በኒው ዮርክ ሁለት ልጆችን ጨምሮ አራት ግለሰቦች በስለት ተወግተው ተገደሉ

በኒውዮርክ ኩዊንስ በተባለ ቦታ በደረሰ የስለት ጥቃት ሁለት ህጻናትን ጨምሮ አራት ሰዎች ሲገደሉ ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

እሑድ ጠዋት ሮክዌይ ከሚባል ሰፈር የስልክ ጥሪ የደረሰው ፖሊስ ተጎጂዎቹን በእሳት በተያያዘ ቤት ውስጥ ቤት ውስጥ አግኝቷቸዋል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ሁለት ፖሊሶች ላይ ጉዳት ቢያደርስም፣ ጉዳት ከደረሰባቸው ፖሊሶች አንዱ ተኩሶ አቁስሎታል።

ተጠርጣሪው ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም፣ በስፍራው እንደደረሰ ህይወቱ ማለፉ ታውቋል።

ፖሊስ በጃማይካ ሆስፒታል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የድረሱልን ጥሪ እንደደረሰው አረጋግጦ “ወጣቷ ስልክ ደዋይ የአጎቷ ልጅ ቤተሰቧን እየገደለ መሆኑን” ተናግራለች ብሏል።

ሁለት መኮንኖች የተባለው አድራሻ ሲደርሱ አንድ ግለሰብ ሻንጣ ይዞ ሲወጣ ይመለከታሉ።

ፖሊሶቹ ከግለሰቡ ጋር ለመነጋገር ሲሞክሩ ቢላዋ አውጥቶ አንዱን የፖሊስ መኮንን አንገቱን እና ደረቱ አካባቢ ሲወጋ፤ ሁለተኛውን ደግሞ ጭንቅላቱን ወግቶታል።

በዚህ ወቅት ከፖሊሶቹ አንዱ ሽጉጡን አውጥቶ ተጠርጣሪውን ተኩሶ ለመምታት ችሏል።

ተጨማሪ ፖሊሶች በቦታው ሲደርሱ አንዲት የ11 ዓመት ልጅን በቤቱ ፊት ለፊት አግኝተዋል። ልጅቷ ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።

የኒውዮርክ የእሳት አደጋ መከላከያ ባልደረቦች በቦታው ሲደርሱ ቤት ውስጥ የ12 ዓመት ወንድ ልጅ እና የ44 ዓመት ሴት አስከሬን አስከሬን አግኝተዋል። በተመሳሳይ ቤቱ ውስጥ በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ግለሰብም ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል።

የ61 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሴት በርካታ ቦታ በስለት ተወግተው የተገኙ ሲሆን ወደ ማውንት ሲናይ ሆስፒታል ተወሰደዋል።

ፖሊስ ሁሉም ተጎጂዎች በቢላዋ ተወግተው እንደሞቱ የሚያምን ሲሆን ከስፍራውም ቢላዋ አግኝቷል።

የኒውዮርክ ፖሊስ ተጠርጣሪው የ39 ዓመቱ ኮርተኒ ጎርደን መሆኑን ጠቅሶ፤ ግለሰቡ ከዚህ በፊት የቤት ውስጥ ጥቃት በመፈጸም አንድ ጊዜ በቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበር አስታውሷል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በኩዊንስ የሚገኙ ቤተሰቦቹን እየጎበኘ ነበር።

ፖሊስ ምርመራው እንደቀጠለ ገልጾ የስልክ ጥሪ ያደረገችው ግለሰብ በፖሊስ ጣቢያ ቃሏን እየሰጠች መሆኑንም ገልጿል።