ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“መኪናዬን ሸጬ ነበር ለሐጂ ጉዞ የተዘጋጀሁት” ጉዞው የተስተጓጎለበት
በየዓመቱ ከመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሐጂ ጉዞ ያደርጋሉ። በርካታ ኢትዮጵያውያንም የሐጂና ኡምራን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመከወን ወደ መካ ይጓዛሉ።
ይህ የሐጂ ሥርዓት ከትናንት በስቲያ በሳዑዲ አረቢያ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው እስላማዊ ቅዱስ ከተማ፣ መካ ውስጥ ተጀምሯል።
ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት በርካታ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮች በዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ለመገኘት አልታደሉም።
አሕመድ ከረም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።
አሕመድ፣ ሐጂ ለማድረግ ላለፉት አራት ዓመታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ሆኖም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተጣሉ እገዳዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ዕድሉን ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።
በዚህ ዓመት ግን ተስፋ አድርጎ ነበር።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ግንቦት ወር ውስጥ የሐጂ ተጓዦችን ሲመዘገብ ቀደም ብሎ ነበር የተመዘገበው።
በእርግጥ ከእርሱ በፊት የተመዘገቡ 5 ሺህ 650 ሰዎች ነበሩ።
አሕመድ እንደሚለው የሳዑዲ ሐጂ ሚኒስቴር ለየአገራቱ ከሚሰጠው ኮታ ለኢትዮጵያ የሰጠው 19 ሺህ 600 ነበርና በምንም ሁኔታ እቀራለሁ የሚል ግምት አልነበረውም።
ለጉዞው የሚያስፈልገውን 241 ሺህ ብር ከፍሎ በመጠባባቅ ላይ ነበር።
ይሁን እንጂ “የሐጂው ጉዞ ሊጠናቀቅ 10 ቀን ሲቀረው መንግሥት በገጠመው የዶላር እጥረት ምክንያት ዶላር መፍቀድ የምንችለው ለሦስት ሺህ ተጓዦች ብቻ ነው የሚለውን ዜና ሰማሁ” ይላል።
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባለቤቷ ጋር የሐጂ ጉዞ ለማድረግ ተመዝግባ የነበረችው ሃናንም ይህንን ዕድል ካላገኙ ሰዎች መካከል ትገኝበታለች።
“በጉጉት ነበር ስጠባበቅ የነበረው። ብዙ ሥራዎቻችን ወደ ኋላ ብለን ይህንኑ ጉዳይ ስንከታተል ነበር የቆየነው” ብላለች።
“በጣም ነው ያዘንኩት፤ እዚህ የማከብረው በዓል አልመሰለኝም”
አሕመድ እንደሚለው ዘንድሮ ሐጂ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አድርጎ ነበር።
“እዚያ ስሄድ የሚለበሰውን ኢህራምም ገዝቼ፣ በግሌ የማወጣውን ወጪም አዘጋጅቼ ነበር ስጠባበቅ የነበረው” ይላል።
ኢህራም ከላይ የሚለበስ እና እንደ ሽርጥ የሚገለደመው ነጭ ፎጣ ነው።
የዛሬ አራት ዓመት በኤጀንሲዎች በኩል ለመሄድ ተመዝግቦ፣ የተመዘገበው ሰው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ቪዛ ማግኘት ሳይችል እንደቀረም አሕመድ ያስታውሳል።
ከዚያ በኋላም ባሉት ሁለት ዓመታት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በተጣሉ እገዳዎች እና የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የሌሎች አገራት ዜጎችን እንደማይቀበል በማስታወቁ ህልሙ ሳይሳካ ቆይቷል።
“በዚህ ዓመት አሳካዋለሁ የሚል ሙሉ ተስፋ ነበረኝ” የሚለው አሕመድ፤ በአገሪቷ ባለው የዶላር እጥረት ምክንያት የልቡ ሳይሞላ ቀርቷል።
“የንግድ ተቋሜን ለማጠናከርና የሐጂ ጉዞ ዕቅዴን ለማሳካት መኪናዬን ሸጫለሁ” ብሏል።
ሃናንም በበኩሏ ሊያተርፉበት የሚችሉበትን እቃ ከመግዛት ተቆጥበው ጉዞውን ሲጠባበቁ እንደነበር ገልጻለች።
ለጉዟቸውም ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር እንደከፈሉ ተናግራለች።
የሐጂ ጉዞ የምዝገባ ቁጥራቸው 6 ሺህ ቤት ገደማ በመሆኑ ዕድሉን እናገኛለን በሚል ተስፋ ሲሰነዳዱ እንደነበር የምትናገረው ሃናን፣ “ጉዞዬ ከመደናቀፉ ባሻገር ኑሮዬን እንደገና ለማስተካከል ተገድጃለሁ” ብላለች።
አሕመድ እንደሚለው በተለይ የተሻለ ገቢ ለሌላቸው የእምነቱ ተከታዮች ሐጂ ማድረግ በብዙ ዓመታት ዕቅድ የሚሳካ ነው።
“ይህንን ዕድል ለአራተኛ ጊዜ ባለማግኘቴ ሐዘን ተሰምቶኛል፤ እኔም ብቻ ሳልሆን ጥሪታቸውን ሸጠው፣ ለዓመታት ገንዘብ ቆጥበው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተሰባስበው ጉዞውን ሲጠባበቁ የነበሩ በእድሜ የገፉ ሰዎች ጭምር ሲያለቅሱና ሲተክዙ ተመልክቻለሁ” ብሏል።
በኢትዮጵያ የሚጠበቅበትን ገንዘብ ከፍሎ ሲጠባበቅ የነበረ ከስምንት ሺህ በላይ ሰው የሐጂ እና ኡምራ ጉዞው እንደተሰረዘበትም አሕመድ አክሏል።
ከባለቤቷ ጋር ሐጂ ለማድረግ ስትጠባበቅ የነበረችው ሃናንም፣ “ዕቅዱ ባለመሳካቱ በጣም ነው ያለቀስኩት” ብላለች።
“በዓሉንም እየከፋኝ ነው እያሳለፍኩ ያለሁት” ስትልም የተዘጋጀችበት ዕቅድ መና በመቅረቱ የተሰማትን ሐዘን አጋርታለች።
ሐጂ እና ኡምራ የሚደረገው ለምንድን ነው?
ሐጂ ማድረግ ከእስልምና አምስት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው።
አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ በእድሜ ዘመኑ አንድ ጊዜ ሐጂ የማድረግ ሃይማኖታዊ ግዴታ አለበት።
በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ አቅሙ የፈቀደለትና ቤተሰቡን ችግር ላይ ሳይጥል ሐጂ ማድረግ የቻለ ሰው በሕይወት ዘመኑ ሲሰራቸው የነበሩ ሀጢያቶችን አላህ ይቅር እንደሚለው ይታመናል።
የሐጂ ሥርዓት የሚጀመረው በእስልምና ዘመን አቆጣጠር ሒጅራ፣ የዓመቱ የመጨረሻው ወር በገባ በስምንተኛው ቀን ላይ ሲሆን፣ የአረፋ ዕለት በሥርዓቱ ላይ ያልተገኘ ሐጂ እንዳደረገ አይቆጠርም።
እስላማዊው የዘመን አቆጣጠር ሒጅራ፣ ነብዩ መሐመድ እና ተከታዮቻቸው ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱበት ጊዜ ነው።
የዘንድሮው ዋናው የሐጂ ሥነ ሥርዓት ሐሙስ [ሰኔ 30/2014 ዓ.ም ] የተጀመረ ሲሆን፣ለተከታታይ አምስት ቀናት ይካሄዳል።
ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ መሄድ የቻለ የእምነቱ ተከታይ የኡምራ ሥርዓት ላይ መሳተፍ ይችላል።
የኡምራ ሥርዓት እንደ ሐጂ ሃይማኖታዊ ግዴታ አይደለም። ኡምራ ግዴታ ያልሆነ [ሱና] ሲሆን ለእምነቱ ተከታዮች ተጨማሪ ምንዳ [በረከት] የሚያስገኝ ነው።
የሐጂ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ በኋላም በቂ ጊዜ ያለው ሰው በመዲና የሚገኘውን የነብዩ መሐመድና ተከታዮቻቸውን መቃብር እንዲሁም ሌሎች እስላማዊ ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት ይችላል።
“ለሚቀጥለው ዓመት ተስፋ ሰንቀናል”
አሕመድ ለዓመታት ያልተሳካለት የሐጂ ጉዞ በሚቀጥለው ዓመት ይሳካልኛል ብሎ ተስፋ አድርጓል።
“በተደጋጋሚ ስላልተሳካልኝ፣ ጉጉቴ ጨምሯል። በሚቀጥለው ዓመት አላህ ካደረሰኝ ቀድሜ ወረፋ ለመያዝ አስባለሁ” ብሏል።
አሕመድ ሃሳቡ ከተሳካለት በሚቀጥለው ዓመት ከባለቤቱ ጋር ለመሄድ ዕቅድ እንዳለው ገልጿል።
ሃናንም በበኩሏ ጉዞውን ለማድረግ በሚቀጥለውን ዓመት ይሳካልናል ብላ ተስፋ አድርጋለች።
በዘንድሮው የሐጂ ጉዞ ከኢትዮጵያ ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተጓዦች ዕድሉ ቢመቻችም የሦስት ሺህ ተጓዦች ብቻ መሳካቱን የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ የሐጂን ጉዞ በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት 19 ሺህ 600 የሚሆኑ የእምነቱ ተከታዮች የሐጂ ጉዞ ላይ እንዲሳተፉ ዕድል መስጠቱን ገልጸው፤ 12 ሺህ ተጓዦችን ለመውሰድ እቅድ ተይዞ እንደነበር አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ በተፈጠረው የዶላር እጥረት ምክንያት የ12 ሺህ የሐጂ ተጓዦችን ወጪ መሸፈን ሳይቻል ቀርቶ፣ ለሦስት ሺዎቹ ብቻ ዕድሉ መመቻቸቱንና አንድ ሺህ የሚሆኑት በተጠባባቂነት ተይዘው እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል።