የውጭ ሀገር ተጓዦች ማግኘት የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ መጠን በእጥፍ አደገ

የፎቶው ባለመብት, NBE/FB
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ የግል ተጓዞች እንዲያገኙ የሚፈቀድላቸውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ከአምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወደ 10 ሺህ ዶላር አሳደገ።
ባንኮች ለሚሰጧቸው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች የሚያስከፍሉት የገንዘብ መጠንም "ከአራት በመቶ እንዳይበልጥ" እንዲሁም "ጥቃቅን የአገልግሎት ወጪዎችን እንዲያስቀሩ" መወሰኑንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓቱ ላይ እነዚህን ማሻሻያዎች መውሰዱን ያስታወቀው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 12/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው። ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረጋቸው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት አስተዳደር ማሻሻያዎች ሦስት ናቸው።
የመጀመሪያው ለውጥ፤ አስመጪዎች መፈጸም የሚችሉት ቅድመ ክፍያ (አድቫንስ ፔይመንት) ላይ የተጣለውን ገደብ ከፍ ያደረገ ነው። ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ሸቀጦችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚፈልጉ አስመጪዎች መፈጸም የሚችሉት ቅድመ ክፍያ አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደነበር መግለጫው ያስረዳል።
ይህ ገደብ "የቆየ" እና "ለብዙ ዓመታት ለውጥ ሳይደረግበት የቆየ" አሠራር እንደሆነም ጠቅሷል። በአዲሱ አሠራር መሠረት አምስት ሺህ ዶላር የነበረው ገደብ በአስር እጥፍ አድጓል።
ባንኩ "ሸቀጦችን ከውጭ ለማስገባት ሊከፈል የሚችለውን የቅድመ ክፍያ መጠን ከ5 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወደ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከፍ ተደርጓል" ሲል አዲሱን ለውጥ አስተዋውቋል።
ማዕከላዊው ባንክ ይህንን ለውጥ ያደረገው "ከአቻ ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት" እንደሆነ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው ሁለተኛው ለውጥ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ማግኘት የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠንን የሚመለከት ነው። በዚህኛውም ማሻሻያ የተጣለውን ገደብ ከፍ አድርጓል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ለበዓል፣ ለትምህርት፣ ለሕክምና እና ሌሎች የግል ጉዳዮች የሚጓዙ ሰዎች ማግኘት የሚችሉት የውጭ ምንዛሬ መጠን አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነበር። ይህንን የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ወይም በክፍያ መፈጸሚያ ካርድ (debit card) ማግኘት ይችላሉ።
የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ተጓዦች ደግሞ እስከ አስር ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድረስ ማግኘት ተፈቅዶላቸዋል። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ተጓዦች በአካውንታቸው ካለው የውጭ ምንዛሬ 10 በመቶውን በክፍያ መፈጸሚያ ካርድ የማግኘት መብት ነበራቸው።

የፎቶው ባለመብት, NBE/FB
ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ማሻሻያ ለግል ተጓዦች የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ከአምስት ሺህ ዶላር ወደ 10 ሺህ ዶላር ከፍ መደረጉን አስታውቋል። ቀድሞውንም 10 ሺህ ዶላር ላይ የነበረው የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ተጓዦች በጥሬ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ ገደብ ለውጥ አልተደረገበትም።
ለንግድ ሥራ የሚጓዙ መንገደኞች ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብም ማሻሻያ ተደርጓል። በነባሩ አሠራር የንግድ ሥራ ተጓዦች የሚፈቀድላቸው የውጭ ምንዛሪ 10 ሺህ ዶላር ነበር። በአዲሱ ማሻሻያ ይህ ገደብ ወደ 15 ሺህ ዶላር አድጓል።
በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ግለሰቦች በአካውንታቸው ካለው የውጭ ምንዛሬ ውስጥ በክፍያ መፈጸሚያ ካርድ ማግኘት ይችሉ የነበረውን የገንዘብ መጠን ከ10 በመቶ ወደ 20 በመቶ አሳድጓል።
ባንኩ ለውጭ ተጓዦች በሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ገደብ ላይ ለውጥ ያደረገው፤ ለተጓዦቹ "ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል" እንደሆነ ገልጿል።
ሦስተኛው የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ "የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ክፍያዎችን ሥርዓት ማስያዝን" የሚመለከት እንደሆነ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። ብሔራዊ ባንክ፤ "ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት የሚያስከፍሏቸው ወጪዎች ተወዳዳሪነትን፣ ግልጸኝነትን እና ምቹነትን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆኑ" እንደሚያበረታታ ገልጿል።
ይህንን የሚያደርገውም በሀገሪቱ የሚሠራባቸው "ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ አስተዳደራዊ ክፍያዎችን ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣል ሲባል" እንደሆነም አስረድቷል።
በዚህም መሠረት ባንኮች "ከገቢ ንግድ፣ ከአገልግሎት ክፍያ ወይም ጥሬ ገንዘብ" ጋር በተያያዘ ለውጭ ምንዛሪ የሚያስከፍሏቸው "ማናቸውም አስተዳደራዊ ወጪዎች እና ክፍያዎች"፤ "ከአራት በመቶ እንዳይበልጡ" መወሰኑን አስታውቋል። ይህ ውሳኔ ከሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ግንቦት 18/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ገልጿል።
በተጨማሪም ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚያስከፍሏቸውን "የተለያዩ ተጨማሪ እና ጥቃቅን የአገልግሎት ወጪዎች እንዲያስቀሩ" መመሪያ ማስተላለፉን ይፋ አድርጓል። ባንኩ ይህንን መመሪያ ያስተላለፈው "ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ አስተዳደራዊ ወጪዎች ለተጠቃሚዎች ግልጽ እና ቀላል መሆናቸውን ለማረጋገጥ" እንደሆነ ጠቅሷል።
በተጨማሪም ይህንን ግልጽነት ለማረጋገጥ ሲባል ከሰኔ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ የሚያስከፍሏቸውን አስተዳደራዊ ክፍያዎች በድረ ገጹ "በመደበኝነት ለሕዝቡ ይፋ" እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲን እየተገበረ ያለው ብሔራዊ ባንክ፤ ይህ እርምጃ "አዎንታዊ ውጤቶችን ማስገኘቱን በዛሬው መግለጫ ላይ አስፍሯል።
በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች "የሸቀጦች ወጪ ንግድ በእጥፍ እንዲጨምር"፣ "የአገልግሎት እና የሐዋላ ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ" እንዲሁም "የግል እና የመንግሥት ካፒታል ፍሰት እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ" ማድረጋቸውን ገልጿል።
"ከዚህም የተነሳ የንግድ ባንኮች እና የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጓል" ብሏል - ብሔራዊ ባንክ። አሁን ይፋ የተደረጉት ማሻሻያዎችም "የሀገሪቱን የፋይናንስ ደንበኞች እና የግሉን ዘርፍ መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚያሟላ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለመፍጠር" ይረዳሉ ብሎ "በጽኑ" እንደሚያምን ገልጿል።















