የሁለት ቅዱስ መስጊዶችን ማስፋፊያ ለሠራበት ክፍያ አልቀበልም ያለው የኪነ ሕንጻ ባለሙያ

በመካ የሚገኘው አል ሐራም መስጊድ
የምስሉ መግለጫ, በንጉሥ ፋህድ ዘመን የተሰራው የአል ሐራም መስጊድ ማስፋፊያ በ14 ክፍለ ዘመን ውስጥ የተደረገ ሰፊ ማስፋፊያ እንደሆነ ተገልጿል።

መሐመድ ከማል እስማኤል በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኙት ሁለት ቅዱስ መስጊዶች መስፋፋት ጀርባ ያለ የሥነ ሕንጻ ባለሙያ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1908 የተወለደው ግብፃዊው የኪነ ሕንጻ ባለሙያ (አርክቴክት) በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን አል ሐራም መስጊድ [በመካ የሚገኝ ትልቅ መስጊድ] እና በመዲና የሚገኘውን አን ናባዊ [የነብዩ መስጊድ] የማስፋፊያ ሥራን እንዲቆጣጠር የተመረጠው በቀድሞው የአገሪቱ ንጉሥ ፋህድ ነበር።

የአል ሐራም መስጊድ ማስፋፊያ በ14 ክፍለ ዘመን [1 ሺህ 400 ዓመት] ውስጥ የተካሄደው ትልቁ ማስፋፊያ ሥራ እንደነበር በወቅቱ ተገልጿል።

እስማኤል እነዚህን ማስፋፊያዎች ለሠራበት ክፍያ አልቀበልም ብሏል።

ንጉስ ፋህድ እና የቢን ላደን ኩባንያ ከፍያውን እንዲቀበል ጥረት ቢያደርጉም እስማኤል ከአቋሙ ፍንክች አላለም።

“በዓለማችን ልዩ ለሆኑት ቅዱስ ቦታዎች ለሠራሁት ሥራ ገንዘብ የምቀበለው ለምንድን ነው? በኋላ ላይ በፍርድ ቀን ከአላህ ፊት እንዴት ነው የምቀርበው?” ነበር ያለው እስማኤል ጥያቄው ሲቀርብለት።

የትምህርት እና የትዳር ሕይወት

እስማኤል ከግብፅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች እንዲሁም የሮያል የምህንድስና ትምህርት ቤትን ከተቀላቀሉት በዕድሜ ትንሹ ተማሪ ነበር።

ከዚያም በእስላማዊ ኪነ ሕንጻዎች የተሻለ ትምህርት ለማግኘት ወደ አውሮፓ ተልኳል።

በ44 ዓመቱ ትዳር መሥርቶ የነበረ ሲሆን፣ አንድ ወንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ባለቤቱን በሞት አጥቷል።

ከዚያ በኋላ እስማኤል በ100 ዓመቱ ሕይወቱ እስከሚያልፍ ድረስ ከሚዲያዎች በመራቅ እና ለሃይማኖቱ በመገዛት ፈጣሪውን እያመለከ አሳልፏል።

መስጊድ
የምስሉ መግለጫ, አርክቴክት እስማኤል ሙሉ ሕይወቱን ለእምነቱ ሰጥቷል።

ነጭ እምነ በረድ

በሳዑዲ አረቢያ ያለውን ሙቀት ለመቋቋም የአል ሐራም መስጊድ ወለሎች በእምነ በረድ እንዲሰሩ ሀሳብ ያነጨው እስማኤል ነበር።

እምብዛም የማይገኘውና ከግሪክ የሚመጣው ነጩ እምነ በረድ ባልተለመደ መልኩ በሚሰጠው ብርሃን፣ በነጭ ቀለሙ እና ሞቃታማ ቤቶችን በማቀዝቀዝ ይታወቃል።

ንጉሥ ፋህድ በኋላ ላይ ለአን ናባዊ መስጊድ ማስፋፊያም ተመሳሳይ ነጭ እምነ በረድ እንዲጠቀም ነግረውታል።

በመካ የሚገኘው ታላቁ መስጊድ አል ሐራም እስላማዊ ቅዱስ ሥፍራ ነው።

ይህ ቅዱስ ሥፍራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሐጂ እና ኡምራ ተጓዦችን ማስተናገድ እንዲችል በታሪኩ ብዙ ማስፋፊያዎች ተደርገውለታል።

በንጉሥ ፋህድ ዘመን ማስፋፊያ ከተደረገለት በኋላ መስጊዱ 356 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በአዘቦት ቀን እስከ 820 ሺህ አማኞችን ማስተናገድ ይችላል።

በረመዳን እና በሒጂ ጉዞ ወቅት ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አማኞችን የመያዝ አቅም አለው።