ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ለእስራኤል ያላቸውን ጥልቅ አጋርነት በድጋሚ አረጋገጡ
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን አገራቸው አሜሪካ ለእስራኤል ያላት አጋርነት ጥብቅና ጥልቅ እንደሆነ አረጋገጡ።
ብሊንከን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለ2ኛ ጊዜ ቴል አቪቭ ለጉብኝት ከገቡ በኋላ እንዳሉት ‘’እስራኤል ራሷን የመከላከል እርምጃዋን አሜሪካ በጥብቅ ትደግፋለች።’’
ሐማስ በእስራኤል ላይ መብረቃዊ ጥቃት ከፈጸመ ወዲህ ብሊንከን ወደ ቴል አቪቭ አቅንተው ቤንያሚን ናታኒያሁን ሲያገኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ብሊንከን አገራቸው አሜሪካ ለእስራኤል ወታደራዊም ሆነ ማንኛውንም አስፈላጊ ድጋፍ ያለማወላወል እንደምትሰጥ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ከዘጠኝ ቀናት በፊት ሐማስ በወሰደው ያልተጠበቀ ወታደራዊ እርምጃ 1ሺህ 400 ሰዎች በእስራኤል ተገድለዋል።
የሐማስ ታጣቂዎች በጋዛ ሰርጥ በኩል ድንበር ተሻግረው ነበር በንጹሐንና በወታደሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙት።
እስራኤል ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ቀን ተሌት ጋዛን በቦምብ በመደብደብ ላይ ትገኛለች። ምናልባትም በቀጣይ ቀናት እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዝ ልታስገባ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።
ናታንያሁ ሐማስን ሳናጠፋ እንቅልፍ የለንም ሲሉ ዝተዋል።
ብሊንከን ከእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ጋር ፎቶ ከተነሱ በኋላ ወደርሳቸው ዞር ብለው ‘’መቼም ቢሆን የአሜሪካ ድጋፍ አይለያችሁም፤ መቼም።’’ ብለዋቸዋል።
ብሊንከን ከናታንያሁ ጋር ባደረጉት ውይይት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ ድጋፎችን ከሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ጋር በሚቀናጁበት ሁኔታ ተወያይተዋል።
ብሊንከን ከናታኒያሁ ጋር በሚወያዩበት ጊዜ የአደጋ ጊዜ ደውል በመሰማቱ ለአምስት ደቂቃ ያህል ውይይታቸውን አቋርጠው ከለላ ፍለጋ ምድር ቤት ተሸሽገው ነበር ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በጋዛ የሰብአዊ ሁኔታው እጅግ አስከፊ በሚባል ደረጃ መድረሱን ተከትሎ ብሊንከን፣ አንድም ይህ ሰብአዊ እርዳታ በሚቀጥልበት ሁኔታ ለመነጋገር ነው መካከለኛው ምሥራቅ አገራትን እየጎበኙ ያሉት።
ይህ ዘገባ እስኪጠናቀር ድረስ ከእስራኤል በሚሰነዘር ጥቃት ከ2ሺህ 700 ፍልስጤማዊያን በላይ ተገድለዋል። 9ሺህ 700 የሚሆኑት ቆስለዋል።
ሐማስ በወሰደው እርምጃ ከሞቱት ውስጥ 30 የሚሆኑት አሜሪካዊያን ናቸው።
ብሊንከን ከናታንያሁ ጋር ባደረጉት ውይይት በሐማስ የታገቱ 200 ዜጎች በሰላም ለማስፈታት በሚቻልበት ሁኔታ መክረዋል።
ሐማስ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሲሆን ከፈረንጆቹ 2007 ጀምሮ ጋዛን ያስተዳድራል። አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች የምዕራብ አገራት አሸባሪ ድርጅት በሚል በይነውታል።