ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔትፍሊክስ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ደንበኞቹን አጣ
ለአመታት ያህል ፊልሞችን በበይነ መረብ በማሳየት ከፍተኛ የዝና ማማ ላይ የደረሰው ኔትፍሊክስ ከባድ ፈተና ገጥሞታል።
አገልግሎቱን የሚያቋርጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ከሚያዝያ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ባለውም 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞቹን አጥቷል።
ነገር ግን ኩባንያው ከዚህም በላይ ደንበኞች አጣለሁ የሚል ስጋት ስለነበረው እንደተፈራው አይደለም ብሏል።
የበለጠ ቁጥር ያላቸው ደንበኞች አገልግሎቱን እንዳያቋርጡ ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የተጠየቁት የኔትፍሊክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሬድ ሄስቲንግስ ‘ስትሬንጀር ቲንግስ’ የተሰኘው ተከታታይ ፊልም ቀጣይ ክፍል መውጣት እንደሆነ ተናግረዋል።
በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው ‘ስትሬንጀር ቲንግስ’ ስኬትን የተጎናጸፈ ሲሆን አዲስ ክፍል መውጣቱም የደንበኞቹን ፍልሰት ለማስቆም እንደረዳ ይታመናል።
የኩባንያው ደንበኞች ቁጥር እየቀነሰ የመጣው ከአውሮፓውያኑ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ቁጥር ቀንሷል።
ተፎካካሪዎቹ የበላይነቱን እየተፈታተኑት ሲሆን ያደረገው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ ጫና አሳርፎበታል።
በያዝነውሳምንት ማክሰኞ የተመዘገበው የደንበኞች መቀነስ በኩባንያው ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው ሲሆን በዋነኝነት አገልግሎታቸውን ያቋረጡ ደንበኞች በአሜሪካ እና በካናዳ ሲሆን በመቀጠልም አውሮፓ ትከተላለች።
በአምፒር አናሊይሲስ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ጋይ ቢሰን ኔትፍሊክስ በገበያው ላይ ያለው ቁጥጥርን ማጣቱ አይቀሬ ነው ይላሉ።
"በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ስትሆን መሄድ ያለብህ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነው፣ በተለይ ከፍተኛ ተወዳዳሪዎች በመጡበት ባለፉት ሁለት አመታት የተፈጠረው ይህ ነው” ብለዋል።
በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች መዝናኛን በአዲስ መልክ በማሳየት አብዮት ያመጣው ኔትፍሊክስ ለዓመታት የማይገታ የሚመስል እድገት ላይ የነበረ ቢሆንም አሁን ያ ሁኔታ ተቀይሯል።
በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት በአውሮፓውያኑ 2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የበላይነት አጠናክሮ የነበረ ሲሆን በተለይም በርካቶች በቤት ውስጥ በተወሰኑበት ሁኔታ እና የመዝናኛ አማራጮች በጠፉበት ወቅት እንደ ስኩዊድ ጌም እና ዘ ክራውን የተሰኙ አይረሴ ተከታታይ ፊልሞችን ማቅረብ ችሏል።