በኪሲንጀር ትዕዛዝ ከ2 ሚሊዮን ቶን በላይ ቦምብ የዘነበባት ካምቦዲያ እንዴት ታስታውሳቸዋለች?

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ አሻራ አሳርፈዋል የሚባሉት የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የሄንሪ ኪሲንጀርን ህልፈት ተከትሎ ምዕራባውያን መሪዎች ለፖለቲከኛው ያላቸውን ክብር ሲገልጹ ተሰምተዋል።

የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽን ጨምሮ የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ምን ያህል በዲፕሎማሲ የተጠበቡ እንደነበሩ፣ የነጻውን የዓለም ሥርዓት ለማስጠበቅ ምን ያህል እንደለፉ እና ሌላም ሌላም ተናግረውላቸዋል።

አለፍ ብሎም የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆን ከዲፕሎማሲው ባለፈ ሰላም በማስፈን ታላቅ ሰው እንደነበሩ አወድሰዋቸዋል።

ነገር ግን በምዕራባውያን የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲዎች መሃንዲስ ተብለው የሚጠሩት እኚ ፖለቲከኛ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እልቂትም ምክንያት እንደሆኑ ታሪክ ተንታኞች ይናገራሉ።

በተለይም እሳቸው በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ የአሜሪካ ቦምብ በዘነበባት ካምቦዲያ ኪሲንጀር ያላቸው ገጽታ ሌላ ነው።

በቬትናም ጦርነት ወቅት ኪሲንጀር እና የወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን በድብቅ በካምቦዲያ ላይ የቦምብ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ይህም በምሥራቅ ካምቦዲያ ነበሩ የተባሉትን የቬትናም የኮሚዩኒስት ፓርቲ፣ ናሺናል ሊበሬሽን ፍሮንት የጦር አንጃ የሆነውን የቬት ኮንግ ኃይሎችን ለማጥፋት በሚል እንደሆነ አሜሪካ ተናግራለች።

አሜሪካ በካምቦዲያ ላይ ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ቦምብ አዝንባለች።

ይህንን በንጽጽር ስናየው በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የአጋር ኃይሎች በጃፓኖቹ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪን ጨምሮ የጣሉት ቦምብ ከ2 ሚሊዮን ቶን በላይ ነው።

አሜሪካ በካምቦዲያ ላይ ያዘነበችው ቦምብ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ከተጣለው ቦምብ ጋር እኩል ነው።

ኪሲንጀር የቦምብ ጥቃቱ ያነጣጠረው በካምቦዲያው ውስጥ በነበረው የቬትናም ጦር ላይ እንጂ በአገሪቱ ላይ እንዳልሆነ ይናገሩ ነበር።

የ76 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው ቮርንግ ሹት መንደራቸው በአሜሪካ ቦምብ እስኪወድም ድረስ ኪሲንጀር የሚባለውን ስም ሰምተውት አያውቁም ነበር። በቬትናም ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው ስቫይ ሪንግ ግዛት በአሜሪካ ቦምብ ሕይወት አልባ እንድትሆን ከተደረጉት መካከል ናት።

“በቦምብ ጥቃቱ ሕይወት የሚባል እንዳይኖር ነው የተደረገው። የቀርከሃ ዛፎች እንኳን አልቀሩም ሲረግፉ። ቀድመው ያመለጡ ተረፉ። እዚያው የነበሩት ተቀጠፉ።”

“በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። ስማቸውን ጠርቼ አልጨርሰውም። ሸሽተው የነበሩት ሰዎች ሲመለሱ ነው የቀበሯቸው” ይላሉ።

“በዓለማችን ታሪክ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በቦምብ ከተደበደቡ አገራት መካከል ካምቦዲያ ተወዳዳሪ እንደሌላት” በአውሮፓውያኑ 2006 በዬል ዩኒቨርስቲ የወጣው ‘ቦምብስ ኦቨር ካምቦዲያ’ ሪፖርት ያሳያል።

“ኪሲንጀር በአውሮፓውያኑ 1969 እና 1970 በካምቦዲያ የተካሄደውን 3875 የቦምብ ድብደባዎች እና እያንዳንዱን ጥቃቶች አጽድቀዋል። እንዲሁም እነዚህ ጥቃቶች በመገናኛ ብዙኃን እንዳይዘገቡም ዘዴዎችን ቀይሰዋል” ይላል በአውሮፓውያኑ 1973 የወጣው የፔንታገን ሪፖርት።

“መፈጸም ያለበት ትዕዛዝ ነው። ማንኛውንም የሚበር ነገር፣ የሚንቀሳቀስ ነገር ላይ [ጥቃት መፈጸም አለበት]። ገባህ?” ሲሉም ኪሲንጀር በአውሮፓውያኑ 1970 ለምክትላቸው ቀጠን ያለ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ከስልክ ንግግራቸው የተገኘ እና በምሥጢር ተይዞ የነበረ ሪፖርት አመልክቷል።

እሳቸው በቀጥታ በሰጡት ትዕዛዝ በተፈጸመሙት የቦምብ ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በውል ባይታወቅም ከ50 ሺህ እስከ 150 ሺህ ሕዝብ አልቋል የሚሉ መረጃዎች አሉ።

ከእነዚህ የቦምብ ጥቃቶች መካከል ከሚታወሱት አንዱ ኒክ ሉኦንግ በተባለችው መንደር በስህተት ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት 137 ካምቦዲያውያን ሲገደሉ፣ 268 ደግሞ ቆስለዋል።

ኒው ዮርክ ታይምስ አውጥቶት በነበረው ዘገባ እና በኋላም ‘ኪሊንግ ፊልድስ’ በሚለው ፊልም ላይ የተጠቀሰው ኬኦ ቻን የተባለ ግለሰብ በዚህ ጥቃት ባለቤቱ እና 10 ልጆቹ ተገድለውበታል።

“ቤተሰቦቼ በሙሉ ተገድለዋል” ሲልም እንባውን እያዘራ ከእንጨት በተሠራ አግዳሚ ወንበር ላይ ሲወድቅ ይታያል።

“ቤተሰቤ በሙሉ ሞቷል፣ ፎቶዬን አንሱ፣ ለአሜሪካውያን አሳዩትም” ሲልም ልቡ በሐዘን የተሰበረው ሰው ሲናገር ይሰማል።

በመንደሯ ውስጥ ያልፈነዳ ቦምብ አጠገብ ቆሞ የሚናገር ሌላ ግለሰብ ደግሞ “አሜሪካውያን ይህንን መቼ ነው የምትወስዱት?” ሲል ይጠይቃል።

የቦምብ ጥቃቶች ብቻ አይደሉም ካምቦዲያንን የፈጇቸው። በካምቦዲያ ገጠራማ አካባቢዎች ያልፈነዱ የአሜሪካ ቦምቦችም ለቀጣይ አስርት ዓመታት የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፈዋል፣ አካል አጉድለዋል።

የፕሬዝዳንት ኒክሰን እና የኪሲንጀር የቦምብ ዘመቻ ሌላኛው መዘዝ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ለታዩ አስከፊ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች መካከል አንዱ ለሆነው መንገድ መክፈቱ ይነገራል።

በፖል ፖት የተመራው የካምቦዲያው ኼምር ሩዥ ፓርቲ በአውሮፓውያኑ 1975 -1979 ባለው ጊዜ ለ1.7 ሚሊዮን ሕዝብ መጨፍጨፍ ምክንያት ሆኗል። ይህም አሐዝ ከሕዝቡ አንድ አራተኛው ያህል ነው።

ጽንፈኛ ኮሚዩኒስት የሚባለው ኼምር ሩዥ ፓርቲ ከአሜሪካ ቦምብ ጥቃት በፊት ብዙም ድጋፍ አልነበረውም። አሜሪካ በካምቦዲያ ላይ ቦምብ ስታዘንብም እንቅስቃሴው እየተጠናከረ እና የአባላቱም ቁጥር ጨመረ።

አሜሪካ በቦይንግ 52 ያደረሰቻቸውን ጥቃቶችም የኼመር ሩዥ ኃይሎች በተሳካ ሁኔታ ለፕሮፓጋንዳነት እንደተጠቁመበትም የሲአይኤ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር በአውሮፓውያኑ 1973 ሪፖርት አድርገዋል።

ኼምር ሩዥ ፓርቲ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በተፈጸሙ ጥሰቶች የተከሰሱት የመጀመሪያው ባለሥልጣን በተባበሩት መንግሥታት ለሚደገፈው ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2009 እንደተናገሩት “ሪቻርድ ኒክሰን እና ኪሲንጀር ለኼምር ሩዥ ወርቃማ ዕድሎችን ፈጥረዋል” ብለዋል።

ኪሲንጀር የካምቦዲያ ቦምብ ጥቃትን አስመከልክቶ የሚሰነዘርባቸውን ትችት ሲያጣጥሉ ቆይተው ነበር።

“የቦምብ ጥቃቱ በካምቦዲያ ላይ የሚፈጸም ሳይሆን በካምቦዲያ ውስጥ ያለውን የሰሜን ቬትናሞች ኃይል ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ” ሲሉም በአውሮፓውያኑ 1973 ተናግረው ነበር።

ሆኖም በ90 ዓመታቸው ቦምቦቹ የተጣሉት “ከቬትናም ድንበር በአምስት ማይል ርቀት በሚገኙ አካባቢዎች እና ሕዝብ ባልበዛባቸው አካባቢዎች ነው” ሲሉም ለማስተባበል ሞክረዋል።

አሜሪካ በካምቦዲያ ላይ ያደረሰችውን የቦምብ ጥቃት በአውሮፓውያኑ 1973 የዘገበችው አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ኤልዛቤት ቤከር ኪሲንጀር በሚሉት አትስማም።

“ከቦምብ ጥቃት ያመለጡ እና የሸሹ ተፈናቃዮችን አናገርን። ከዚያም የቦምብ ጥቃቶቹ ወደተፈጸሙባቸው ስፍራዎች ሄድን አካባቢዎቹ በጥቃቱ ወድመው ተመለከትን። የጎሽ አስከሬን ወድቆ፣ ቤቶች ተቃጥለው፣ የሩዝ እርሻዎች ወድመው ተመለከትን” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ጥፋቱን ስንመለከት ግራ ተጋባን። ለምንድን ነው ይህ ዘመናዊ ኃይል በእነዚህ የገጠር ስፍራዎች ላይ ይህንን ያህል የቦምብ ጥቃት የፈጸመው? በዚያን ጊዜ የነበሩት የካምቦዲያ አርሶ አደሮች የሞተር ተሽከርካሪዎችን እንኳን አያውቁም ነበር። ከሰማይ ላይ እሳት ለምንድን ነው የሚወርደው እያሉም ይጠይቁኝ ነበር?” ብላለች።

የ78 ዓመቱ ፔን ያይ በአሜሪካ ቦምቦች አባታቸውን እና አማቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች እንደተገደሉ ይናገራሉ።

“በጣም ፈርቼ መተኛት አልችልም ነበር። በየቦታው ሰዎች ይገደሉ ነበር። የሚገደሉ ሰዎችንም እናውቃቸው ነበር። ምንም ማድረግ አንችልም ነበር” ብለዋል።

ይህንን ሁሉ የፈጸሙት ኪሲንጀር የቬትናም ጦርነት እንዲያበቃ ላደረጉት ሚና በአውሮፓውያኑ 1973 የኖቤል ሽልማት ተቀብለዋል፤ እንዲሁም የአሜሪካ ከፍተኛ ሽልማት የሆነውን የፕሬዝዳንቱን የነጻነት ሜዳሊያም ተቀብለዋል።