የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዛከርበርግ ልጆቻችን ተጎድተዋል ያሉ ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠየቀ

ከፍተኛ ክርክር በተካሄደበት የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተገኘው የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዛከርበርግ በማህበራዊ ሚዲያው ምክንያት ልጆቻችን ተጎድተውብናል ያሉ ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠይቋል።

ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታን የሚመራው ዛከርበርግ በምክር ቤቱ ወደተገኙት ቤተሰቦች ፊቱን አዙሮ እናንተ ያለፋችሁበት መንገድ ለማንም አይገባም ብሏል።

ከዛከርበርግ በተጨማሪ የቲክቶክ፣ ስናፕ፣ የኤክስና ዲስኮርድ ማሕበራዊ ትስስር ገጽ መሪዎች በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርበው አራት ሰዓት ለሚጠጋ ጊዜ ከሪፐብሊካን እና ዲሞክራቶች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት እነዚህ ማሕበራዊ ገጾች የህጻናትን ደህንነት እንዴት እንደሚጠበቁ ለማወቅ በማለም ነው ወደ ምክር ቤቱ የጠሯቸው።

የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊዎችን ለጥያቄ ሲጠራ እምብዛም የተለመደ አይደለም።

ዛከርበርግ እና የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሾ ዚ ቼው ምክር ቤት እንዲቀርቡ ሲጠየቁ የተስማመው ቢሆንም የስናፕ፣ የኤክስ (ትዊተር) እና ዲስኮርድ ኃላፊዎች ለመጠየቅ አሻፈረኝ ብለው ነበር። ሆኖም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ምክር ቤት ተገኝተዋል።

በእዚህ ውይይት ላይ በማሕበራዊ ሚዲያ ሰበብ ልጆቻቸው እራሳቸው እንደጎዱ ወይም እንደገደሉ የሚገልጹ ቤተሰቦች ታድመዋል።

በዚህ ውይይት ዋነኛው ትኩረት ስራ አስፈጻሚዎቹ የሚመሯቸው የትስስር ገጾች ህጻናትን ከወሲባዊ ድርጊቶች ተጋላጭነት እንዴት እንደሚታደጉ የሚጠይቅ ቢሆንም ሌሎች ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ “የሶሰት ልጆች አባት እንደሆነ ሰው እኔ እራሱ ዛሬ እየተወያየንበት ያለነው ጉዳይ ለወላጆች ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ” እረዳለሁ ብሏል።

ቀጥሎም እሱ በሚኖርብት ሲንጋፖር ባለው ህግ ምክንያት ልጆቹ ቲክቶክ እንደማይጠቀሙ ገልጿል።

በዚህ ውይይት በርካታ ጥያቄዎችን ያስተናገደው የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዛከርበርግ ነው። ዛከርበርግ በሌላኛው የአሜሪካ ምክር ቤት ስምንት ጊዜ ቀርቧል።

ስራ አስፈጻሚው ከአባላቱ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡለት ሲሆን የሪፐብሊካን አባል የሆኑት ጆሽ ሀውሊ፤ ዛከርበርግ በምክር ቤቱ የሚገኙትን ቤተሰቦች ይቅርታ እንዲጠይቅ ጋብዘውታል።

እሱም ከመቀመጫው ተነስቶ ፊቱን ወደ ታዳሚው በመመለስ “ባለፋችሁበት ነገር ሁሉ በጣም አዝናለሁ። አስፈሪ ነው። ማንም እናንት ባለፋችሁበት ማለፍ አይገባውም” ብሏል።