ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁለት ሳምንት ያስቆጠረው የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ዋና ክስተቶች
ልክ የዛሬ ሁለት ሳምንት ሐማስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ከባድ ጥቃት የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው። አስካሁን በፍልስጥኤማውያን እና በእስራኤላውያን በኩል ሰላማዊ ሰዎች የግጭቱን ዋጋ እየከፈሉ ነው። ለአጭር ጊዜ በቆየው የሐማስ ጥቃት ከ1400 በላይ እስራኤላውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ተገድለዋል።
የቀጥታ ሽፋን
ከ7 የእስራኤል የግድያ ሙከራዎች አምልጦ አሁን ተገድሏል የተባለው የሐማስ ጦር አዛዥ ዴይፍ ማን ነው?
በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሺህ አለፈ
በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ5,000 ማለፉን የፍልስጤማ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 5,087የደረሰ ሲሆን፣ ከትላንትናው የሟቾች ቁጥር በ436ጨምሯል።
ከተገደሉት መካከል 2,055ሕጻናት፣ 1,119ሴቶች፣ 217አረጋውያን እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ከ15,273በላይ ሰዎች ተጎድተዋል።
እስሬኤል በጋዛ ስለምታደርገው ዘመቻ እስካሁን የምናውቀው
ባለፉት 24 ሰዓታት የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ወረራ መፈጸማቸው ተገልጿል። እስካሁን የምናውቃቸው ዋና ዋና ነጥቦች ቀጣዮቹ ናቸው።
እሑድ:
• እሑድ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ምዕራባዊ ክፍል ገብተው ታጋቾችን እንደፈለጉ፣ አካባቢውን ከአሸባሪዎችና መሣሪያ ለማጽዳት እንደሞከሩም እስራኤል አስታውቃለች።
• የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንዳለው ሚሳኤሎች በሐማስ ተተኩሰውባቸዋል። አንድ የእስራኤል ወታደር እንደተገደለና ሦስት ወታደሮች እንደቆሰሉ ተገልጿል።
• የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ እንዳለው ይህ የተከሰተው በደቡባዊ ጋዛ ካሀን ዩኒስ ነው። ይህ ከተማ ፍልስጤማውያን ለደኅንነታቸው ሲሉ ትተውት እንዲወጡ የተጠየቀ ነው። የእስራኤል ወታደሮች “በበርካታ ሜትሮች” ጥሰው እንደገቡም ተገልጿል።
• የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ እንዳለው “ከወራሪው ኃይል ጋር ተዋግቷል”። ሁለት ቡልዶዘሮችና ታንክ እንዳወደሙም ገልጸዋል። እስራኤላዊ ወታደሮች መኪናቸውን ትተው በእግራቸው ወደ ምሥራቃዊ አቅጣጫ ሸሽተዋል።
ሰኞ:
• የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሐግሪ እንዳሉት፣ እስራኤል በአንድ ምሽት ብዙ ወረር በጋዛ ፈጽማለች።
• ቃል አቀባዩ አክለውም “ምሽት ላይ ዘመቻው ሲካሄድ በታንክና በእግረኞች ነው። አሸባሪዎችን የገደሉት እነዚህ ዘመቻዎች ለቀጣይ የጦርነቱ ክፍል የተደረገ ዝግጅትን ኢላማ አድርገዋል። የታገቱ ሰዎችን ለማግኘትና የደኅንነት መረጃ ለማግኘትም ጠልቀን ወደ ውስጥ ገብተዋል” ብለዋል።
ይህ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ጋዛ ዘልቀው የገቡበት የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም። በግጭቱ የመጀመሪያው ሳምንት እስራኤል ወታደሮቿና ታንኮች ወደ ጋዛ ሰርጥ ሐማስን ለመዋጋትና ወደ እስራኤል የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን ለማግኘት እንደገቡ ገልጻለች።
እስራኤል ዜጎቿ ከግብጽ እና ጆርዳን እንዲወጡ አሳሰበች
የእስራኤል መንግሥት በግብጽ እና ጆርዳን ያሉ ዜጎቹ ከአገራቱ በአስቸኳይ እንዲወጡ ማዘዙ ተዘገበ።
ኤአፍፒ የዜና ወኪል የእስራኤል ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ዜጎች ወደ ሁለቱ አገራት እንዳይጓዙ እንዲሁም በአገራቱ ያሉ ከአገራቱ እንዲወጡ የጉዞ ማሳሰቢያ አውጥቷል ብሏል።
ባለፈው ሳምንት እንዲሁ በተመሳሳይ የእስራኤል መንግሥት ተመሳሳይ የጉዞ ማስጠንቀቂያ በቱርክ ለሚገኙ ዜጎቹ አስተላልፎ ነበር።
እርዳታ የጫኑ የመጀመሪያዎቹ ተሸከርካሪዎች ጋዛ ገቡ
የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከግብጽ ወደ ጋዛ ገብተዋል።
እስራኤል ምግብ፣ ውሃ እና መድሃኒት የጫኑ 20 ተሸከርካሪዎች ጋዛ እንዲገቡ ፈቅዳለች። ቴልአቪቭ ነዳጅ ግን ጋዛ እንዲገባ አልፈቀደችም።
የተባበሩት መንግሥታት እስራኤል ጋዛን ከበባ ውስጥ በመክተቷ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ይፈጠራል የሚል ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ነበር።
ተንቀሳቃሽ ምስሎች የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑት ተሸከርካሪዎች ከግብጽ የራፋን ደንበር መሻገሪያ አልፈው ወደ ጋዛ ሲገቡ አሳይተዋል።
ግጭቱ ከጀመረ ቢያንስ 22 ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለጸ
የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ድርጅት የእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ከጀመረ አንስቶ ቢያንስ 22 ጋዜጠኞች ተገድለዋል አለ።
የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው (ሲፒጄ) ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል 18ቱ ፍልስጤማውያን ናቸው ብሏል።
እንደ ሲፒጄ ከሆነ 15 ጋዜጠኞች ሕይወታቸውን ያጡት በእስራኤል የአየር ጥቃት ሲሆን ሁለት ጋዜጠኞች ደግሞ በደቡባዊ እስራኤል በሐማስ ጥቃት የተገደሉ ናቸው።
ቡድኑ በመግለጫው 8 ጋዜጠኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጸ ሲሆን ሦስት ጋዜጠኞች የደረሱበት አልታወቀም ወይም በእስር ላይ ናቸው ብሏል።
ሲፒጄ ጋዜጠኞች ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን እና በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እጅግ አስፈላጊ ስራን የሚሰሩ በመሆኑ በተዋጊዎች ዒላማ መደረግ የለባቸውም ብሏል።
ግብጽ በእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ዙሪያ ዓለም አቀፍ የሰላም መድረክ አዘጋጀች
ግብጽ ከ20 በላይ አገራት ተሳታፊ የሚሆኑበት ለእስራኤል እና ሐማስ ግጭት መፍትሄ የሚሻ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረክ አዘጋጀች።
የአገራት መሪዎች እና ተወካዮች ዛሬ በካይሮ በሚጀመረው እና በመከላከለኛው ምስራቅ የሰላም ሁኔታ በሚመክረው ጉባኤ ለመገኘት ግብጽ እየገቡ ነው።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በዚህ ጉባኤ ላይ የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ፣ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ሞሐሙድ አባስ፣ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጄምስ ክሌቨርሊ እና የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒ ጉተሬዝ ከተሳታፊዎች መካከል እንደሚገኙበት ጽፏል።
ከላይ ከተጠቀሱት ባለስልጣንት በተጨማሪ የበርካታ የአረብ አገራት መሪዎች እና ተወካዮች በካይሮ እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ በዚህ ስብሰባ ላይ ከእስራኤል፣ ከሐምስ፣ ከአሜሪካ እና ከኢራን ተወካዮች ስለመገኘታቸው እስካሁን ማረጋገጫ አልተሰጠም።
የግብጽ ባለስልጣናት የዚህ ውይይት መድረክ ዋና ግብ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ማስቻል ነው ይላሉ። ካይሮ ይህን ተበል እንጂ የግጭቱ ዋና ተሳታፊዎች እና እንደ ኢራን እና አሜሪካ ያሉ ቁልፍ አገራት ተሳታፊ ባልሆኑበት መድረክ ይህን የማሳካት ዕድሉ ጠባብ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ትናንት ዓርብ ፍልስጤምን የሚደግፉ ሰልፎች በተለያዩ አገራት ተካሄዱ
ትናንት ዓርብ በበርካታ አረብ አገራት እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ያለችውን ድብደባ እንድታቆም የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደው ውለዋል።
ፍልስጤማውያንን የሚደግፉ ሰልፎ በኢንዶኔዢያ፣ ማሌዢያ እና ሕንድ ጭምር ተካሂደዋል።
ለፍልስጤም አጋርነት ለመግለጽ አደባባይ ከተወጣባቸው አገራት መካከል ቱኒዚያ፣ አማን፣ ጆርዳን እና ሞሮኮ ተጠቃሽ ናቸው።
ሐማስ ከሁለት ሳምንታት በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ቴል አቪቭ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ4ሺህ ያላነሱ ሰላማዊ ሰዎች በጋዛ መገደላቸውን በጋዛ ያሉ የጤና ኃላፊዎች ገልጸዋል።
የሳዑዲ ልዑል ሐማስን፣ እስራኤልን እና ምዕራባውያንን ተቹ
የሳዑዲው ልዑል ቱርኪ አል-ፋይሰል ሐማስን እና እስራኤልን ንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ተችተዋል።
“ማንም ጀግና የለም። ተጎጂዎች ናቸው ሁሉም” ብለዋል።
እምብዛም አስተያየት ከማይሰማበት የአረቡ ዓለም በተሰጠው በዚህ አስተያየት ምዕራበውያንም ተወቅሰዋል።
ልዑሉ በአሜሪካ ራይስ ዩኒቨርስቲ ነው ንግግሩን ያደረጉት።
የቀድሞ ዲፕሎማትና የስለላ ኃላፊ የነበሩት ልዑሉ ሐማስ ንጹኃንን እንዳገተና እስልምና ግን ማንንም ሰው አለመጉዳትን እንደሚያስተምር ተናግረዋል።
እስራኤልም ንጹህ ፍልስጤማውያንን በጋዛ በቦምብ መደብደቧን እንዲሁም ፍልስጤማውያን ሕጻናት፣ ሴቶችና ወንዶችን በዌስት ባንክ ማሰሯን ኮንነዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የሐማስን ጥቃት “መነሻ የሌለው ትንኮሳ” ብለው መዘገባቸውን ልዑሉ ተችተዋል።
“ከዚህ በላይ ምን መነሻ ያስፈልጋል? እስራኤል ፍልስጤማውያን ላይ ለሦስት አሥርታት የፈጸመችው መነሻ ነው” ብለዋል።
በይዞታው ውስጥ ያሉ ሰዎች ለነጻነታቸው መታገል መብታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የምዕራባውያንን ፖለቲካ ልዑሉ የተቹ ሲሆን፣ “እስራኤላውያን በፍልስጤማውያን ሲገደሉ ታለቅሳላችሁ። ሆኖም ግን እስራኤላውያን ፍልስጤማውያንን ሲገድሉ ለማዘን አትፈቅዱም” ብለዋል።
መውጫ መግቢያው ለተዘጋባቸው የጋዛ ነዋሪዎች ለመድረስ መከፈቱ የሚጠበቀው በር
በሐማስ ታግተው የነበሩ አሜሪካዊ እናትና ልጅ ተለቀቁ
በሐማስ ጋዛ ውስጥ ታግተው የነበሩ እናትና ልጅ ተለቀቁ። ጁዲት ራናን እና ናታሊ ይባላሉ እናትና ልጅ።
እስራኤል ላይ ጥቃት በተፈጸመ ወቅት ነበር የታገቱት።
የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አል-ቃሲም ብርጌድስ ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኞች ነጻ የወጡትን ታጋቾች ሲያግዙ ይታያል።
በእየሩሳሌም ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ እናትና ልጅ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በስልክ ሲያወሩ የሚያሳይ ምሥል ለቋል።
ኤምባሲው “ፕሬዝዳንቱ ከሐማስ ከተለቀቁ ሁለት ታጋቾች ጋር ተነጋግረዋል። ደኅና ስለሆኑ ደስ ብሎናል። ሌሎች ታጋቾችንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመቀላቀል የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንቀጥላለን” ብሏል ኤምባሲው።
ዋይት ሀውስ በለቀቀው መግለጫ ባይደን ታጋቾቹ ከቤተሰባቸው ጋር በቅርቡ እንደሚቀላቁ ገልጸው በዚህም “እጅግ ተደስቻለሁ” ማለታቸውን አስፍሯል።
“የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ከጀመረ ሁለት ሳምንት ሆነው”
ልክ የዛሬ ሁለት ሳምንት ሐማስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ከባድ ጥቃት የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።
አስካሁን በፍልስጥኤማውያን እና በእስራኤላውያን በኩል ሰላማዊ ሰዎች የግጭቱን ዋጋ እየከፈሉ ነው።
ለአጭር ጊዜ በቆየው የሐማስ ጥቃት ከ1400 በላይ እስራኤላውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ተገድለዋል።
ከዚያ በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ እየካሄደችው ባለው የአጸፋ የአየር ጥቃት ከ4000 በላይ ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል።
የአየር ጥቃቱም እንደቀጠለ ነው፤ የእግረኛ ሠራዊት ወረራ በእስራኤል ሊካሄድ እንደሚችል እየተጠበቀ ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተከሰተው በአጭሩ:
• መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ቅዳሜ ማለዳ የሐማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ዘልቀው በመግባት ድንገተኛ ጥቃት ፈጸሙ።
• የሐማስ ታቂዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ግዛት መተኮሳቸውን አስታወቁ።
• በጥቃቱ ከ1400 በላይ ከእስራኤል በኩል ሲገደሉ፣ ከዚህ ቁጥር የሚልቁት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
• ከ200 የሚበልጡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሐማስ ታጣቂዎች ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
• ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል በሐማስ ቁጥጥር ስር ባለችው ጋዛ ላይ ቀን ከሌት ያልተቋረጠ የአየር ድብደባ እያካሄደች ነው።
• ሐማስም ወደ እስራኤል አልፎ አልፎ ሮኬቶችን ማስወንጨፉን ቀጥሏል።
• እስራኤል በጋዛ ላይ ያለማቋረጥ እየፈጸመችው ባለው የአየር ድብደባ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ4000 በላይ ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ፣ ከ13 ሺህ የሚበልጡ ደግሞ ቆስለዋል።
• እስራኤል ሰውም ሆነ ምንም ነገር ወደ ጋዛ እንዳይገባ ሙሉ ከበባ ያወጀች ሲሆን፣ ምግብ፣ ውሃ እና መድኃኒት በግዛቲቱ ውስጥ እየተሟጠጠ ነው።
• እስራኤል በጋዛ ላይ የእግረኛ ሠራዊት ወረራ ለማካሄድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን እና የጦር መሳያዎቿን አስጠግታ አመቺ የምትለውን ጊዜ እየተበቀች ነው።
• እስራኤል በጋዛ ላይ ለምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ በሰሜናዊ ጋዛ የሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ ያዘዘች ሲሆን፣ አስካሁን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ተፈናቅለዋል።
• ከሁለት ሚሊዮን በላይ ባላት ጋዛ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች በአየር ድብደባ ስር ሆነው፣ መሠረታዊ አቅርቦቶች ተቋርጦባቸው በሚገኙበት ሁኔታ አደገኛ ሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል የረድኤት ድርጅቶች እያሳሰቡ ነው።
• የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የሌሎች አገራት መሪዎች በእስራኤል ላይ ባሳደሩት ግፊት፣ ከግብፅ በኩል ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ፈቅዳ አቅርቦቱ የሚጀመርበት ጊዜ እየተጠበቀ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር በግብፅ
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ አርብ ከሰዓት በኋላ ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ጋር ተገናኝተው ውይይት አደረጉ።
ሐሙስ ከእስራኤል ጀምረው በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ሱናክ፣ አርብ ጠዋት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ከኳታሩ አሚር ጋር በተመሳሳይ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ዩናይትድ ኪምግደም “ቅድሚያ” በመስጠት ትኩረት የምታደርገው የራፋህ የድንበር መተላለፊያ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ክፍት በመሆንበት ሁኔታ ላይ ነው።
ሐማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቀ
ሐማስ ከእስራኤል አግቶ ከወሰዳቸው ከሁለት መቶ በላይ ታጋቾች መካከል የተወሰኑ እስረኞችን በመልቀቅ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ንግግር እየተካሄደ መሆኑ ተዘገበ።
ቢቢሲ ከምንጮቹ እንደተነገረው በሐማስ ታግተዋል ተብለው ከሚታመኑት 203 ሰዎች መካከል አብዛኞቹን ለማስለቀቅ የሚደረገው ንግግር መቀጠሉን እና ሐማስ በምትኩ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቁ ተገልጿል።
ነገር ግን እስራኤል እስካሁን በቀረበው ሃሳብ አለመስማማቷ ተነግሯል።
በዓለም አቀፍ አሸማጋዮች አማካይነት እየተደረገ ያለው ድርድር ትኩረቱን ጋዛ ውስጥ ተይዘው በሚገኙት በታጋቾች ላይ አድርጎ እየተካሄደ ይገኛል። የዚህን ንግግር ዝርዝር በተመለከተ ከሁለቱም ወገን በይፋ የተሰጠ ማረጋገጫ የለም።
በእገታ ስር ያሉት ሁሉም ሰዎች ሐማስ እጅ ያሉ አለመሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ የተወሰኑት በሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ናቸው ተብሏል።
ጋዛ ውስጥ በእገታ ላይ ያሉት ሰዎች ሁኔታ የእስራኤል ጦር አዛዦች ወደ ጋዛ ዘልቆ በመግባት ሊያደርጉት ያሰቡትን ዘመቻ ካወሳሰቡባቸው ምክንያቶች አንዱ ነው።
ታጋቾቹን ከወታደራዊ እርምጃ ይልቅ በድርድር እንዲለቀቁ ማድረግ በሕይወት ወደ አገራቸው የመመለስ ዕድላቸውን ከፍ ያደርገዋል።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ እስራኤል ውስጥ ዘልቆ በመግባት በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ከ1400 በላይ ሰዎችን መግደሉ የተዘገበ ሲሆን፣ 200 የሚሆኑ ሰዎችንም አግቶ ወደ ጋዛ ሰርጥ መውሰዱን የእስራኤል ጦር ሠራዊት አስታውቋል።
ሠራዊቱ ባወጣው አዲስ መግለጫ ላይ የታጋቾቹን ዝርዝር ሁኔታ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሠረት ከታገቱት 203 ሰዎች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ናቸው።
ከአስር አስከ ሃያ የሚደርሱት ደግሞ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ሲሆን፣ ከታጋቾቹ መካከል አብዛኞቹ በሕይወት መኖራቸውን የገለጸው የእስራኤል ሠራዊት፣ የሟቾች አስከሬን እንደ ታጋች ወደ ጋዛ መወሰዳቸውንም ጠቅሷል።
በጋዛ በርካታ ክርስቲያኖችን ያስጠለለው የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በአየር ጥቃት ተመታ
በጋዛ የሚገኝ እና በርካታ ክርስቲያኖችን አስጠልሎ የነበረው የግሪክ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በአየር ጥቃት ተመታ።
ጥቃቱን በተመለከተ ሐማስ ባወጣው መግለጫ የቅዱስ ፖርፊየስ ቤተ-ክርስቲያን ያጋጠመው ከፍተኛ ፍንዳታ በሕንጻው ላይ ከባድ ጉዳት ማስከተሉን እና በርካቶችን መጉዳቱን አስታውቋል።
ሐማስ ጥቃቱ የተፈጸመው በእስራኤል ጦር ነው ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ግን ቤተ-ክርስቲያኑን ዒላማ አለማድረጉን ይገልጻል።
ጦሩ ለፈንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደገለጸው የተዋጊ ጄቶቹ ጥቃት የታጣቂዎችን የሮኬት እና ሞርታ ጥቃት ትዕዛዝ መስጫ ማዕከለን መምታታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ያለችው ቤተ-ክርስቲያን ግድግዳ ወድሟል ብሏል።
ቢቢሲ በቤተ-ክርስቲያኗ እና በሰው ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ማወቅ ባይችልም ኤኤፍፒ ያጋራቸው ምስሎች በእምነት ቤቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
የእየሩሳሌም የኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ጥቃቱን አጥብቀው በማውገዝ ባወጡት መግለጫ ለፍንዳታው ምክንያት የሆነው የእስራኤል የአየር ጥቃት ነው ብለዋል።
የሠላማዊ ዜጎች መጠለያ በሆኑት በአብያተ ክርስቲያናት እና በተቋሞቻቸው ላይ የሚፈጸመው ጥቃት “ቸል ሊባል የማይችል የጦር ወንጀል ነው” ብለዋል በመግለጫቸው።
ቅዱስ ፖርፊየስ ቤተ-ክርስትያን ከ12ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተመሠረተ ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ በከባድ ፍንዳታ ተመትቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉበት አል አህሊ ሆስፒታል በቅርብ ርቀት ይገኛል።
የአሜሪካ ተዋጊ መርከብ ከየመን ወደ እስራኤል የተተኮሰ ሚሳኤል አከሸፈ
የአሜሪካ ተዋጊ መርከብ ከየመን ነው የተተኮሰው የተባለ ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ማክሸፉን የአሜሪካ ባለሥልጣኖች አሳወቁ።
የተተኮሰው ከኢራን ጋር ትስስር ባለው የሁቲ ንቅናቄ ነው ተብሏል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሚሳኤሎቹ የተተኮሱት “እስራኤል ዒላማ በማድረግ ነበር” ብለዋል።
ሚሳኤሉ የከሸፈው የአሜሪካ መሣሪያ ዩኤስኤስ ካርኒ የተባለው ሚሳኤል አክሻፊ በቀይ ባሕር ሰሜናዊ ክፍል ነበር እየተንቀሳቀሰ ያለው።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የአሜረካ ወታደሮች በኢራቅ እና ሶርያ ጥቃት እንደደረሰባቸው ፔንታጎን ገልጿል።
በኢራን የሚደገፉ ቡድኖችን አሜሪካ በዐይነ ቁራኛ እየተከታተለች ትገኛለች።
የፔንታጎን ብርጋዴር ጀነራል ፓትሪክ ራይደር እንዳሉት፣ ሦስት ሚሳኤሎች እና ብዙ ድሮኖች ከየመን ተተኩሰው ከሽፈዋል።
በክስተቱ የተፈጠረ አደጋ ስለመኖሩ ሪፖርት አልተደረገም።
በጋዛ የሆስፒታል ፍንዳታ ስፍራ የተፈጠረው ድንጋጤ እና ግራ መጋባት
ሪሺ ሱናክ ወደ ግብጽ ሊያመሩ ነው
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ እስራኤል እና ጋዛን በመተለከተ በቀጠናው ካሉ አገራት ጋር ውይይት ለማድረግ ወደ ግብጽ ሊያመሩ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ሪሺ ሱናክ በጉብኝታቸው ትኩረት የሚያደርጉት በቀጠናው ውጥረት እንዳይባባስ ማድረግ እና የተጨማሪ ሰላማዊ ሰዎች ሞትን ማስቆም ነው ብሏል።
ትናንት ሐሙስ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን ጋር የተገናኙ ሲሆን ሳዑዲ በመካከለኛው ምሥራቅ መረጋጋት እንዲፈጠር ድጋፏን እንድታደርግ ጠይቀዋል።
ሱናክ ቀደም ሲል ወደ እየሩሳሌም በተጓዙ ወቅት አገራቸው ከእስራኤል ጎን እንደምትቆም አስታውቀው ነበር።
በጋዛው አል-አህሊ ሆስፒታል ላይ ስለደረሰው ፍንዳታ ማስረጃዎች ምን ይጠቁማሉ?