የሚድሮክ ለገ ደንቢ የማዕድን ማውጫ እንዲዘጋ ሂዩማን ራይትስ ዋች ጠየቀ

የ6 ዓመቱ ታዳጊ ከለገ ደንቢ ማዕድን ማውጫ አቅራቢያ ሲወለድ የቀኝ እርግ መዳፉ እና የግራ እግሩ ሦስት ጣቶቹ አጥንት የላቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Tom Gardner

የምስሉ መግለጫ, የ6 ዓመቱ ታዳጊ ከለገ ደንቢ ማዕድን ማውጫ አቅራቢያ ሲወለድ የቀኝ እርግ መዳፉ እና የግራ እግሩ ሦስት ጣቶቹ አጥንት የላቸውም።

በነዋሪዎች ላይ ከባድ የጤና ጉዳት እያስከተለ ነው ያለው የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ማዕድን ማውጫ ስፍራ በአስቸኳይ እንዲዘጋ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ሂማን ራይትስ ዋች ጠየቀ።

ሚድሮክ በለገ ደንቢ የማዕድን ማውጫ ሰፍራ አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ላይ የማዕድን ማውጣት ሥራው ከፍተኛ የጤና ጉዳት ቢያደርስም፣ ኩባንያው ለዓመታት ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ አለመወሰዱን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ለገ ደንቢ ተብሎ በሚጠራው የማዕድን ማውጫ ሰፍራ አካል ጉዳተኛ ሆነው የሚወለዱ ሕጻናት መኖራቸውን ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ማዕድን ማውጫ በአካባቢ ነዋሪዎች ላይ ለረዥም ጊዜ የቆየ ጤና ችግር ስለማድረሱ ቢቢሲ ከዚህ ቀደም በሠራው ዘገባም ተመልክቶ ነበር።

ማዕድን ማውጫ ስፍራው ተቃውሞችን ተከትሎ ከዓመታት በፊት ተዝግቶ የነበረ ቢሆንም፣ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ኩባንያው ዳግም ከመንግሥት ፍቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ መመለሱን የሂዩማን ራይትስ ዋች ጥናት አሳይቷል።

የማዕድን ማውጣት ሥራው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ማስከተሉን ቢገለጽም፤ ብክለትን የሚያስቀር ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ ሳይወሰድ ኩባንያው ሥራውን ዳግም ጀምሯል ብሏል ሪፖርቱ።

ከአምስት ዓመት በፊት የተከናወነ ጥናት ነዋሪዎች መርዛማ ለሆኑ ነጥረ ነገሮች መጋለጣቸውን አሳይቷል። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት መርዛማ ነጥረ ነገሮች ለአካባቢው ነዋሪዎች አደጋ መሆኑ መቅረቱ እስከሚረጋገጥ ድረስ ፍቃድ አልሰጥም ብሎ ነበር።

ይሁን እንጂ ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ ሳይወሰድ ኩባንያው ኅዳር 2013 ዓ.ም. ዳግም ሥራ መጀመሩ በሳተላይ ምስል ጭምር ማረጋገጡን ሂማን ራይትስ ዋች አመልክቷል።

ለተጎጂዎች ካሳ ይከፈል

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ መንግሥት ሚድሮክ በለገ ደንቢ የማዕድን ማውጫ ስፍራ ሥራ እንዲጀምር ዳግም መፍቀዱ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን መሠረታዊ መብትን የሚጋፋ ነው ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዋች ባልደረባ ጁሊያን ከፔንበርግ ተናግረዋል።

ጁሊያን ማዕድን ስፍራው በአስቸኳይ እንዲዘጋ እና ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፈል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፈር እና በውሃ ውስጥ ከሚፈደቀው መጠን በላይ መርዛማ ነጥረ ነገሮች አለመኖራቸውን በማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የመብት ድርጅቱ ጠይቋል።

በተጨማሪም ሚድሮክ እና ከሚድሮክ ወርቅ ተቀባይ የሆነው የስዊትዘርላንዱ አርጎር-ሄሮዮስ ኩባንያ ተጎጂዎች ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ መክፈል አለባቸው ብሏል።

እአአ 2018 ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ጥናት በአካባቢው ውሃ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው አርሴኒክ የተባለ መርዛማ ንጥረ ነገር እንዳለ አረጋግጧል።

በአካባቢው ከሚገኝ አፈር የተወሰዱ ናሙናዎች ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያላቸው አርሴኒክ፣ ኒክል እና ክሮሚየም የተባሉ መርዛማ ንጥረ ነገሮች ተገኝተውባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሕረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የካሄደው ጥናትም በለገ ደምቢ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከማዕድን ማውጫ ስፍራው በሚወጡ አደገኛ ለሆኑ መርዛማ ነጥረ ነገሮች ተጋላጭ እንደሆኑ አሳይቷል።

በኢትዮጵያ ግዙፍ ከሆኑ ቀዳሚ የማዕድን የግል ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ይህን የማዕድን ስፍራ እአአ 1997 ላይ ከመንግሥት ተርክቧል።

ከሚድሮክ ወርቅ የሚረከበው እውቁ የስዊትዘርላንድ ኩባንያ አርጎር-ሄሮዮስ፤ የማዕድን ማውጫው በአካባቢው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከተረዳሁ በኋላ ከሚድሮክ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ከአምስት ዓመታት በፊት አቋርጫለሁ ሲል ለሂዩማን ራይትስ ዋች መልስ ሰጥቷል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ግን ከሂዩማን ራይትስ ዎችም ሆነ ከቢቢሲ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።