ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዶላር እጥረት ምክንያት የተደናቀፈው የበርካታ ኢትዮጵያውያን የሃጂ ጉዞ
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ወደ ሳዑዲ አረብያ መካ የሃጂ እና ኡምራ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ለመፈፀም ይጓዛሉ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሥርዓቱ ሳይካሄድ ቆይቶ ዘንድሮ ተጀምሯል።
ከኢትዮጵያም ለ19 ሺህ ያህል ሰዎች በዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል ፈቃድ ተሰጥቶ ነበር።
ይህ ቁጥር ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት አንጻር ሲታይ ከፍተኛው ነው።
ነገር ግን ከተመዘገቡ ሰዎች መካከል ሦስት ሺህ የሚሆኑት ብቻ ለሃጂ አንደተጓዙ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) መረጃ ያሳያል።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሰዎች፣ በተለያዩ ምክንያቶች መሄድ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሃጂ አህመድ ሳሊ፣ ዕድሉን አግኝተው ዘንድሮ ከተጓዙ ሰዎች መካከል ሲሆኑ፣ አብረዋቸው ሊጓዙ ተዘጋጅተው የነበሩ በርካቶች ግን በዶላር እጥረት ምክንያት መቅረታቸውን ይናገራሉ።
ሃጂ ናስር አህመድ፣ ከምሥራቅ ሐረርጌ ለሃጂ ጉዞ ከቤታቸው ከወጡ ሁለት ወር አልፏቸዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ለመሄድ ተስፋ አድርገው የቆዩ በመሆኑም አሁን የሃጅ ሥርዓት እየተጠናቀቀ በመሆኑ ተስፋ መቁረጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዶላር እጥረት እና ሌሎች ምክንያቶች በተጨማሪ በመጅሊስ ውስጥ ያለው አስተዳደራዊ ችግር ብዙዎች ጉዞው እንዳይሳካላቸው አድርጓል ይላሉ ሼክ ሃጂ ኢብራሂም።
በዘንድሮው የሃጂ ጉዞ ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተጓዦች ዕድሉ ቢመቻችም የሦስት ሺዎቹ ተጓዦች ብቻ መሳካቱን የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ እድሪስ ተናግረው ነበር።
የዘንድሮውን የሃጂን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የሳዑዲ መንግሥት 19 ሺህ 600 ለሚሆኑ የሃጂ ጉዞ ላይ እንዲሳተፉ ዕድል መስጠቱን በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን አገሪቱ ያጋጠማትን የዶላር እጥረት ታሳቢ በማድረግ ቢያንስ 12 ሺህ ተጓዦችን ለመውሰድ ዕቅድ ተይዞ ነበር።
ነገር ግን በተፈጠረው ከፍ ያለ የዶላር እጥረት ምክንያት 12 ሺህ የሃጂ ተጓዠችን ወጪ ለመሸፈን ሳይቻል ቀርቷል።
የመጅሊሲ የሽግግር ፕሬዝዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ በኢትዮጵያ የሃጅ ተጓዦች፣ ዘንድሮ ያጋጠማቸው ችግር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ችግሩ ምን ነበር?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አመራር ውስጥ የተነሳው አለመግባባት መነጋገሪያ ሆኗል። አንዳንዶችም ይህ ሁኔታ የሃጂ ጉዞን ጨምሮ በሌሎች የሕዝብ ሙስሊሙ ጉዳዮች ላይ እንቅፋት እያስከተለ ነው ይላሉ።
ነገር ግን በሥራ ላይ የሚገኘው ምክር ቤት የሃጂ ሥርዓትን በራሱ ለማስፈፀም ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ቢነገርም፣ ተጓዦቹን ወደ መካ በመሸኘት ሂደት ችግሮች እንዳጋጠሙት ገልጿል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ እድሪስ መንግሥት ይህንን ጉዞ ለማሳካት 30 ሚሊዮን ዶላር ለመበጀት እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ዕቅድ ሳይሳካ ቀርቶ 8 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረው ነበር።
በዚህም ለ3000 ያህል የሃጂ ተጓዦች ብቻ ዕድሉ መመቻቸቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም 1000 የሚሆኑት በተጠባባቂነት እንዲቆዩ መደረጉን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ በመግለጫው ላይ “ከእኛም ጉድለት የለም፤ ከመንግሥትም ጉድለት የለም። በሰላም ወደየቤታችሁ ተመለሱ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር።
ነገር ግን ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ግን የችግሩ ምንጭ ዶላር እጥረት ነው የሚለውን አይስማሙበትም፣ ከዚያ ይልቅ ጉዳዩን ከአመራር ሕጋዊነት ጋር ያያይዙታል።
ሃጂ መሄድ ከማን ይጠበቃል?
በእስልምና ሃይማኖት አቅሙ ያለው ሁሉ ሃጂ የመሄድ ግዴታ አለበት።
ስለዚህም በመላው ዓለም ያሉ ሙስሊሞች የገንዘብ አቅማቸው ከፈቀደ፣ ያላቸውን ንብረት ወደ ገንዘብ ቀይረው ወደ መካ ይጓዛሉ።
በኢትዮጵያ የገጠሪቱ ክፍል የሚኖሩ በርካታ ሙስሊሞች ያላቸውን ንብረት ከብት፣ መሬት ሽጠው ወደ የሃጂ ጉዞ ያደርጋሉ።
ለሦስተኛ ጊዜ ሃጂ ለመሄድ በዚሁ መንገድ የተዘጋጁት ሃጂ ሐሰን ኢብራሂም እንደ ሌሎቹ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሳይሳካላቸው መቅረቱን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ተናግረዋል።
ለሃጂ ከቤታቸው የወጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለወራት አዲስ አበባ ያለመፍትሄ ቆይተው በመጅሊሱ ዋና ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ በማድረግ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ከተመዘገቡ በርካታ ሰዎች መካከል ከሦስት ሺህ እስከ 4000 ሰዎች ብቻ መላክ እንደሚችል መጅሊሱ ሲገልጽ በድንጋጤ ራሳቸውን የሳቱ ሰዎች እነደነበሩ ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ይናገራሉ።
በመጅሊሱ ውስጥ ያለ ችግር ከመካ መቅረት ብቻ ሳይሆን ወደ መካ የተጓዙት ላይም ጫና ፈጥሯል ይላሉ፤ ሼክ ሃጂ ኢብራሂም።።
“በመጅሊስ ውስጥ የሃጂ ጉዞ የሚከታተል ክፍል አለ። ይህ ክፍል ከምዝገባ ጀምሮ ሃጂ እስኪመለሱ ድረስ የሚከታተል ነው። እና መጅሊሱ ከተዳከመ ጠቅላላው የሃጂ ሂደት ችግር ይገጥመዋል” ይላሉ።
እና ይህ ችግር በጊዜ የማይፈታ ከሆነ በቀጣይ ዓመታት የሚደረገው የሃጂ ጉዞ ላይም ችግሮች ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ያላችው ስጋት ይገልጻሉ።