ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ምክንያቱ የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ችግር መሆኑ ተገለጸ

ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-ማክስ 8 አደጋ ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ችግር መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለ157 ሰዎች ህልፈት የሆነው የበረራ ቁጥር ኢቲ 302ን አደጋ አስመልክቶ ሚኒስቴሩ ሲካሄድ የነበረው ምርመራ የማጠቃለያ ሪፖርቱን ዛሬ ታኅሣሥ 14/2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው ይህንን ያሳወቀው።

በሪፖርቱም መሠረት ለአውሮፕላኑ አደጋ ምክንያት ቦይንግ የገጠመው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም” የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር እንደሆነም ተገልጿል።

አደጋ የደረሰበት የኢቲ 302 በረራ አውሮፕላን ከቦሌ አየር ማረፊያ ተንደርድሮ ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ የተሳሳቱ መረጃዎች ወደ በረራው መቆጣጠሪያ ሥርዓት በመላክ አፍንጫው የመድፈቅ ችግር ስላጋጠመው ለመቆጣጠር አልተቻለም ተብሏል።

አውሮፕላኑ ሳይታዘዝ አፍንጫውን የመድፈቅ ችግር እንዳጋጠመው እና አብራሪዎቹም መቆጣጠር ባለመቻላቸው መከስከሱ ከዚህ ቀደም በወጣ ሪፖርት ተገልጾ ነበር።

ቦይንግ 737-ማክስ 8 በገጠመው ኤምካስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር ምክንያትም አደጋው ለመፈጠሩ መንስዔ መሆኑንም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የምርመራ ሪፖርቱ የበረራ ቡድን አባላቱ ብቃት ማሳየታቸውን እንዲሁም የታደሰ ፍቃድ ነበራቸው ብለዋል።

በተጨማሪም አውሮፕላኑ በአየር ላይ ለመብረር በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንደነበርና ሕጋዊ ማረጋገጫም እንደነበረው መረጋገጡም ተገልጿል። የአውሮፕላኑ ክብደትና እና ሚዛንም በተፈቀደው ልክ ነበር ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም ቦይንግ አደጋው የተከሰተው ኤምካስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር መሆኑንና የተሳሳቱ መረጀዎችን በመስጠቱ አደጋው መከሰቱ ተገልጿል።

ቦይንግ 737- ማክስ 8ን አምርቶ ካወጣ በኋላ የኤምካስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር መገጠሙ በምስጢር እንደተያዘ እና ለአብራሪዎችም በሥልጠና ማኑዋሎች ላይ እንዳልተካተተ መገለጹ ይታወሳል።

የኢንዶኔዥያ ላየን ኤር አውሮፕላን አደጋ መድረሱም ተከትሎ ኤምካስ መገጠሙ ይፋ እንደተደረገና የኢትዮጵያ አብራሪዎችም አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለውን በቦይንግ የተሰጠውን መመሪያ መከተላቸው ተገልጿል።

ነገር ግን ይህም ሆኖ አውሮፕላኑን በተደጋጋሚ ለመቆጣጠር ቢሞክሩም ሳይታዘዝ ቀርቶ ወደ ምድር አሽቆልቁሎ እንደተከሰሰ ተገልጿል።

ቦይንግ 737- ማክስ- 8 ለሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች ምክንያትና ለበርካታ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ተከትሎ በዓለም ላይ ያሉ አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ እግድ መጣሉ ይታወሳል።

በቦይንግ አስፈላጊው ማስተካካያ ተደርጎ ተገቢው ምርመራ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ አውሮፕላኑ ወደ አገልግሎት መመለሱን ገልጿል።

የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ አውሮፕላን ማሪፊያ ወደ ኬንያ ለማቅናት በተነሳ በስድስት ደቂቃ ውስጥ ተከስክሶ ከ35 አገራት ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች ሕይወት መቅጠፍ ምክንያት ሆኗል።

ባለፈው ዓመት የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ እና ለሟቾች ቤተሰብ ከፍተኛ መጠን ያለው ካሳ ለመክፈል መስማማቱ ይታወሳል።