ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ ታጣቂ ፓሪስ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ቆሰሉ
በፈረናሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ማዕከላዊ ክፍል አንድ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ሌሎች ሦስት ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው።
ጥቃቱን የሰነዘረው ግለሰብ ኢላማ ያደረገው የኩርዶች ባህል ማዕከልን ሲሆን፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ነው ተኩስ የከፈተው።
የዘረኝነት ጥቃት ሊሆን እንደሚችል የታመነው ይህ ክስተት ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል።
ጥቃቱን ያደረሰው የ69 ዓመት ግለሰብ ከዚህ ቀደም ታስሮ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ ነነበር ከእስር የተለቀቀው።
ሦስት ሰዎች የተገደሉበትን ክስተት ተከትሎ በፖሊስ እና ጥቃቱ በተፈጸመበት አከባቢ በተሰባሰቡ ሰዎች መካከል ግጭት ተቀስቅሷል።
በዚህም ተቃዋሚዎች መሃል መንገድ ላይ እሳት ሲያቀጣጥሉ እና የመኪና መስታወቶችን ሲሰባበሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ላይ በምላሹ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ሲተከሱ ታይተዋል።
የዐይን ምስክሮች እንዳሉት ይህ ግጭት የተቀሰቀሰው ረጅም፣ ነጭ አዛውንት ግለሰብ በፓሪስ አንድ ጎዳና ላይ በከፈተው ተኩስ ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት መግደሉ ከተሰማ በኋላ ነው።
ከተጎዱት ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ለሕይወት በሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ የተቀሩት ሁለት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ተጎድተው ህክምና እየተከታተሉ ነው።
ጥቃቱ የተሰነዘረበት ዓላማ ምን እንደሆነ የተረጋገጥ ምክንያት ባይስጥም፣ የፓሪስ ዐቃቤ ሕግ ላውሩ ቤኩ፣ ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም የዝረኝነት ጥቃት በመፈጸም ክስ ተመስርቶበት እንደነበር ተናግረዋል።
ግለሰቡ ከሁለት ዓመታት በፊት በፓሪስ የስደተኞች ማዕከል ውስጥ በስለት ጥቃት ፈጽሞ ነበር። ነገር በቅርቡ ከእስር ለምን እንደተለቀቀ ግልጽ አይደለም ተብሏል።
ቀደም ብሎ ጥቃት የተፈጸመበትን ስፍራ የጎበኙት የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ግሪአልድ ዳርማይን ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ከ“ጽንፈኛ ቀኝ አክራሪዎች” ጋር ያለው ግንኙነት አሁን ላይ አልታወቀም ብለዋል።
የከተማዋ ከንቲባ አሌክስአንድራ ኮርዴባርድ ጥቃት አድራሹ በክስተቱ መሃል እንደቆሰለ ገልጸው፣ የኩርዶች ማኅበረሰብ ማዕከል፣ ምግብ እና ፀጉር ቤቶች ጥቃት የደረሰባቸው ቦታዎች ናቸው ብለዋል።
በስፍራው የነበረ አሊ ዳሌክ የተባለ የዐይን እማኝ ለቢቢሲ ሲናገር “መንገዱ ላይ እየተጓዝን ነበር የተኩስ ድምጽ የሰማነው። ስንዞር ሰዎች ወደ ግራና ቀኝ ሲሮጡ አየን” ሲል ተናግሯል።
“ከአምስት፣ ስድስት ደቂቃ በኋላ በፀጉር ቤት ውስጥ የምናውቃቸው ሰዎች ስለነበረ ወደዚያው ሄድን። እዚያ ሰውዬውን ሲያስሩት ተመልክተናል” ሲል አክሏል።
ለፈረሳይ የዜና ወኪል አስተያየቷን የሰጠች ሌላ ግለሰብ ደግሞ የምትሰራበትን ሱቅ ከውስጥ እንደቆለፈችው የተናገረች ሲሆን፣ ሰባት ወይም 8 ጊዜ የተኩስ ድምጽ መስማቷን ገልጻለች።
ፖሊስ ግለሰቡን ያለምንም ግብግብ በቁጥጥር ስር ያዋለው ሲሆን፣ ጥቃቱ ተፈጸመበት መሳሪያም መግኘቱን አመላክቷል። ዐቃቤ ሕግ ደግሞ የግድያ ምርመራ መክፈቱን ገልጿል።
ጥቃት የደረሰበትን ማዕከል የሚያስተዳድረው እና በፈረንሳይ የሚገኘው የኩርዲሽ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ባወጣው አጭር መግለጫ ድርጊቱን ኮንኖታል።
'ለሞንድ' የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ፣ የማዕከሉን ቃል አቀባይ ጠቅሶ እንደዘገበው የፈረንሳይ ባለሥልጣናት በፓሪስ የሚገኙ ኩርዶችን ሕይወት በድጋሚ ለመጠበቅ አልቻለም ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፓሪስ ከተማ የሚገኘው የኩርዶች ማዕከል “የአስቃቂ ጥቃት” ሰለባ መሆኑን ገልጸው ፖሊስ ለፈጸመው ተግባር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ጥቃት ከመፈጸሙ ከ10 ዓመታት በፊት በፓሪስ የኩርድ ታጣቂዎች ብሔራዊ ፓርቲ ተባባሪ መስራችን ጨምሮ ሦስት የኩርድ ሴት አክቲቪስቶች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል።
ይህንንም ተከትሎ አንድ ቱርካዊ የግድያ ክስ ተመስርቶበት የነበረ ቢሆንም፣ የፍርድ ሂደቱ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ግለሰቡ እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ሕይወቱ አልፏል። .
በፈረንሳይ የሚገኘው የኩርዲሽ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በመግለጫው ላይ ይህንን ክስተት ያስታወሰ ሲሆን ትላንት የተፈጸመው ጥቃር “ሦስት የኩዲሽ አባላት የተገደሉበትን 10ኛ ዓመት ልናከብር ጥቂት ሲቀረን የተፈጸመ ነው” ብሏል።
እስካሁን በሁለቱ ክስተቶች መካከል ስላለው ግንኙነት በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ዛሬ ጠዋት የፓሪስ ፖሊስ ኃላፊ እና የኩርዶች ማኅበረስብ መሪዎች እንደሚገናኙም መግለጫው ጠቅሷል።