በሕንድ አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ወደ 270 ከፍ አለ

በአደጋው የሞቱ ሰዎችን ለመዘከር ሻማ ይዘው በምሽት የተሰበሰቡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሟቾች ላይ የደረሰውን አደጋ ለመዘከር የተዘጋጁ ስነ ስርዓቶች በሕንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም ተከናውነዋል

ሐሙስ ዕለት በሕንድ አህመዳባድ ከተማ የአውሮፕላን አደጋ በደረሰበት ስፍራ የተገኙ አስከሬኖች ብዛት 270 መድረሱን ሐኪሞች ተናገሩ።

ወደ ለንደን ለመጓዝ የተነሳው አውሮፕላን 242 ተጓዦች እና የበረራ ሠራተኞችን ይዞ በመኖሪያ ስፍራ አካባቢ የተከሰከሰው በረራውን ከጀመረ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው።

በአደጋው፣ ከአንድ የ40 ዓመት ብሪታኒያዊ ግለሰብ በቀር ሁሉም የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ባለስልጣናት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ለማረጋገጥ በስፍራው ላይ የሚገኙ ሲሆን አዝጋሚ የሆነውን የዘረመል ናሙናን ከተጎጂዎች ማንነት ጋር እያዛመዱ የማረጋገጥ ተግባር ማከናወን ቀጥለዋል።

ሟቾች ላይ የደረሰውን አደጋ ለማስታወስ የተዘጋጁ ስነ ስርዓቶች በሕንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም ተከናውነዋል።

እሁድ ዕለት በለንደን የሚገኘው የሕንድ ከፍተኛ ኮሚሽን ደጃፍ ላይ 100 ገደማ ሰዎች ተሰብስበው ሻማ በማብራት በአደጋው የሞቱትን ሰዎች ዘክረዋል።

አንድ የማኅበረሰብ መሪ፤ የወዳጆቻቸውን አስከሬን ለመለየት ወደ ሕንድ የተጓዙ እና በሆስፒታል ሆነው የዘረመል ምርመራ ውጤትን እየተጠባበቁ ያሉ ሰዎችን ማነጋገሩን ገልጿል።

ሟቾቹን ለማሰብ የተሰበሰቡት በርካታ ሰዎች አደጋው እንዴት እና ለምን እንደደረሰ መልስ ማግኘት እንደሚሹም የማኅበረሰብ መሪው ተናግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአደጋውን ምክንያት የሚደረገውን ምርመራ የሚመራው የሕንድ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ሲሆን የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም ቡድኖች እገዛ ያደርጉለታል።

አርብ ዕለት የአውሮፕላኑ የበረራ መረጃዎች የሚመዘገቡበት "ብላክ ቦክስ" እንደተገኘ ይፋ ተደርጓል።

የሕንድ ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትር ራም ሞሃን ናኢዱ ኪንጃራፑ፤ የአውሮፕላኑ "ብላክ ቦክስ" መገኘት አደጋውን "ለሚደረገው ምርመራ ትልቅ እገዛ" እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ በአህመዳባድ ከሚገኘውን ሳርዳር ቫላባይ ፓቴል ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ በተነሳ በ60 ሴኮንዶች ውስጥ የበረራ ከፍታውን በመሳቱ፤ "ቢጄ ሜዲካል ኮሌጅ ኤንድ ሲቪል ሆስፒታል" በተባለ የሕክምና ተቋም ሕንጻ ላይ ተከስክሷል።

የኮሌጁ የጀማሪ ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሃቫል ጋሜቲ፤ ሆስፒታሉ የ270 ተጎጂዎችን አስከሬን መቀበሉን ቅዳሜ ዕለት አረጋግጠዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 241 ያህሉ የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች እና የበረራ ሠራተኞች ናቸው ተብሎ ይታመናል። ከ30 በላይ ተጎጂዎች ቤተሰቦቻቸው ባቀረቡት ናሙና የዘረመል ምርመራ ተካሂዶ ማንነታቸው ተረጋግጧል።

የበረራ መረጃ መከታተያ ድረ ገጽ የሆነው የፍላይትራዳር24 መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የተከሰከሰው ቦይንግ ድሪምላይነር 787-8 አውሮፕላን የ11 ዓመት እድሜ ያለው እና ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከአህመዳባድ ወደ ለንደን ጋትዊክ 25 በረራዎችን ያከናወነ ነው።

የሕንድ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ተቋም የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክቶሬት፤ በሌሎች የኤር ኢንዲያ ቦይንግ 787-8 እና 787-9 አውሮፕላኖች ላይ "የመከላከል እርምጃ" ሲል የገለጸውን ተጨማሪ የደህንነት ምርመራ እንዲካሄድ አዝዟል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አርብ ዕለት ወደ አደጋው ስፍራ ተጉዘው ለ20 ደቂቃ ገደማ አካባቢውን ቃኝተዋል።

ብቸኛውን በሕይወት የተረፈ ተሳፋሪ ቪሽዋሽኩማር ራምሽን ጨምሮ ሌሎች ተጎዱ ሰዎችን በሆስፒታል ተገኝተው ጎብኝተዋል።

"መላው አገር በቶሎ እንዲያገግሙ ጸሎት እያደረገ ነው" ብለዋል።