የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢቢሲ ከዜጎች የሚሰበስበው ክፍያ ‘እውነታን መሰረት ያደረገ’ ሊሆን ይገባል አሉ

“ከፍተኛ የዋጋ ንረት ባለበት በዚህ ወቅት ቢቢሲ ከዜጎች የሚሰበስበው የቴሌቪዥን ግብር ተጨባጭ እውነታን መሰረት ያደረገ” ሊሆን ይገባል ሲሉ የዩናይትድ ኪንግድም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሽ ሱናክ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢቢሲ የሚሰበሰስበው ክፍያ ተገቢነት ሊኖረው ይገባልም ብለዋል።

እስካሁን ባይረጋገጥም በዋጋ ንረት ምክንያት ቢቢሲ ከቀጣዩ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጀምሮ ከዜጎች የሚሰበስበውን ክፍያ እንደሚጨምር ተሰምቷል።

ጠቅላይሚኒስትሩን ክፍያውን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ እንዳልተሰጠም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢቢሲ የሚሰበስበው ክፍያ ዘላቂ ይሆናል ወይ? ተብለው ሲጠየቁ “ነገሮች አስቸጋሪ በሆኑበት ሰዓት ሰዎች የቤተሰባቸውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በዋጋ ንረትና ክፍያው ለሁለት ዓመት ተቋርጦ በመቆየቱ ምክንያት ቢቢሲ በቴሌቪዥን ግብር አማካኝነት 500 ሚሊዮን ፓውንድ የመሰብሰብ ዕቅድ አለው። የቴሌቪዥን ግብር የቢቢሲ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ነው።

ዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሱናክ እንደማንኛውም ድርጅት ዜጎችን ማገልገል አለበት ያሉ ሲሆን ክፍያውን በተገቢ መንገድ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ የታቀደው የክፍያው መጠን ላይ ገደብ ለማስቀመጥ እንደሚፈልጉ አልተናገሩም።

ቢቢሲ ባለፈው ስምንት ታዋቂውን የምሽት የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል። ይህንንም ውሳኔ ብሄራዊ የጋዜጠኞች ማህበር በምርመራ ዜና ላይ ያጋጠመ ትልቅ ክሰተት ነው ብሎታል።

ይህ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እውቅ ጋዜጠኞቹን የሚያጣ ሲሆን የሚያካትተውን የ10 ደቂቃ የምርመራ ፕሮግራም ቀንሶ ስቱዲዮ ውስጥ ወደሚደረግ ክርክር ይቀይረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ወጪ ለመቀነስ ቢቢሲ ሌሎች ፕሮግራሞቹ ላይ ለውጥ ያደርጋል።

በርካታ የቲቪ ፕሮግራሞችን በመቀነስ ወደ ዲጂታል ጋዜጠኝነትና የቀጥታ ዘገባ ላይ ያተኩራል።

በዚህም ለውጥ ቢቢሲ እስከ 7.5 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚቆጥብ ይጠበቃል።

የቢቢሲ ቃል አቀባይ በአውሮፓውያኑ 2022 መንግስትና ቢቢሲ የ6 ዓመት የቴሌቪዥን ግብር ለመሰብሰብ መስማማታቸውን ጠቅሷል።