ሺንዞ አቤ እና አበበ ቢቂላ

ሺንዞ አቤ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር። የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ።

በወርሃ ጥር 2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ መጥተው ምን አደረጉ?

ከአበበ ቢቂላ ልጅ የትናየት አበበ ጋር ተገኛኙ። የትናየት የአባቱን የአበበ ቢቂላን ፎቶ አበረከተላቸው።

ለመሆኑ አበበ ቢቂላና ሺንዞ አቤ ምንና ምን ናቸው?

ከሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት እንደተሰማው ከሆነ እሳቸው አበበ ቢቂላን አይረሱትም።

አበበ ከ58 ዓመት ገደማ በፊት በቶኪዮ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ድል ሲያደርግ እሳቸው ትንሽ ልጅ ነበሩ። ተማሪ ቤት ነበሩ።

የአበበ ቢቂላ ስምና ዝና ደግሞ በመላዋ ጃፓን እጅግ ናኝቶ ነበር።

ሺንዞ አቤ ደግሞ መጠሪያ ስማቸው አቤ ነው።

‘አቤ’ በሰሜን ጃፓን ሆካይዶ ደሴት ውስጥ ከሚነገር ‘አይኑ’ ቋንቋ የተገኘ ስያሜ ነው።

አቤ በጃፓን ውስጥ የበርካታ ሰዎች መጠሪያ ስም ከመሆኑ በተጨማሪ ብዙ ቦታዎችም ይህንን ስያሜ ይጋራሉ።

በዚህም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከዝነኛው አበበ ቢቂላ ጋር ባላቸው የስም ምስስሎሽ ትምህርት ቤት መቆሚያ መቀመጫ አጡ። የክፍል ልጆች አስቸገሯቸው። አበበ እያሉም ይጠሯቸው ነበር።

በአበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ የቶኪዮ ማራቶንን ባሸነፈበት ወቅት እሳቸው ገና 10 ዓመታቸው ነበር።

ቢሆንም የአበበ ቢቂላ ድል ልክ ትናንት የሆነ ያህል ትዝ ይለኛል፣ ሲሉ ነበር ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት በመጡበት ጊዜ የተናገሩት።

በጉዟቸው አቤ የስመ ጥሩ ሞክሺያቸውን ፍቅር ለመግለጽ፣ የልጅነት ጊዜያቸው ጀግና ወደ ሆነው ሰው አገር ከመጡ አይቀር ቤተሰቡን እና አትሌቶችን አግኝተዋል።

የአበበ ቢቂላን የሙያ ልጆች ፈለጉ አስፈለጉ። ደራርቱን፣ ኢብራሂም ጀይላንን፣ ቲኪ ገላና እና መሰረት ደፋርን አገኙ ኤኤፍፒ በወቅቱ እንደዘገበው።

የአበበ ቢቂላ ልጅ የትናየት አበበም ለሺንዞ አቤ አባቱ ከ50 ዓመት በፊት ቶኪዮ ላይ ታሪክ ሰርቶ የመጨረሻውን የማራቶን መስመር በማለፍ ድል ያደረገበትን ጊዜ የሚያስታውስ ፎቶ በስጦታ አበረከተላቸው።

ሺንዞ አቤ አበበ ቢቂላ ቶኪዮ ላይ ሲያሸንፍ የነበረውን ሁኔታ እያስታወሱ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት አድናቆታቸውን ገልጸው ነበር።

“በርካታ ጃፓናውያን ተወዳዳሪዎች ሩጫውን ጨርሰው ተዘርረው ሲወድቁ፣ አበበ ግን ከባዱን ሩጫ ጨርሶ እዚው ሰውነቱን ያፍታታ ዱብ፣ ዱብ ይል ነበር” በማለት የ10 ዓመት ልጅ ሳሉ ያዩትን አበበን አስታውሰዋል።

አበበ ቢቂላ በኦሊምፒክ ታሪክ ስሙ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም በደማቁ የተጻፈ አትሌት ነው። በተጨማሪ ደግሞ ሺንዞ አቤን ጨምሮ አሁን ድረስ በበርካታ ጃፓናውያን የሚጠቀስ ኮከብ ሯጭ ነው።

የአቤ ግድያ እና የፈጠረው ድንጋጤ

ሐሙስ ዕለት የዓለም መገናኛ ብዙኃን በብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ላይ ዐይኑን ጥሎ ነበር። አርብ ዕለት ከማለዳው ጀምሮ ደግሞ ዓለም በሺንዞ አቤ በጥይት መመታት ከዚያም መሞት በእጅጉ ደንግጧል።

እሳቸው ሥልጣን በቃኝ ካሉ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ነገር ግን ለጃፓን የላይኛው ምክር ቤት የሚወዳደር ዕጩን ወክለው ቅስቀሳ እያደረጉ ነበር።

በኋላ ላይ የተመረመሩ ፎቶግራፎች እንዳሳዩት ተጠርጣሪው ገዳይ ከአቤ ኋላ በቅርብ ርቀት ቆሞ ንግግራቸውን ያዳምጥ ነበረ።

ከዚያም ከጀርባቸው አከታትሎ ተኮሰባቸው። በቀኝ በኩል አንገታቸውና ጀርባቸው ላይ በጥይት ተመቱ።

ተዝለፍልፈው ወደቁ። ደም ፈሰሳቸው። ሄሌኮፕተር ተጠራ። ሆስፒታል ገቡ። የጃፓን ስመጥር ሐኪሞች ነፍስ ለማዳን የቻሉትን ሁሉ አደረጉ። አልተሳካም።

እሳቸው ይቺን ምድር ሲሰናበቱ ገና 67 ዓመታቸው ነበር። ረጅም ዕድሜን ለሚኖሩት ጃፓኖች ይህ ዕድሜ በአጭር የመቀጨት ያህል ነው።

የጦር መሣሪያ ጥቃት እምብዛም ባልተለመደባት ጃፓን ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

ጃፓን ጥብቅ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ያለባት አገር ነች።

እንደ አሜሪካ ጃፓን ውስጥ የጦር መሣሪያ ከሱቅ እንደሸቀጥ እንደልብ አይገዛም።

በአውሮፓውያኑ 2014 አሜሪካ ውስጥ 33,599 የጦር መሣሪያ ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ ጃፓን ውስጥ ግን ስድስት ብቻ ነበረ።

መሣሪያ ለመታጠቅ የሚፈለግ ጃፓናዊ በመንግሥት የሚሰጥን ጥብቅ ፈተና እና የአእምሮ ጤና ምርመራን በብቃት ማለፍ ይጠበቅበታል።

ለዚህም በጃፓን የጦር መሣሪያ ፍቃድ ለማግኘት ከመሞከር መሣሪያ መፈብረክ ይቀላል።

ጃፓኖች ደግሞ ቁስ በማምረት ማን አህሏቸው፤ ከወዳደቀ ቁሳቁስም ቢሆን የጦር መሣሪያ ሊፈበርኩ ይችላሉ።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ገዳያቸው መሣሪያውን ቤቱ ውስጥ ራሱ ጠፍጥፎ እንደሰራው እየተዘገበ ነው።

ፖሊስ የአቤ ገዳይ ለምን ግድያውን እንደፈጸመና ለድርጊቱ ተባባሪ እንዳለው ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ነው።

ቤቱ ላይ በተደረገው ፍተሻም ከጦር መሳሪያ በተጨማሪ ፈንጂዎች መገኘታው ተነግሯል።

ሺንዞ አቤን በመግፈል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው ቴተሱያ ያማጋሚ የሚባል ሥራ አጥ የ41 ዓመት ጎልማሳ መሆኑን የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።

ያማጋሚ ጡረተኛውን ጠቅላይ ሚኒስርት ለመግደል ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከግምት በስተቀር የተነገረ ጉዳይ የለም።

ሺንዞ አቤ፣ የአበበ ቢቂላ አድናቂና ሞክሼ፣ 20 ሺህ ጃፓናውያንን የጨረሰውን ሱናሚ አልፈው፣ እንደ መሪ የሚደረገውን ሁሉ አድርገው በአንድ ግለሰብ በተተኮሰ ቤት ሠራሽ ጥይት ላይመሱ አሸልበዋል።

የፈሩት የአንጀት ቁስለት፣ ሥልጣን የለቀቁለት በሽታ ሳይገድላቸው፤ በቤት ሠራሽ ጥይት እስከወዲያኛው አሸልበዋል።

ዓለም በተለይም ጃፓናውያን በእጅጉ ደንግጠዋል፣ ግድያውን ተከትሎም “ዴሞክራሲ እንጂ ፖለቲካዊ ጥቃትን አንፈልግም” የሚል የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻን ከፍተዋል።