ኔትፍሊክስ በአስከፊ የስራ ሁኔታ ክስ ቀረበበት

በኔትፍሊክስ ላይ የሚተላለፈው የላቭ ኢዝ ብላይንድ ተከታታይ ሪያሊቲ ሾው ላይ የሚወዳደር አንድ ግለሰብ ድርጅቱ መሰረታዊ የአስሪ እና ሰራተኛ ሕጎችን ጥሷል ሲል በፍርድ ቤት ክስ መሰረተ።

ጄረሚ ሃርትዌል የተሰኘው የዚህ ሾው ተወዳዳሪ አዘጋጆቹ ተዋናዮቹ አልኮል እንዲጠጡ እንደሚያበረታቱ እና ምግብእና ውሃ ማግኘት ግን እንደሚከለክሉ ብሎም ዝቅተኛ ክፍያ እንደሚከፈላቸው ተናግሯል።

ትዕይንቱን ለኔትፍሊክስ የሚቀርጸው ኪኔቲክ ኮንቴንት የሃርትዌልን ውንጀላ “ፍፁም ይዘት የሌለው’’ ሲል ለቫራይቲ አጣጥሏል።

የተቋሙ ቃለ አቀባይ “ክሶቹን አጥብቀን እንከላከላለን” ሲሉም ተናግረዋል።

በሎስአንጀለስ የካሊፎርኒያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ኔትፍሊክስን እና ኪኔቲክ ኮንቴንትን ብሎም የተዋንያን ምልመላ የሚያካሂደውን ተቋም ተከሳሽ አድርጎ አቅርቧል።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎቹ በውድድሩ ላይ ካሉት ፍቅረኞቻቸው ጋር ቢገናኙም መተያየት ግን አይችሉም። ይልቁንም በድምጽ ማጉያዎች ብቻ ይነጋገራሉ።

የሚጣመሩት እጩዎቹ ፊት ለፊት ለመገናኛት መተጫጨት አለባቸው።አንዳንድ ጥንዶች መጨረሻ ላይ ሲጋቡ እንዲሁም ሲፋቱ ይታያሉ።

ከሳሹ ሃርትዌል በሳምንቱ መጨረሻ ለሲኤንኤን በሰጠው ቃለ ምልልስለረጅም ሰዓታት በጠንካራ መብራት ስር ሲቀረጹ እንደሚቆዩ እና ይህንን ተከትሎ እንቅልፍ እንደሚያጡም ተናሯል።

ተዋናዮቹ “በስራ ላይ ሳሉ በመደበኛነት ምግብ እና ውሃ እንደማያገኙ’’ ክሱ እንደሚያሳይ ፒፕል ዘግቧል። "በሆቴሉ የመኖሪያ ክፍሎች ውስጥ ምግብ በመከልከሉ እስከ ከፋ ረሃብ ደርሰናል’’ ሲልም ክሱ እንደሚያስነብብ አክሏል።

ግለሰቡ ያልተከፈለውን ደሞዝ ብሎም ላመለጡት የምግብ ብሎም መደበኛ የእረፍት ጊዜያት የገንዘብ ማካካሻ ጠይቋል።

ፍትሃዊ ባልሆኑ የንግድ ተግባራትን ተከትሎ ለደረሰ ጉዳትም ያልተገለፀ የገንዘብ ኪሳራ እንዲሁም የአሰሪ ሰራተኛ ሕግ በመጣሱ የፍትሐ ብሔር ክስ በመመስረት ካሳ እንደሚጠይቅም አስታውቋል።

አሰሪው ኪኔቲክ እንደገለጸው ግለሰቡ በትወናው ከአንድ ሳምንት ያነሰ ግዜ መቆየቱን ብሎም ‘’ከተሳታፊዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር አቅቶት ነበር’’ ሲልም ምላሽ ሰጥቷል።

ተከታታይ የሪያሊቲ ትዕይንቱ ለኤሜ ሽልማት መታጨቱ ያለፈው ሳምንት ነበር ይፋ የተደረገው።