ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተቃዋሚዎች የሲሪ ላንካው ፕሬዝዳንት መኖሪያ ቤትን ጥሰው ገቡ
በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በሲሪ ላንካ መዲና ኮሎምቦ ውስጥ ወደሚገኘውን ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ መኖሪያ ቤት በኃይል ጥሰው መግባታቸው ተዘገበ።
ከመላው አገሪቱ የተወጣጡ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት በመዲናዋ ኮሎምቦ ተሰባስበዋል።
ተቃዋሚዎች የፕሬዝዳንቱን መኖሪያ ቤት ጥሰው ሲገቡ ፕሬዝዳንቱ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ስለመኖራቸው እርግጠ ለመሆን ባይቻልም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ጊታባያ ራጃፓክሳ ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ ቦታ ተወስደዋል ተብሏል።
ሲሪ ላንካ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።
በሲሪ ላንካ ክ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ያጋጠማት ሲሆን፤ መድኃኒት፣ ነዳጅ እና ምግብ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ተስኗታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ከመላው አገሪቱ በግል መኪኖች እና በአውቶቢሶች ወደ መዲናዋ ሲተሙ ቆይተዋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ደግሞ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ባቡሮችን አስገድደው ወደ መዲናዋ ተጉዘዋል።
ተቀዋሚዎች ወደ ፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት በኃይል ከመግባታቸው በፊት ወደ ከተማዋ የአስተዳደር ሕንጻ በኃይል ገብተዋል።
በመቀጠልም ፕሬዝዳንቱን የሚቃወሙ መፈክሮችን እያሰሙ በርካታ የፖሊስ ኬላዎችን ጥሰው በማለፍ ፕሬዝዳንታዊ መኖሪያ ቤት መድረሳቸውን የዐይን እማኞች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ፖሊስ ተቀዋሚዎች ወደ መኖሪያ ቤቱ ዘልቀው እንዳይገቡ ለመከላከል ጥይት ወደ ሰማይ ሲተኩስ ቢቆይም፤ ተቃዋሚዎች የጎታባያ ራጃፓክሳ መኖሪያ ቤትን ሰብረው ከመግባት ማስቆም አልተቻለውም።
ባለሥልጣናት ቀደም ብለው ታቅዶ የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ ለማስቆም ዓርብ ሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ሰዓት እላፊ አውጀው ነበር።
ይሁን እንጂ ሲቪል ማኅበራት እና ተቀዋሚ ፓርቲዎች የሰዓት እላፊ አዋጁን አጥብቀው ከተቃወሙ በኋላ ታውጆ የነበረው ሰዓት እላፊ እንዲነሳ ተደርጓል።
ሲሪ ላንካ የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን የጨረሰች ሲሆን መሠረታዊ የሚባሉ ቁሶችን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አልቻለችም።
በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ሲሪ ላንካ ላጋጠማት ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ፕሬዝዳንት ራጃፓካሳን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፤ ተቀዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ለወራት ሲጠይቁ ቆይተዋል።