ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፅንስ የማቋረጥ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን አደባባይ ወጡ
ከሁለት ሳምንት በፊት የፅንስ ማቋረጥን የሚፈቅደው ሕግ የቀለበሰውን የፍርድ ውሳኔ በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በዋይት ሐውስ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
በትናንትናው ዕለት የጀመረው ተቃውሞ ዝናብ አልበገረውም፣ እንዲሁም በርካቶች ሊታሰሩ እንደሚችሉ ቢያውቁም በተቃውሟቸው ቀጥለዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ‘ሮ ቨርስ ዌድ’ የተሰኘውን እና በአገር አቀፍ ደረጃ ለ50 ዓመታት ያህል የፅንስ ማቋረጥን በመፍቀድ ተደራሽ መሆኑን ያረጋጠውን ውሳኔ መቀልበሱን ካሳወቀ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው የተቃውሞው ሰልፍ እየተካሄደ ያለው።
“ወደ ኋላ አንመለስም” የሚሉ ተቃዋሚዎች በዋይት ሐውስ የተሰባሰቡ ሲሆን አንዳንዶቹም ራሳቸውን ከበሩ ጋር በማያያዝ እሰረው ታይተዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆቹ እንዳሳወቁት ከመላው አሜሪካ የተሰባሰቡ በ10 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች ተገኝተዋል።
በዳላስ ጠበቃ የሆነችው የ33 ዓመቷ ላውረን ፒርስ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ለመገኘት 2 ሺህ 100 ኪ.ሜ ተጉዛለች።
“ለእኔ ከዚህ አላማ የበለጠ የምታገልለት ምንም ነገር የለም። በራሳችን ሰውነት የማዘዝ መሠረታዊ መብታችን ነው። ይህንን ለማስከበር ተቃውሞ መውጣት እና መታሰር ከሆነ የምከፍለው ዋጋ ነው” ብላለች።
የላውረን የትውልድ ቦታ ቴክሳስ ግዛት ፅንስ ማቋረጥ ከተከለከለባቸው 10 የአሜሪካ ግዛቶች መካከል አንዱ ነው። ቢያንስ አስር ሌሎች ግዛቶች የቴክሳስን ፈለግ ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፅንስ ማቋረጥን የሚቃወሙ ግለሰቦች ድርጊቱን እንደ ግድያ የሚቆጥሩት ሲሆን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ እና በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች ፅንስ ማቋረጥን ሕገ ወጥ ለማድረግ ዕድል በማስገኘቱም ደስታቸውን እየገለጹ ነው።
ላውረን ይህ ውሳኔ በቴክሳስ በርካቶች በድንገት ያለ ሥነ ተዋልዶ ጤና እንክብካቤ አገልግሎት እንዲቀሩ አድርጓቸዋል በማለት ታስረዳለች።
በቴክሳስ ውስጥ በመጀመሪያዎቹ 20 ሳምንታት ፅንስ ማቋረጥ ለሚፈልጉ ሴቶች 400 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ ይኖርባቸዋል ሲል ጉትማቸር የተባለ የፅንስ ማቋረጥ ደጋፊ የምርምር ቡድን ገልጿል።
“እግድ ላይ ነን” ብላለች ላውረን።
ላውረን እንደ ሌሎች በዋይት ሐውስ እንደተሰበሰቡት ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና አስተዳደራቸው የፅንስ ማቋረጥን መብት ለማስጠበቅ ባለመቻላቸው ብስጭታቸውን እየገለጹ ነው።