አንዲት ቤተክርስቲያንን ጠብቀው ያቆዩት ኢትዮጵያዊ ሼኽ

አንዲት ቤተክርስቲያንን ጠብቀው ያቆዩት ኢትዮጵያዊ ሼኽ ሃሰን ይመር

የፎቶው ባለመብት, Keber Getachew

የምስሉ መግለጫ, ሼኽ ሃሰን ይመር [ከቀኝ በኩል የመጀመሪያው]
    • ፀሐፊ, በፍሬህይወት ካሳ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ አማርኛ

የእስልምና እምነት ተከታይ ናቸው። ይሰግዳሉ፣ ይጾማሉ፣ መስጊድ ይሄዳሉ።

አረፋን፣ ኢድ አልፈጥርን፣ መውሊድን እምነቱ በሚፈቅደው መልኩ ያከብራሉ።

ሰላምታ ሲሰጧቸው " አልሃምዱሊላሂ" [አላህ የተመሰገነ ይሁን] ነው የሚሉት። ከ'ወላሂ!' ሌላ መሃላ አያውቁም።

እግራቸው ግን ከአንዲት ቤተ ክርስትያን ደጅ አይጠፋም። ይህ እድሜ ዘመናቸውን ሳይታክቱ ያደረጉት ነው።

እርጅና ተጫጭኗቸው ጉልበታቸው ቢደክምም በምርኩዛቸው ታግዘው ቤተ ክርስትያኗ ወደ ምትገኝበት ተራራ ብቅ ሳይሉ አይውሉም።

ቤታቸው ጎራ ብሎ ለጠየቃቸውም ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ የሚጠይቁት ስለ ቤተክርስቲያኗ ደህንነት መሆኑን የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።

ሼኽ ሃሰን ይመር ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ ነው።

ብዙዎች ወሎን የተለያየ እምነት ተከታዮች ተሰናስለው የሚኖሩበት፣ የመዋደድና የመከባበር ምሳሌ ያደርጉታል።

የተለያየ እምነት ተከታይ የሆኑ ጥንዶች ልጅ አፍርተው በአንድ ጎጆ ሥር ይኖራሉ። ሙስሊሙ በጥምቀት ታቦት ይሸኛል። ክርስቲያኑ በኢድ አልፈጥር መስገጃ ያሰናዳል።

"ስሙ ኃይለማሪያም አባቱ መሃመድ

እንዴት ያስደስታል ወሎ ላይ መወለድ" በሚልም ይቀኙለታል።

መንፈሳዊ መዝሙርን የሚሰማ ሰው አይቶ የእምነቱ ተከታይ ነው ብሎ መደምደም ያስቸግራል። መንዙማ የሚሰማን ማንኛውንም ሰው ሙስሊም ነው ብሎ መፈረጅም ሊያሳስት ይችላል። አንዱ ያንዱን ያከብራል፤ አንዱ የሌላውን ይወዳልና።

ገንዘብ አዋጥተው ሙስሊሞች ቤተክርስቲያን ያሰራሉ፤ ክርስቲያኖችም መስጊድ ይገነባሉ።

ወሎ በርካታ አንቱ የተባሉ የእስልምና እምነት አሊሞች (መሪዎች) የወጡበትም ነው።

የኢትዮጵያ ኡለማዎች ምክር ቤት ፕሬዚደንት ተቀዳሚ ሃጂ ሙፍቲ ኡመር ኢድሪስን፣ በትንቢታቸው የሚታወቁትን ሼኽ ሁሴን ጅብሪልን፣ መንዙመኛው ሼኽ መሃመድ አወል ሃምዛን መጥቀስ በቂ ነው።

ሼኽ ሃሰን የቤተክርስትያኗ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሲሆን ቤታቸው ጠላ አስጠምቀው፤ ድፎ ዳቦ አስጋግረው ይወስዳሉ።

የእርሳቸው ዝና በአካባቢው ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም የናኘ ነው።

ለክብረ በዓሉ አገር አቆራርጠው ወደ አካባቢው የሚጎርፉ የእምነቱ ተከታዮችም እርሳቸውን ሳይዘይሩ [ሠላም ሳይሉ] አይመለሱም።

ሼኽ ሃሰን የግል እምነታቸው፤ ጠብቀው ላቆይዋት ቤተ ክርስትያን ከሚከፍሉት ዋጋ፣ እንክብካቤና ጥበቃ ጋር አይጋጭባቸውም።

"ሼኽ ሃሰን 'ደንጎራ' ተይዞባቸው ነበር"

በእርግጥ ሼኽ ሃሰን ከአንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደሚያውቅ ልጆቻቸውና የሚያውቋቸው ተናግረዋል።

ሼኽ ሃሰን ያለ እምነታቸው 'የአካባቢውን ነዋሪ ክርስትያን ሊያደርጉት ነው' በሚልም ከአንድም ሁለት ሦስቴ በጥይት እንደተሳቱ የእርሳቸውን ታሪክ የከተበው ከበር ይናገራል።

ከበር ጌታቸው ሼኽ ሃሰንን በቅርበት ያውቃቸዋል። ስለ ቤተክርስቲያኗ መጽሃፍ ጽፏል። የእርሳቸው ታሪክ የተካተተበት "ወረኢሉ ማህደረ ኢትዮጵያ" የሚል መጽሃፍም አሳትሟል።

እርሱ እንደሚለው ሼኽ ሃሰን በወቅቱ ከእድርና እቁብ ተገልለው ነበር።

'ደንጎራም' ተይዞባቸው ነበር [ደንጎራ በአገሬው ቋንቋ የቀብር ጉድጓድ መቆፈሪያ ማለት ነው]። ከእድር እንደመውጣት፤ ቀባሪ እንደማጣት ይቆጠራል።

ቤተሰባቸውም ቢሆኑ የኋላ ኋላ ሃሳባቸውን እየተረዷቸው መጡ እንጂ ትንሽ ቅሬታ እንደነበራቸው ልጃቸው መሃመድ ሃሰን ይናገራል።

ይህ ሁሉ ግን ሼኽ ሃሰንን ከመልካም ተግባራቸው አልገታቸውም።

የሼኽ ሃሰን የመጨረሻ ልጅ የሆነው የ35 ዓመቱ መሃመድ፤ "አባታችን አንዳንድ ተቃውሞ ቢገጥመውም ሙስሊሙ ሰውዬ እንደ ክርስቲያን ወረኢሉና ደሴ እየተመላለሰ ቤተ ክርስቲያኗን አሰርቷል" ይላል።

የሼኽ ሃሰንን ታሪክ የሰማነው ቀደም ብለን ቢሆንም አድራሻቸውን ስናፈላልግ ነበር ሕልፈታቸውን የሰማነው። እኝህ አባት በ96 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው ባለፈው ዓመት ነበር።

ልጃቸው መሃመድ እንደሚለው ሼኽ ሃሰን ከመሞታቸው አስቀድሞ ቤተክርስቲያኗን እንዲጠብቁ ለልጆቻቸው አደራ ሰጥተዋል።

አሁን እርሱም ይህንን አደራ ተቀብሎ በጥበቃ ሥራ ሊገባ መሆኑን ተናግሯል።

"ይህ ከአያቶቻችን የጀመረ በጎ ተግባር ነው። ከእምነታችን ጋር የሚጋጭ ነገር የለም። በትብብር መስጊድም ይሰራል። በሐይማኖታችን የሚዋጣ ሲኖር እናዋጣለን፤ የሚረዳውን እንረዳለን" ይላል መሃመድ።

"ሁሉንም ሐይማኖቶች አክብረን፤ ተዋውቀን ነው የምንኖረው" የሚለው መሃመድ፤ አባቱ ይህንን ካልተረዱ አንዳንድ ሰዎች የሚገጥማቸውን ተቃውሞ ተቋቁመው ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን መስክሯል።

ሼኽ ሃሰን ባለትዳርና የ7 ልጆች አባት ነበሩ።

ወይብላ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን

ወይብላ ማሪያም በወረኢሉ ወረዳ 06 ቀበሌ ከዋናው መንገድ 6 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ቀደም ሲል ቀርቀሬ ማሪያም በሚል ነበር የምትታወቀው።

ወረኢሉ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኝ ወረዳ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ498 ኪሎ ሜትሮች ይርቃል።

ቤተ ክርስቲያኗ በ1476 እንደተቆረቆረች ይነገራል። ከ400 በላይ ካህናትና መነኮሳትም ነበሯት።

ይሁን እንጅ በግራኝ አህመድ ወረራ ጊዜ ጉዳት ደርሶባት ሙሉ በሙሉ ተቃጥላ እንደነበር ይነገራል።

በወቅቱ ቦቦታው ብዙ የክርስትና እምነት ተከታዮች አልነበሩም።

ቦታው ዝንጀሮዎችና ድኩላዎች የሚቦርቁበትና በአገር በቀል ዛፎች የተሸፈነ ነው።

የአካባቢው ነዋሪ የተጣላን ለማስታረቅ ሐይማኖት ሳይለየው ለሽምግልና ይቀመጥበታል።

ከበር "በአካባቢው ለረዥም ጊዜ የኖሩት የሼኽ ሃሰን ቅድመ አያትና አባት ቤተክርስቲያኗን ያስቡ፤ ይዘክሩ ነበር" ይላል።

እርሱ እንደሚለው በወቅቱ ያንን ሲያደርጉ ማንም አያውቅም ነበር።

ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሰ የመጣው በጎ እሳቤም ሼኽ ሃሰን ጋር ደረሰ። እርሳቸውም ጥበቃቸውን በዚሁ መልኩ ቀጠሉ።

መጨረሻ ላይ ግን በወረዳው ወደሚገኝ ቤተ ክህነት ሄደው ቦታውን አሳዩ።

"እኛ ሙስሊሞቹ ስንዘክር ነው የቆየነው፤ እባካችሁ ቤተክርስቲያኗን አሰሩ" ሲሉም ጥያቄ አቀረቡ።

ወይብላ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን

የፎቶው ባለመብት, Keber Getachew FB Page

የምስሉ መግለጫ, ወይብላ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን

"የቤተ ክርስቲያኗን ግንባታ ከፊት ሆነው የመሩት ሼኽ ሃሰን ናቸው"

ሼኽ ሃሰን የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ድረስ ሄደው ቤተክርስቲያኗ እንድትሰራ ግንባር ቀደም ሆነው መርተዋል።

በዚህ የተጀመረው ግንባታ ተጠናቆ አሁን ሐይማኖታዊ ክብረ በዓል በደማቅ ሁኔታ ከሚከበርባቸው ቤተክርስትያናት አንዷ ሆናለች።

በቤተ ክርስቲያኗ ግንባታ ወቅት የቤተክርስትያኗ ገንዘብ ያዥ የነበሩትና የሐሮ ገነተ ጊዮርጊስ እና የወይብላ ማርያም ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ አቶ ጉልላት አለሜ "ወደ ቤተክርስትያኗ ግንባታ ስንገባ ሼኽ ሃሰንን ይዘን ነው የገባነው" ይላሉ።

የአቶ ጉልላትና ሼኽ ሃሰን ትውውቅ የጀመረው በ1997 ዓ.ም ነው።

አቶ ጉልላት የቤተክርስትያኗ ቦታ ሼኽ ሃሰን ከቤተሰብ የወረሱት ይዞታ ነበር ይላሉ።

"ቦታውን ፈቅደውልን ለወረዳና ለዞን አገረ ስብከት እንዲያመለክቱ፤ እርሳቸውን ከፊት አስቀድመን እኛ ደግሞ እርሳቸውን ተከትለን ፍጻሜው ላይ ደርሷል" ይላሉ ስለነበረው ሁኔታ ሲያስታውሱ።

ቦታው ከሦስት ሔክታር በላይ እንደሚሆን ይገምታሉ።

ሼኽ ሃሰንና ቤተሰባቸው የቤተ ክርስትያኗን ቦታ በክብር ጠብቀው ብቻ አይደለም ያቆዩት።

ቤተ ክርስትያኗ ስትሰራ ባህር ዛፍ ሰጥተዋል።

ድንጋይ በሸክም አግዘዋል። በወቅቱ 'ለእንስሳት እንኳን አይመችም' በሚባል መንገድ በትከሻቸው ዕቃ ተሸክመው ወደ ተራራው አጓጉዘዋል።

እንደየ እምነታቸው በግም፣ ከብትም ለብቻ አርደው፤ ዳስ ጥለው፤ ደግሰው ከእምነቱ ተከታዮች ጋር አብረው ቤተክርስቲያኗን አስመርቀዋል።

የቤተክርስቲያኗ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በግንባታው ላይ በመሳተፍም ሆነ፤ ሲሚንቶ፣ ቆርቆሮ፣ ብሎኬት፣ እንጨትና የግንባታ ቁሳቁሶችን ተሸክመው ያጓጓዙት በአካባቢው የሚኖሩ ሙስሊሞች ናቸው።

"የሼኽ ሃሰን ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ይህንን የሚያደርጉት በፍፁም ደስታ ነው። ቆመው ነው ቤተ ክርስትያኗን ያሰሩት። ሼኽ ሃሰን በጊዜ ብዛት የዓይን ብርሃናቸውን ቢያጡም በሰው እገዛ ቤተክርስቲያኗን ሳይጎበኙ አይውሉም ነበር" ይላል ከበር።

ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ቤተክርስቲያኗን ቆመው አስመርቀዋል።

የእምነቱ ተከታዮችም ጋቢ፣ ሙሉ ልብስ፣ ጫማ፣ ሌሎች ሽልማቶችና ስጦታዎች አበርክተውላቸዋል።

ሼኽ ሃሰን ምን ዓይነት ሰው ነበሩ ተብለው የተጠየቁት የቤተክርስትያኗ አስተዳዳሪ አቶ ጉልላት "ሼኽ ሃሰን ከባድ ሰው ናቸው እኮ! የእድሜ ጉዳይ ሆኖ ይችን ምድር ተሰናብተዋል። እስካሁን ድረስ ግን በእርሳቸው ሃዘን ላይ ነው ያለነው" ብለዋል።