የዓለም ጤና ድርጅት በአማራ ክልል በጤና ባለሙያዎች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት በአስቸኳይ በገለልተኛ ወገን እንዲመረመር ጠየቀ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት በግጭት ውስጥ ባለው አማራ ክልል ውስጥ እየተፈፀመ ባለው የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋማት ጥቃት ላይ አስቸኳይ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀ።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በኤክስ ገፃቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ ግድያን፣ እስርን እና ድብደባን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች ለተለያዩ ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸውን የሚያሳዩ የሚረብሹ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ጠቅሰው ድርጊቱን አውግዘዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ከአስር ቀናት በፊት ዶ/ር ፀጋሁን ስሜ የተባለ ሐኪም በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች እንደተወሰደ እና ከዚያ በኋላ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን በጽሑፋቸው ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባሻገር በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ "ሆስፒታሎች ወድመዋል ፤ የእርዳታ ሠራተኞችም ሕይወታቸውን አጥተዋል" ብለዋል።

በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት መረጃዎችን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ቴድሮስ፤ በተፈጠሩት ክስተቶች ላይ አስቸኳይ እና ገለልተኛ ምርምራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የጤና ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች የጥቃት ኢላማ መሆን እንደማይገባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።

መቋጫ ባልተገኘለት የክልሉ ግጭት የጤና ተቋማትን እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በርካታ የሲቪል መሠረተ ልማቶች መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የጤና ባለሙያዎች በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የጥቃት ኢላማ መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።

ባለፈው ዓመት የባሕር ዳር ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ከሥራ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ዶ/ር አንዷለም በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ሥር የሚገኘው ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጉበት፣ የቆሽት ስብ እና የሃሞት ከረጢት ስፔሻሊት ሐኪም፣ ተመራማሪ እንዲሁም መምህር ነበሩ።

ኅዳር ወር ላይም በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና (ኦፕቶሜትሪ) ነርስ የነበረው አቶ ዳንኤል ነጋ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ የተጠየቀው 3.5 ሚሊዮን ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ቢከፈልም መገደሉን የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በግጭት ቀጠና ውስጥ ሆነው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና እና የትምህርት ባለሙያዎች ላይ ግድያ፣ እገታ፣ እስር እንዲሁም ድብደባ እንደሚደርስባቸው ይነገራል።

የፌደራል መንግሥት የክልሉን ጨምሮ ልዩ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሁለት ዓመት በላይ አስቆጥሯል።

ግጭቱ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተስፋፋ ሲሆን በበርካታ ዞኖች እና ወረዳዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው። ምንም እንኳን በግጭቱ ሁለቱም ወገኖች ኪሳራ እያጋጠማቸው እንደሆነ ቢነገርም ሰላማዊ የክልሉ ነዋሪዎች ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ የሰብዓዊ ድርጅቶች ሪፖርቶች አመልክተዋል።

በክልሉ ለሚፈፀሙ ግድያዎች እና የሰብዓዊ ጥሰቶች ሁለቱም ወገኖች የሚከሰሱ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ያስተባብላሉ።

በቅርቡ ቢቢሲ ባካሄደው ምርመራ ከሐምሌ 2015 እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ ከስምንት ዓመት እስከ 65 ዓመት ዕድሜ ያላቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው አመልክቷል።

ምንም እንኳ እውነተኛው ግጭት ነክ የወሲባዊ ጥቃት መጠን ሪፖርት ባለመደጉ እና ባለመርመሩ በትክክል ባይታወቅም፤ ቢቢቢ 4 በመቶ ከሆኑት የክልሉ 43 ጤና ጣቢያዎች እና የሕክምና ምንጮች በሰበሰበው መረጃ 2 ሺህ 697 ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል።

ለእነዚህ ጥቃቶች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተከሰሱ ሲሆን መንግሥት በዚህ ላይ ሰጠው ምላሽ የለም።

ከዚህ ቀደም ዩኤን ኦቻ በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት ምክንያት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ እና በርካታ ጉዳቶች ማጋጠማቸውን ገልጾ ያውቃል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በረድዔት ሠራተኞች ላይ ዕገታ፣ ዝርፊያ እና ጥቃትን ጨምሮ 93 ክስተቶችን በአውሮፓውያኑ 2023 መዝግቤያለሁ ብሎ ነበር።