ቤተ መንግሥታቸው በተቃዋሚዎች የተወረረው የሲሪላንካ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን ሊለቁ ነው

ተቃዋሚዎች የሲሪላንካውን ፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ አስታወቁ።

ተቃዋሚዎቹ በደረሱበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፕሬዚዳንቱ በቅጥር ግቢው ውስጥ አልነበሩም።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በመዲናይቱ ኮሎምቦ አደባባይ ወጥተው ፕሬዚዳንት ራጃፓክሳ ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ጠይቀዋል።

ይህም በአገሪቱ በኢኮኖሚ አስተዳደር እጦት ምክንያት ለወራት ከዘለቀው የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ መሆኑም ተዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ራጃፓክሳ ከቀናት በኋላ ሥልጣን ይለቃሉ ተብሏል። ከእሳቸው በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዊክሬሜሲንጌ ከሥልጣን ለመልቀቅ ተስማምተዋል።

የፓርላማው አፈ-ጉባዔ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት “በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ርክክብ እንዲኖር ነው” ሲሉ ሕዝቡም “ሕግ እንዲያከብር” ጠይቀዋል።

የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ፈንጠዝያን ፈጥሯል፤ በርካቶችም ርችቶችን በተኮስ ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

በትናንትናው ዕለት ተቃዋሚዎች የፕሬዚዳንቱን መኖሪያ ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ አሜሪካ የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት ችግር ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ የሲሪላንካ አመራሮችን ጠይቃ ነበር።

በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ለተቃውሞ ወጥታ የነበረች ፊዮና ሲርማና የተባለች ግለሰብ “ፕሬዚዳንቱን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን በማስወገድ ለሲሪላንካ አዲስ ዘመን የምንቀዳጅበት ጊዜ አሁን ነው” ስትል ተናግራለች።

“ቀደም ብለው ከሥልጣን ባለመውረዳቸው በጣም አዝኛለሁ፤ ምክንያቱም ቀደም ብለው ቢሰናበቱ ምንም አይነት ውድመት ባልደረሰም ነበር” ስትል ለሮይተርስ ዜና ወኪል አስረድታለች።

በቅዳሜው ተቃውሞ በርካታ ዜጎች የቆሰሉ ሲሆን፣ የኮሎምቦ ዋና ሆስፒታል ቃል አቀባይ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው ህክምና እየተደረገላቸው ነው።

ሲሪላንካ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተናጠች ሲሆን በአገሪቱ በ70 ዓመታት ውስጥ ያልታየ በተባለው አስከፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድኃኒት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየታገለች ነው።

የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ተመናምኖ ያለቀ ሲሆን፣ ለግል ተሽከርካሪዎች ቤንዚን እና ናፍታ ሽያጭ ላይ እገዳ ተጥሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞም ነዳጅ ለማግኘት ለቀናት በርካቶች ረጃጅም ሰልፎች ላይ ታይተዋል።

የቅዳሜው ያልተለመደ ክስተት በሲሪላንካ ውስጥ ለወራት የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ማክተሚያ ይመስላል።

በፕሬዚዳንት ራጃፓክሳ መኖሪያ ቤት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገሪቱን ሰንደቅ አላማ የያዘ ሕዝብ መፈክሮችን በማሰማት አጥሩን ጥሰው ገብተዋል።

ከስፍራው የወጣ ቪዲዮ ተቃዋሚዎች በግቢው ውስጥ ሲዘዋወሩ እና በፕሬዚዳንቱ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሲዋኙ፣ ሌሎች ደግሞ የፕሬዚዳንቱን እቃዎች ሲበረብሩ እንዲሁም አንዳንዶች የቅንጦት መታጠቢያ ቤታቸውን ሲጠቀሙ ያሳያል።

ቅንጡ የሚባለው የፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት እና 22 ሚሊዮን ሕዝብ ነዋሪ ያሳለፈው የመከራ ወራት ልዩነት ተቃዋሚዎች በዝምታ ሊያልፉት አልፈለጉም።

“መላው አገሪቱ እንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ ባለበት ወቅት ሰዎች የተሸከሙት ጫና ለማስተንፈስ ወደዚህ መጥተዋል። በዚህ ቤት ውስጥ ያለውን የቅንጦት ሁኔታ ስንመለከተው ለአገር ለመስራት ጊዜ እንደሌላቸው ግልፅ ነው” በማለት ቻኑካ ጃያሱሪያ የተባሉ ግለሰብ ለሮይተርስ ተናግረዋል።