በጋዛ ሰርጥ ውጊያ የጦር ወንጀል ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል አምነስቲ ገለጸ

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ወር በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል እና በፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል በተካሄደው ውጊያ የጦር ወንጀል ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል ገለጸ።

የእስራኤል ወታደሮች ያልተመጣጠነ የአየር ጥቃት በመፈጸም ፍልስጤማዊ ንጹኃንን መግደላቸውን አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

የፍልስጤሙ ‘ፓለስቲኒያን ኢዝላሚክ ጂሀድ’ ወይም ፒአይጄ የተኮሰው ሮኬት ንጹኃን ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያንን እንደገደለም አስታውቋል።

ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምርመራ እንዲያደርግ አምነስቲ ጠይቋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደተንቀሳቀሰ እና ንጹኃን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንደሞከረ ገልጿል።

ፒአይጄ የአምነስቲን ሪፖርት መቀበሉን ቃል አቀባያቸው ገልጸዋል።

በድንበር አካባቢ በተካሄደው ውጊያ 34 ፍልስጤማውያንና አንድ እስራኤላዊ ተገድለዋል።

ባለፈው ወር የተነሳውና ለአምስት ቀናት የቆየው ውጊያ የረገበው በእስራኤል የተኩስ አቁም አሸማጋይነት ነበር።

ውጊያው የተጀመረው የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በምሽት የአየር ጥቃት ፈጽመው ሦስት የፒአይጄ ወታደራዊ ክንፍ ከፍተኛ አመራሮችን እንዲሁም ዘመዶቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን ከገደሉ በኋላ ነው።

አምነስቲ እንዳለው የት እንደሚወድቁ ታቅዶ የተተኮሱ ቦምቦች መኖራቸው የሚጠቁመው ጥቃቱን የወጠኑትና ያዘዙት አካላት ንጹኃን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ሆነ ብለው ችላ ማለታቸውን ነው።

“እንዲህ ያለ ያልተመጣጠነ ጥቃት የጦር ወንጀል ነው” ብሏል አምነስቲ።

የእስራኤል መከላከያ እንዳለው፣ ይህንን ተከትሎ በተፈጠረው ውጊያ አየር ጥቃት የሰነዘረው ከ400 በላይ በሆኑ የፒአይጄ ወታደራዊ ዒላማዎች ነው።

የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ አመራር የሆኑ ሌሎች ሦስት ሰዎች መገደላቸውንም ገልጿል።

አመራሮቹ ከክስተቱ ከሳምንት በፊት ወደ እስራኤል ሮኬት እና ሞርታር እንደተኮሱም ከሷል።

አምነስቲ ዘጠኝ የአየር ጥቃቶችን የመረመረ ሲሆን፣ ሦስት የፒአይጄ ኮማንደሮች ቤታቸው ሳሉ የተገደሉበት ጥቃትም ተካቷል።

የእስራኤል ጦር እንዳለው፣ በጋዛ ሰርጥ ንጹኃን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሲል ጥቃቶችን ከማዘግየት ባሻገር እስከ መሰረዝም ደርሷል።

“ጥቃት የሰነዘርነው መሬት ላይ ያለውን ካጠናን በኋላ ነው። ንጹኃን እና ንብረታቸው እንደማይጎዳ ካረጋገጥንም በኋላ ነው” ብሏል።

አምነስቲ ባደረገው ምርመራ፣ በጋዛ ሰርጥ ጥልቅ የንብረት ውድመት ማስከተል እንደተስተዋለ ገልጿል።

“ሰዎችና ቤታቸው ላይ ጥቃት ማድረስ እንዴትም እንደ ልክ ነገር ሊገለጽ አይችልም” ብሏል።

እአአ በግንቦት 13 አራት ፎቅ ያለው ሕንጻ ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረና ይህ ሕንጻ ጃባሊያ የስደተኞች ማቆያ ካምፕ እንደነበር አምነስቲ ገልጿል። በዚህ ማቆያ 42 ሰዎች እንደሚኖሩም ተገልጿል።

የአምነስቲ የመካከለኛው ምሥራቅ ዳይሬክተር ሂባ ሞርያፍ “በምርመራችን ቦምቦች ቤቶችን ማፍረሳቸውን፣ አባቶች ትንንሽ ልጆቻቸውን ከፍርስራሽ ለማውጣት መገደዳቸውን አይተናል። አንድ ልጅ አልጋዋ ላይ አሻንጉሊቷን አቅፋ ሳለ የከፋ ጉዳት ደርሶባታል” ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ ግን ፒአይጄ በንጹኃን መኖሪያ አካባቢ እንደሚኖር ከሷል።

ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ንጹኃን እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠቱን ሲገልጽ፣ ፒአይጄ በበኩሉ ወደ እስራኤል 1,400 ሮኬቶች መተኮሱ ተገልጿል።

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጥቃቱን በመሸሽ መጠለያ ለመግባት መገደዳቸውም ተገልጿል።

ሾኬዳ በተባለ ቦታ በተተኮሰ ሮኬት በመኖሪያ ሕንጻ አካባቢ የነበሩ እስራኤላዊ ሴት እና ፍልስጤማዊ የጉልበት ሠራተኛ ተገድለዋል።

የአምነስቲ የመካከለኛው ምሥራቅ ዳይሬክተር እንዳሉት፣ በእስራኤል በኩል የተሰጡት ምላሾች ትክክለኛነት የሚጎላቸው ሲሆኑ የፍልስጤም ተዋጊዎችም ያልተመጣጠኑ ጥቃቶች መፈጸማቸው በጦር ወንጀልነት ሊመረመር ይገባል።

ተጎጂዎች ፍትሕ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።