በቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ቤት የመንግሥት ምስጢራዊ ሰነዶች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቀድሞው እና ከአሁኑ የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶች በተጨማሪ በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ መኖሪያ ቤት ውስጥ የመንግሥት ምስጢራዊ ሰነዶች መገኘታቸው ተዘገበ።
ሰነዶቹ ኢንዲያና ግዛት ባለው የማይክ ፔንስ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኘው ባለፈው ሳምንት በጠበቃቸው አማካይነት ሲሆን፣ ለፌደራሉ የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ተላልፈው ተሰጥተዋል ተብሏል።
ይህ ሰነድ በምክትል ፕሬዝዳንቱ ቤት የተገኘው መርማሪዎች በወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይዞታ ውስጥ አሉ የተባሉ ምስጢታዊ ሰነዶችን እየፈለጉ ባለበት ጊዜ ነው።
ትራምፕ የመንግሥት ምሥጢራዊ ሰነዶችን በአግባቡ ባለመያዝ የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛሉ።
የማይክ ፔንስ ተወካዮች በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ቤት ስለተገኙት ሰነዶች ለአገሪቱን ብሔራዊ ቤተመዛግብት በደብዳቤ አሳውቀዋል።
የኤፍቢአይ አባላትም ወደ ፔንስ ቤት በመሄድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰነዶቹን በአስቸኳይ መሰብሰባቸውን ጠበቃቸው በደብዳቤ ገልጸዋል።
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ መዛግብት አያያዝ ደንብ መሠረት፣ የመሪዎቹ የሥልጣን ዘመን ሲያበቃ ሁሉም ሰነዶች ለብሔራዊ መዛግብት ማከማቻ ተላልፈው እንዲሰጡ ይደረጋል።
በደንቡ እንዲህ ያሉት አገራዊ እንዲሁም ምስጢራዊ ሰነዶች ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ እንዲቀመጡ ያዛል።
በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ማብቂያ ላይ “ባልታሰበ ሁኔታ ምስጢራዊ የሚል መለያ ያላቸው የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰነዶች በካርቶን ውስጥ ተደርገው” ወደ ፔንስ ቤት ተወስደዋል፣ ሲሉ ጠበቃቸው ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በጻፉት ደብዳቤ ላይ ገልጸዋል።
ሰነዶቹ ሊገኙ የቻሉት ፔንስ ለጥንቃቄ ሲሉ በምስጢራዊ ሰነዶች አያያዝ ዙሪያ የሕግ ባለሙያዎችን ድጋፍ በጠየቁበት ጊዜ ነው።
“በፕሬዝዳንት ባይደን ዊልሚንግተን መኖሪያ ቤት ውስጥ ምስጢራዊ የሚል መለያ ያላቸው ሰነዶች መገኘታቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ ነው” የቀድሞው ፕሬዝዳንት ድጋፍ የጠየቁት ሲል ደብዳቤው አመልክቷል።
“የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ጥንቃቄን የሚፈልጉ ወይም ምስጢራዊ መረጃዎችን ሊይዙ የሚችሉ ሰነዶችን” በማይክ ፔንስ ካዝና ውስጥ ተቆልፎባቸው ማግኘታቸውን ጠበቆች አሳውቀዋል።
ሰነዶች በቀድሞው ምክትላቸው ቤት ውስጥ መገኘቱ ይፋ ከሆነ በኋላ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በራሳቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ‘ትሩዝ ሶሻል’ ላይ ፔንስን “ንጹህ ሰው ነው” ሲሉ ተከላክለዋል።
“በሕይወቱ ውስጥ ሆን ብሎ ተአማኒነት የጎደለው ነገር ፈጽሞ አያውቅም” ያሉት ትራምፕ “ለቀቅ አድርጉት” በማለት ስለፔንስ ንጽህና መስክረዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ባለፉት ወራት በእጃቸው ውስጥ ምስጢራዊ ሰነዶች ይኖራሉ ብለው እንደማያስቡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።
ከቀድሞው ፕሬዝዳንት በተጨማሪ ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ የተዘጋጁ ምስጢራዊ ሰነዶች በቢሯቸው እና በመኖሪያ ቤታቸው መገኘቱ በአሜሪካ ውስጥ መነጋገሪያ ሆኗል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ እና ጆርጅ ቡሽ ባለፈው ማክሰኞ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ሥልጣን በለቀቁበት ጊዜ በእጃቸው የነበሩ ሁሉንም ሰነዶች ለብሔራዊው ቤተመዛግብት መልሰዋል።
በባይደን እና ፔንስ ቤት ውስጥ ምስጢራዊ ሰነዶች መገኘታቸው የተገለጸው፣ ትራምፕ መንግሥታዊ ሰነዶችን በአግባቡ አልያዙም በሚል ልዩ የምርመራ እየተደረጋባቸው መሆኑ ከተገለጸ በኋላ ነው።
ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኘው ማራ ላጎ በተባለው የትራምፕ መኖሪያ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምስጢራዊ ሰነዶች ተገኝተዋል። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ትራምፕ እና ጠበቆቻቸው ሰነዶቹን ለኤፍቢአይ አሳልፈው ለመስጠት አሻፈረኝ ብለው ነበር።
ትራምፕ በበኩላቸው ምንም ጥፋት አለመፈጸማቸውን በመግለጽ፣ ኤፍቢአይ ለፕሬዝዳንት ባይደን እያደላ ነው በማለት ወቅሰዋል።












