የሁቲ አማጽያን ቀይ ባሕርን ሲቀዝፍ የነበረ የአሜሪካ መርከብ መምታቸውን ገለጡ

የየመን ሁቲ አማጽያን ቀይ ባሕርን ሲቀዝፍ የነበረ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ መርከብ መምታቸውን አስታወቁ።

አማጽያኑ የአሜሪካ ንብረት ነው ያሉት መርከብ መጠሪያው ኬኦአይ እንደሆነ ተሰምቷል።

የባሕር ጥበቃ ኩባንያ የሆነው አምብሬ፤ በየመን የኤደን ጠረፍ አቅራቢያ ፍንዳታ መስማቱን ይፋ ቢያደርግም ስለመርከቧ ምንነት ያለው የለም።

በተያያዘ ዜና ዩናይትድ ስቴትስ በየመን የምታደርሰውን ጥቃት የቀጠለች ሲሆን ሊወነጨፉ የተዘጋጁ 10 ድሮኖችን መደምሰሷ ተሰምቷል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጠው ኬኦአይ በላይቤሪያ ባንዲራ የምትንቀሳቀስ፤ መቀመጫውን ዩኬ ባደረገ አንድ ኩባንያ የምትተዳደር መርከብ ናት።

በዚሁ ኩባንያ የምትተዳደረው ማርሊን ሉዋንዳ የተባለች ነዳጅ ተሸካሚ መርከብ ባለፈው ሳምንት ጥቃት እንደደረሰባት ይታወሳል።

የሁቲ አማጽያን የእስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታኒያ ንብረት የሆኑ መርከቦችን ዒላማ ማድረግ የጀመሩት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።

ይህን ተከትሎ አሜሪካ እና ብሪታኒያ ዓለም አቀፍ ንግድን ለመጠበቅ በሚል የሁቲዎችን ሚሳዔል ማከማቻ መምታት ጀምረዋል።

የሁቲ አማጽያን የወታደራዊው ክንፍ ቃል አቀባይ የሆኑት ያህያ ሳሪያ ረቡዕ ዕለት እንዳሉት ቡድኑ “በርካታ ሚሳዔሎች ተጠቅሞ” የአሜሪካ ወታደራዊ መርከብ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።

አፈ ቀላጤው እንደሚሉት መርከቧ “በቁጥጥር ሥር ወዳለችው ፍልስጤም” እያመራች ነበር። “በቁጥጥር ሥር የምትገኘው ፍልስጤም” የሚለው መጠሪያ እስራኤል ማለት እንደሆነ ይነገራል።

ያህያ አክለው የመን “ለአሜሪካና ብሪታኒያን ጥቃት ምላሽ ለመስጠት አታመነታም” ብለዋል።

“ሁሉም የአሜሪካና የብሪታኒያ መርከቦች በቀይ እና በአረቢያን ባሕር በኩል እስካለፉ ድረስ የየመን ታጣቂ ኃይሎች ዒላማ ናቸው። አሜሪካ እና ብሪታኒያ ሀገራችን ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እስካልቆመ ድረስ ይህ ይቀጥላል።”

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ከየመን ሊወነጨፉ የነበሩት 10 ድሮኖች የአሜሪካ ወታደራዊና የንግድ መርከቦችን ለማጥቃት የተሰናዱ ነበሩ ብሏል።

ዩናይትድ ስቴትስ አክላ በየመን ባሕረ ሰላጤ ሶስት የኢራን ድሮኖችን እና አንድ የሁቲ ፀረ-መርከብ ባለስቲክ ሚሳዔል መትታ መጣሏን ተናግራለች።

የየመን አማጽያን ቀይ ባሕርን ለንግድ መመላለሻ የሚጠቀሙ መርከቦች ላይ እየወሰዱ ባሉት ጥቃት ምክንያት ዓለም አቀፍ ንግድ እየተጓተተ ሲሆን የአቅርቦት ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ባለፈው ጥቅምት በእስራኤል እና በፍልስጤሙ ሐማስ መካከል የተነሳው ግጭት በመካከለኛው ምስራቅ እየተስፋፋ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።