ዩኬ ቪዛ ለመከልከል የዛተችባቸው የአፍሪካ አገራት ስደተኞችን መልሰው ለመቀበል ተስማሙ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የቪዛ ክልከላ ለመጣል የዛተችባቸው ሦስት የአፍሪካ አገራት ስደተኞችን መልሰው ለመቀበል ተስማሙ።

የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባና መሐሙድ በአገራት ላይ የቪዛ ቅጣት እንደሚጥሉ ካስታወቁ ከአንድ ወር በኋላ ናሚቢያ እና አንጎላ ስደተኞችን እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም ስደተኞችን መልሶ በመቀበል ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር እንደምትተባበር ገልጻለች።

የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባና መሐሙድ ከሦስቱ አገራት ጋር የተደረሰውን ስምምነት አስመልክተው "መልዕክቴ ግልጽ ነው። አገራት ስደተኞቻቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆኑ እርምጃ ይወሰድባቸዋል" ብለዋል።

አንጎላ፣ ናሚቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስደተኞችን ከዩናይትድ ኪንግደም ለመቀበል ካልተስማሙ የቪዛ ዕግድ እንደሚጣልባቸው የዩኬ መንግሥት አስጠንቅቆ ነበር።

ስደተኞችን ወደ ሦስቱ የአፍሪካ አገራት የመመለስ ሒደት በመጓተቱ ምክንያት እክል እንደገጠመው የዩኬ መንግሥት አስታውቋል።

ስደተኞቹ በሌሉበት ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ መጠየቁም ስደተኞችን የመመለስ ሒደቱን እንዳዘገየው ተገልጿል።

ሦስቱ አገራት "የተመላሽ ስደተኞችን ጉዳይ ተቀባይነት በሌለው መንገድ በማጓተታቸው" የቪዛ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ከተገለጸ በኋላ አገራቱ አሠራራቸውን እንደሚለውጡ ተናግረዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም የስደተኞች ፖሊሲዋን ታኅሣሥ ላይ ስታሻሽል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና መሐሙድ እንደተናገሩት፤ ከአዲሱ አሠራር ጋር በሚጣጣም መንገድ የማይሄዱ አገራት ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ዩኬ እጥላለሁ ካለቻቸው ቅጣቶች መካከል ለአገራቱ የሚሰጥ ቪዛን "በድንገተኛ ምክንያት ማቋረጥ" ይጠቀሳል።

በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የገቡ ስደተኞቻቸውን ለመቀበል ሦስቱ አገራት የተስማሙትም ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ ነው።

አገራቱ ስደተኞችን ለመቀበል መስማማታቸውን ተከትሎም "ሕገ ወጥ ስደተኞች እና አደገኛ ወንጀለኞች ተይዘው ወደ አንጎላ፣ ናሚቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይላካሉ" ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሻባና መሐሙድ ተናግረዋል።

ድንበራችንን ለመቆጣጠር እና ለመጠበቅ የሚጠበቅብኝን ሁሉ አደርጋለሁ።

የዩኬ መንግሥት እንዳለው ከ3,000 በላይ የሚሆኑ የሦስቱ አፍሪካ አገራት ስደተኞች ወደ የአገራቸው ይመለሳሉ።

ስደተኞቻቸውን ከመቀበል ጋር በተያያዘ ከዩኬ ጋር ስምምነት ላይ ያልደረሱት ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ናይጄሪያ፣ ባንግላዲሽ፣ ሶማሊያ እና ጋቦን የቪዛ ክልከላ ሊጣልባቸው እንደሚችል ተገልጿል።