ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ጉብኝት በኤርትራ
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በኤርትራ መንግሥት ግብዣ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ዋና ከተማዋ አሥመራ ገብተዋል።
ለአራት ቀናት ጉብኝት ወደ ኤርትራ የተጓዙትን ሐሰን ሼክ ሞሐመድን በአሥመራ አውሮፕላን ማረፊያ የተቀበሏቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ አብረው ለመስራት የሶስትዮሽ ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ይታወቃል።
በተጨማሪም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ ወደ ኤርትራ ለሥልጠና ልከዋቸዋል በተባሉ አምስት ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች ዙሪያ በርካታ ጥያቄና ትችቶች ሲሰነዘሩባቸው ቆይቷል።
በቅርቡ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በሚያደርጉት ጉብኝት በኤርትራና በሶማሊያ ግንኙነት ዙሪያ፣ በአካባቢያዊ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብመስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ጨምረውም በፕሬዝዳንቱ የሚመራው የሶማሊያ ልዑካን በተለያዩ የኤርትራ ክፍሎች ጉብኝት በማድረግ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ሥራዎችን ይመለከታሉ ብለዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት ለሥልጠና ወደ ኤርትራ ተልከዋል የተባሉትን የሶማሊያ ወታደሮች በተመለከተ የወታደሮቹ ቤተሰቦችና የፋርማጆ ተቃዋሚዎች ሲወዛገቡ ቆይተዋል።
ባለፈው ግንቦት ወር ሶማሊያ ውስጥ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን የለቀቁት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ፣ ወታደሮቻቸው ኤርትራ ውስጥ ስለመኖራቸው በይፋ ከመናገር ተቆጥበው ቆይተው ነበር።
ነገር ግን ሥልጣናቸውን ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ባስረከቡበት ጊዜ 5 ሺህ ወታደሮች ለሥልጠና ወደ ኤርትራ መላካቸውንና ወደ አገራቸው ሳይመለሱ የቆዩት ሶማሊያ ውስጥ ሊከሰት የሚችልን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመከላከል ነው ሲሉ ለመጀመሪያ ጊዜ አምነዋል።
በምስጢር ተመልምለው ወደ ኤርትራ የተላኩት የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ቤተሰቦቻቸው ስላሉበት ሁኔታ ምንም እንደማያውቁ በመግለጽ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ግንቦት ወር በሶማሊያ ምርጫ ተካሂዶ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ፋርማጆ ሥልጣን ባስረከቡበት ጊዜ እንደተናገሩት፣ ወታደሮቹ አሁን ወደ አገራቸው ተመልሰው ከሠራዊቱ ጋር በመቀላቀል እስላማዊውን ታጣቂ ቡድን አልሻባብን በመዋጋቱ ዘመቻ ላይ ይሳተፋሉ ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፋ በጦርነቱ ከተሳተፈችው ኤርትራ ጎን የሶማሊያ ወታደሮች ተሳትፈዋል የሚል ክስ በተደጋጋሚ ሲሰማ ነበር።
ነገር ግን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የሶማሊያ ወታደሮች በትግራዩ ጦርነት ውስጥ ተሳትፈዋል የሚለውን ክስ ማስተባበላቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ለሁለተኛ ጊዜ ሶማሊያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የተመረጡት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ከተመረጡ ሁለት ወር ሳይሞላቸው ካደረጓቸው ጥቂት የውጭ አገራት ጉዞዎች መካከል የኤርትራው ከቀዳሚዎቹ ይጠቀሳል።
በዚህ ጉብኝታቸውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለሥልጠና ወደ ኤርትራ ስለላኳቸው የአገራቸው ወታደሮች ጉዳይና ወደ አገራቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ መነጋገር ዋነኛ አጀንዳቸው ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ የመጀመሪያውን ጉብኝት ያደረጉት ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ተጉዘው ነው።
አሁን ከቅዳሜ ጀምሮ በኤርትራ ለአራት ቀናት የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት በዚህኛው ዙር የሥልጣን ጊዜያቸው መጀመሪያ ላይ የሚካሄድ ሁለተኛው ይፋዊ ጉብኝት ይሆናል።