እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቁት የደቡብ አፍሪካ አጋቾች

በደቡብ አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠለፋና እገታ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ይህንንም አሃዝ በመመልከት በዓለም ላይ በጠለፋና በእገታ ቁንጮ ከሚባሉት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ኤምፎ ላካጄ ከጆሃንስበርግ ዘግቧል።

ሌሴጎ ታው ይህ ዕጣ ከገጠማቸው የጆሃንስበርግ ነዋሪዎች አንዷ ናት።

የዚያን ዕለት ሌሴጎ መኪናዋን ጆሃንስበርግ በሚገኝ አንድ የገበያ አዳራሽ ደጅ አቁማ ነበር።

በወቅቱ ዋና ትኩረቷ የነበረው በምሽቱ ለነበረው ዝግጅት የተወሰኑ ዕቃዎችን ከመሸመቷ በፊት ለጓደኛዋ መልዕክት መላክ ነበር።

በዚህ መሃል ግን ድንገት አንድ የማታውቀው ግለሰብ የግራጫ መርሴዲስ መኪናዋን የኋላ በር ከፍቶ ገባ።

መጀመሪያ ላይ አልደነገጠችም ነበር።

"በመኪናዬ ወደ ኋላ መመልከቻ መስታወት ግለሰቡን እየተመለከትኩት የተሳሳተ መኪና ውስጥ መግባቱን ሲያውቅ ምን ያህል ያሳፍረው ይሆን ስል እያሰብኩ ነበር" ትላለች በሰኔ ወር የተፈጠረውን ስታስብ።

ነገር ግን እንዳሰበችው ግለሰቡ ተሳስቶ አልነበረም መኪናዋ ውስጥ ዘው ብሎ የገባው።

"ድንገት ተፋጠጥን እና እየሆነ ያለው ነገር ተገለጸልኝ" ትላለች።

እገታ ነበር።

ከስድስት ወራት በፊት በንግድ ሥራ የሚተዳደረው ያሲን ብሂኩ ከመስጊድ ሲመለስ ጆሃንስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው ቤቱ አቅራቢያ ባለ መንገድ አካባቢ ታገተ።

በማኅበራዊ ሚዲያ በሰፊው የተጋራው የደኅንነት ካሜራ (ሲሲቲቪ) ቪዲዮ እንደሚያሳየው ሰማያዊ ሸሚዝና ጥቁር ሱሪ የለበሰው ያሲን ከጓደኛው ጋር ቆሞ እያወራ ነበር።

ከእነሱ በተቃራኒ ከቆመ መኪና ሁለት ሰዎች ሲወርዱ ይታያል። መጀመሪያ ላይ ቀስ ብለው እየተጠጉት ነበር፣ ነገር ግን ያሲን ምን እየተፈጠረ እንደሆነ በማወቁ ሊሸሽ ሲሞክር በፍጥነት ተከተሉት።

ግለሰቦቹን ማምለጥ ግን አልቻለም። በሽጉጥ አስገድደው ወደ ተሽከርካሪው እንዲገባ አደረጉት።

በኋላ ላይ ግን ነጋዴው ያሲን ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት ፖሊስ ታድጎታል።

በፕሪቶሪያ የራሷ የጽዳት ድርጅት ያላት ሌሴጎ ታውም ልትታገት እንደሆነ ስታውቅ ለመሸሽ ሞክራ ነበር።

የመኪናዋን በር ለመክፈት እንደሞከረች የምትናገረው ሌሴጎ፣ የፓርኪንግ አስተናጋጅ የደንብ ልብስ የለበሰ ሌላ ግለሰብ በሩን እንደዘጋባት ታስታውሳለች።

በዚህ ጊዜ ከኋላ ወንበር የተቀመጠው ግለሰብ ሽጉጥ እንዳለው አሳይቶ ሌሴጎ ከገበያ አዳራሹ እንድትወጣ አዘዛት።

እየሄዱ ሳለ መንገድ ላይ እንድትቆም ነግሯት ሌላ ግለሰብም ወደ መኪናዋ ዘልሎ ገባ።

የአራት ሰዓት ፈተና

አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል አስፈሪውን ጉዞ ተጉዘው ገጠር ከደረሱ በኋላ አጋቾቹ ሌሴጎ መኪናዋን እንድታቆም አዘዙ።

ቀይ መኪና ቦታው ላይ ከደረሰ በኋላ አንድ ግለሰብ ወርዶ የባንክ ካርዶቿን ወስዶ የይለፍ ቁጥሮቹን እንድትሰጠው አስገደዳት።

"በመኪናው ውስጥ ያሉት ሌሎች ሰዎች. . . ሁሉንም ካርዶቼን እያዩ ገንዘብ ማስተላለፍ ጀመሩ" ትላለች።

በተመሳሳይ አጋቾቿ በሽጉጥ ጭንቅላቷን ደጋግመው እየመቱዋት የሚተላለፈውን የገንዘብ መጠን እንድትጨምር ትዕዛዝ እየሰጧት ነበር።

መከራውም ከአራት ሰዓታት በላይ ዘለቀ።

በዚህም ወቅት ካሉት አጋቾች አንደኛው ጋር በስልክ እየተነጋገረ ያለ ሰው "ጨርሳት። ጨርሰናል" ሲል ሰማች።

"ሊገድሉኝ ነው ብዬ እርግጠኛ ሆንኩ፤ ነገር ግን መታገል እንዳለብኝ አሰብኩ። መታገል አለብኝ። ሊገድሉኝ ከሆነ እኔም ታግዬ ለመሞት አሰብኩ" ስትል ሌሴጎ የነበረውን ሁኔታ ታስረዳለች።

ታግላ ከመኪና ለመውጣት ብትችልም አጋቾቿ ይዘው ይደበድቧት ነበር። በመጨረሻም የሞትና የሕይወት ትግል አድርጋ አምልጣ ወደ ዋናው መንገድ መሮጥ ጀመረች።

ይህ የሌሴጎም ሆነ የያሲን የእገታ ታሪክ የሁለት ሰዎች ብቻ አይደለም።

የፖሊስ ሚኒስትሩ ብሄኪ ሴሌ በአውሮፓውያኑ 2021 የመጨረሻዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 2 ሺህ 605 ጠለፋዎችና እገታዎች ለባለሥልጣናት ሪፖርት መደረጉን ገልጸዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥም በደቡብ አፍሪካ እገታና ጠለፋ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።

በአሁኑ ወቅት ከ100,000 ሰዎች 10 ሰዎች እንደሚታገቱ የደቡብ አፍሪካ የጥበቃ ጥናት ተቋም አስታውቋል።

ይህ በዓለም ላይ ካሉት የእገታ አሃዞች ከፍተኛው ነው።

የፖሊስ ሚኒስትሩ በአውሮፓውያኑ 2018 ጠለፋና እገታዎች ማስቆም ቅድሚያ የሚሰጡት ተግባር መሆኑን ቃል ገብተው ነበር።

ከባንክ ሂሳብ ብር ለመውሰድ አሊያም ወሲባዊ ጥቃት ለመፈፀም ሲሉ አጋቾች በሚፈጽሙት እገታ ተጎጂዎች ያለ ፈቃዳቸው እንዲቆዩ ተገደዋል።

አንዳንዶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ሆኖም በዚህ ወንጀል የምን ያህል ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና ድርጊቱ ምን ያህል ተደጋጋሚ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ፖሊስ እነዚህን መሰል ወንጀሎች ለመቋቋም ባደረገው ሙከራ የመረጃ መሰብሰብን ከስልታዊ ምላሽ ጋር በማጣመር የጠለፋ ግብረ ኃይል አቋቁሟል።

ደቡብ አፍሪካን ኢላማ ያደረገው የወንጀለኞች ቡድን

እስካሁን ከተደረጉ ጠለፋዎች የታየው አጋቾች በቡድን ሆነው የመንቀሳቀስ አዝማሚያ እንዳላቸው እና እያንዳንዱ የወሮበሎች ቡድን አባል የራሱ የሆነ ሚናን እንደሚከተል የፖሊስ ቃል አቀባዩ ኮሎኔል አትሌንዳ ማቲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እነዚህን ታጋቾች ኢላማ የሚያደርጉትን የሚመርጡ አሉ። ከዚያም የተመረጡትን ግለሰቦች የሚያግቱና የሚጠልፉ አሉ" ይላሉ።

አጋቾቹ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ተሽከርካሪዎች የሚያሽከረክሩ ሲሆን የታጠቁ ናቸው።

"የተጠለፉትን ወይም የታገቱትን የሚወስዱት ጠባቂዎችም አሉ። ይህም ካሳ እስኪከፈል ድረስ ይቆያል" ብለዋል።

ከበስተጀርባ ግን ጠለቅ ያለ ምርምር የሚያደርግ እና ነገሮችን የሚያቀነባብር ዋነኛ ሰው ወይም ቡድን አለ።

"ከእነዚህ ጠለፋዎች ጀርባ ከፍተኛ ሃብት ያላቸው እና በእነዚህ ጥቃቅን ሥራዎች የማይሳተፉ ሰዎች አሉ" በማለት ኮሎኔል ማቲ ይናገራሉ።

እነዚህ የወንጀል ቡድኖች እንደ ሞዛምቢክ ካሉ ጎረቤት አገራት እስከ ፓኪስታን ድረስ ባሉ አገሮች ውስጥ ሰንሰለቶች አሏቸው።

አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ብር መክፈል የሚችሉ ሀብታም ነጋዴዎችን ኢላማ ያደርጋሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ ተጎጂዎች ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አካባቢዎች የመጡ ሲሆን ህጻናትም ይገኙበታል።

የግል ታጋቾች ተደራዳሪ ጌራርድ ላቡሻኝ፣ በጣም ከፍ ያለ ገንዘብ የሚጠየቅባቸው የእገታ ተግባራት መጨመራቸውን ይናገራሉ። አንዳንድ ጊዜም እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር ይጠየቃል ይላሉ።

"በሞዛምቢክ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት የሚንቀሳቀሱ የተደራጁ ቡድኖችም ደቡብ አፍሪካ ለዚህ ዓይነት ወንጀል በጣም ምቹ እንደሆነች ይቆጥሯታል። ተግባራቸውንም በተሳካ ሁኔታ እየፈጸሙ ይገኛሉ" ይላሉ ጌራርድ ላቡሻኝ።

አንዳንድ ማኅበራዊ ተንታኞች በአጠቃላይ በደቡብ አፍሪካ የሰፈነው ሕገ-ወጥነት አገሪቷን በዓለም ዙሪያ ለተደራጁ ወንጀለኞች ተመራጭ አድርጓታል ብለው ያምናሉ።

ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ቁጣ ማሰማቱን ተከትሎ ፖሊስ ብዙ ሥራ መስራት እንዳለበት ቢያውቅም ኮሎኔል ማቴ መሻሻል እንደታየ እምነት አላቸው።

"እነዚህ የወንጀለኛ ቡድኖች ከታወቁ ጀምሮ ከፓኪስታን፣ ከሞዛምቢክ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ የተውጣጡ 115 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል" ይላሉ።

ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የ43 ዓመቱ ፋይዝል ቻርለስ በመጋቢት ወር በቁጥጥር ሥር ውሏል።

በቅርቡ የነበሩ እገታዎችንና ጠለፋዎችን ያቀነባበረው እሱ እንደሆነ ይታመናል።

ፖሊሶች ከእሱ ጋር በተገናኙ በበርካታ የጆሃንስበርግ አካባቢዎች ባደረገው ፍተሻ አደንዛዥ እፅ፣ ገንዘብ እና ከፍተኛ ጉልበት ያለው መኪና ተገኝቷል።

ፋይዝል ቻርለስ በቅርቡ ከሌሎች በርካታ ሰዎች ጋር በጠለፋ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን ምንም አስተያየት አልሰጠም።

ግለሰቡ የደቡብ አፍሪካ እና ሞዛምቢክ ጥምር ዜግነት እንዳለውም ታውቋል።

"ፖሊስ ተጎጂዎችን አያድንም"

ፖሊስ በሚያዝያ ወር በጆሃንስበርግ ከሚገኝ ትምህርት ቤት አሳዳጊ መስላ ከጠለፈቻት ሴት የአራት ዓመቷን ሕጻን ታድጓታል።

ጠላፊዎቿ ሕጻኗ በሰላም እንድትመለስ ከተፈለገ ቤተሰቦቿ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር እንዲከፍሉ ጠይቀዋል።

ነገር ግን አራት ግለሰቦች ይህንን የጠየቁትን ገንዘብ ለመውሰድ ከአንድ የገበያ ማዕከል ውጪ ሲደርሱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ምንም እንኳን እንደዚህ ዓይነት ጥሩ ዜናዎች ቢሰሙም፣ ላቡሻኝ ግን ፖሊስ ከወንጀለኞቹ አንጻር እያሸነፈ አይደለም ይላሉ።

"አንድ ወይም ሁለት ሰው በቁጥጥር ሥር ውለናል፤ ነገር ግን በአብዛኞቹ ጠለፋዎች ላይ ፖሊስ የታገቱትን ተጎጂዎች አይታደጋቸውም። ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ ይለቀቃሉ" ይላሉ።

ሌሴጎ ለማምለጥ በመቻሏ እድለኛ ነበረች፤ ነገር ግን አጋቾቿ 1 ሺህ 400 ዶላር ወስደዋል።

ሁኔታው ሥነ ልቦናዋን ከመጉዳቱ በተጨማሪ ቤተሰቧን ጭንቀት ውስጥ ጥሎታል።

"አባቴ የሚያለቅስ ዓይነት ሰው አይደለም፤ ነገር ግን በእንባ ነው የተሞላው። ልጠብቅሽ ይገባኝ ነበር ብሎ ያምናል" ትላለች።

"በእውነቱ የዚያ ቀን የሆነ ነገሬ የሞተ መስሎ ነበር የተሰማኝ፤ ያ ስሜት እስካሁንም ድረስ አለ" በማለት የደረሰባትን ተናግራለች።