የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ አባላት በሕንድ የቢቢሲ ቢሮ መፈተሹ ማስፈራራት ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባላት በሕንድ የቢቢሲ ቢሮዎች ላይ በአገሪቱ የታክስ ባለሥልጣናት የተደረገውን ፍተሻ ማስፈራራት እንደሆነ ገለጹ።
ባለፈው ሳምንት በዴልሂ እና ሙምባይ ከተሞች የሚገኙት የቢቢሲ ቢሮዎች የተፈተሹ ሲሆን፣ አንዳንድ ሠራተኞችም ሙሉ ሌሊቱን በጥያቄ ሲጣደፉ ነበር ተብሏል።
እየተደረገ ካለው ምርመራ ጋር በመተባበር ላይ መሆኑን የገለጸው ቢቢሲ፣ በቅርቡ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን የሚተች ዘጋቢ ፊልም ማቅረቡም ይታወሳል።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ሩትሊ መንግሥት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ነው ብለዋል።
የሥራ እና አሠሪ ሚኒስትር ፋቢያን ሃሚልተን በበኩላቸው “ትችትን በዲሞክራሲ ውስጥ መዝጋት አይቻልም” ሲሉም ወቅሰዋል።
ሚኒስትሩ ሕንድ በቢቢሲ ቢሮች ላይ ስላደረገችው ፍተሻ ያቀረበችው ይፋዊ ምክንያት ምንም ይሁን ምን ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
አክለውም “ቢቢሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረ ዜና አቅራቢ እና ከፍተኛ ጥራት እና እምነት የሚጣልባቸው ዘገባዎችን በመሥራት ይታወቃል። ቢቢሲ ያለ ምንም ማስፈራራት በነጻነት ሪፖርት ማድረግ እና መስራት አለበት” ብለዋል።
ጂም ሻነን በበኩላቸው ፍተሻውን “የአገሪቱ መሪን የሚመለከት ደስ የማይል ዘጋቢ ፊልም መውጣቱን ተከትሎ ሆን ተብሎ የማስፈራራት ተግባር ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ የዩኬ መንግሥት የሕንድ ከፍተኛ ኮሚሽንንም እንዲጠራ ጠይቀዋል።
ወግ አጥባቂው ሰር ጁሊያን ሉዊስም ፍተሻውን “እጅግ አሳሳቢ” ሲሉ ገልጸውታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ሩትሊ በጉዳዩ ላይ በቀጥታ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው “የሕግ የበላይነትን ማክበር የፍሬያማ ዲሞክራሲ ወሳኝ አካል ነው፣ እንዲሁም ነፃ ሚዲያ እና የመናገር ነፃነትም ጭምር” ብለዋል።
ቢቢሲ የሠራው ዘጋቢ ፊልም “ኢንዲያ፡ ዘ ሞዲ ኩዌስችን” የሚሰኝ ሲሆን፣ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውሮፓውያኑ 2002 የጉጅራት ግዛት ዋና አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት በግዛቲቷ ፀረ-ሙስሊም ሁከት ውስጥ በነበራቸው ሚና ላይ ያተኮረ ነው።
የሕንድ መንግሥት ፊልሙን “የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ” ሲል የጠራው ሲሆን፣ ፊልሙ በሚታይበት ወቅት የዴልሂ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋልን ጨምሮ በአገር ውስጥ እንዳይተላለፍ ለማገድ ሞክሯል።












