች አማካይነት የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በሰንሰለት ታስረው፣ የሕክምና መረጃዎችን ማዛባት እና በቲቢ ጆሽዋ ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በተናገሩ ሴቶች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ቲቢ ጆሽዋ ፈጽሞታል የተባለው በደል ይፋ ከሆነ በኋላ ዲኤስቲቪ እና ጎቲቪ የተባሉ ተወዳጅ ቻናሎችን የሚያቀርበው ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ የሳተላይት ቴሌቪዥን አግልግሎት ሰጪ ኢማኑኤል ቲቪን ከሚያሰራጫቸው ቴሊቪዥን ጣቢያዎች ዝርዝር ውስጥ አስወጥቶታል።
ኢማኑኤል ቲቪ ቻናል በመላው ዓለም በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች በመታየት ለበርካታ ዓመታት ስኬታማ የክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያ በመሆን ቆይቷል።
ቢቢሲ በቲቢ ጆሽዋ ላይ ለሁለት ዓመታት ያካሄደውን የምርመራ ዘገባ ይፋ ማድጉን ተከትሎ፣ በዘገባው ላይ ስለሚያውቁት ነገር ምስክርነት በሰጡ ግለሰቦች ላይ ከቤተክርስቲያኗ እና ከኢማኑኤል ቲቪ ጋር ግንኙነት ባላቸው አካውንቶች አማካይነት ዛቻ እና ማስፈራሪያ ተሰንዝሮባቸዋል።
ይህም በኦፕንዴሞክራሲ አማካይነት ለዩቲዩብ ሪፖርት ቢደረግም እስካሁን እንዲነሱ አልተደረገም።
ዩቲዩብ እና ሌሎችም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ከሚከተሉት የደኅንነት ፖሊሲዎች አንጻር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠንካራ ክትትል እና ትችት እየተሰነዘረባቸው ነው።