በሶማሊላንድ የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶማሊላንድ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መሸሻቸውን ገለጸ።
ተመድ ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት መካከል አብዛኛዎቹ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ከወላጆቻቸው የተለዩ ሕጻናት እንደሆኑ አመልክቷል።
ሉዓላዊት አገር ነኝ የምትለው ሶማሊላንድ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በመንግሥት ኃይሎች እና በአካባቢ የሚሊሻ አባላት መካከል በሚከሰት ግጭት ሰላም እርቋት ቆይቷል።
ከሳምንታት በፊት ላስ አኖድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከስቶ በነበረ ግጭት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መገደላቸው ተዘግቦ ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ በግጭት ውስጥ ካለችው ላስ አኖድ ወረዳ በመሸሸ ወደ ኢትዮጵያ ዶሎ አካባቢ የደረሱ ሰዎች ቢያንስ 80 ሺህ ይደርሳል ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ግጭት በመሸሽ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉ ሰዎች ቁጥር በአማካይ 1ሺህ ይሆናል ብሎ ነበር።
ድርጅቱ በአምስት የዝናብ ወቅት እጥርበት ባላገኛቸው እና ከፍተኛ ድርቅ ከተከሰተበት አካባቢ ቀያቸውን ጥለው የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር መጨመር ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ብሏል።
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ለሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ “ባለፉት ሁለት ሳምንታት አብዛኛዎቹ ትንሽ ከፊሉ ደግሞ ምንም ምግብ ስላላገኙ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ ግብዓት አቅርቦት እና ልዩ የጥበቃ እና የከላላ አገልግሎት በአስቸኳይ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ወደ ኢትዮጵያ ከተሰደዱት በተጨማሪ በሶማሊላንድ ውስጥ የተፈናቀሉ እንዳሉ ይገመታል። እንደ ድርጅቱ ከሆነ በመላው ሶማሊላንድ በሚገኙ 66 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ 180ሺህ ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አመልክቷል።
ሶማሊላንድ እአአ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከሶማሊያ እራሷን ገንጥላ ነጻ አገር ነኝ ብትልም ዓለም አቀፍ እውቅና ግን የላትም።
ሶማሊላንድ በቅርቡ ከምርጫ መዘግየት ጋር በያያዘ አለመረጋጋት ይግጠማት እንጂ ሰላም በሚርቀው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ተረጋግታ ለረዥም ጊዜ ዘልቃለች።












