አሜሪካ እና ሩሲያ በሚያደርጉት የሰላም ንግግር ዩክሬን አለመጋበዟን አንድ ምንጭ ተናገሩ

የዪክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካ እና ሩሲያ በሚያደርጉት የሰላም ንግግር አገራቸው አለመጋበዟን የዩክሬን መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑ አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዩክሬን የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ኬይት ኬሎግ ሰኞ በሳዑዲ አረቢያ በሚደረገው ንግግር ዩክሬን ትሳተፋለች ቢሉም ምንጩ ምንም አይነት ልዑካን እንደማይገኙ ገልጸዋል።

የአውሮፓ መሪዎችም የሰላም ንግግሩ ላይ እንዲሳተፉ ያልተጋበዙ ሲሆን በምትኩ ዛሬ፣ሰኞ፣ ፓሪስ ውስጥ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት በአስቸኳይ ባዘጋጁት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የሚገኙ ይሆናል። አህጉሪቱ ከሰላም ንግግሩ ውጪ ተደርጋለች የሚለው ስጋት እየጨመረ ይገኛል።

እነዚህ የተናጠል ስብሰባዎች እየተካሄዱ ያሉት አሜሪካ የዩክሬንን ጦርነት አስመልክቶ ስር ነቀል የሚባል እርምጃዎችን እየተከተለች ነው በተባለ ማግስት ነው።

የዋይት ሃውስ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የዩክሬንን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት አሜሪካ እና ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት በሚያደርጉት ንግግር ላይ ለመገኘት እሁድ አመሻሽ ላይ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መጓዛቸውን አረጋግጠዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ እለት እንዳስታወቁት ልዩ መልዕክተኛው ከፑቲን ጋር "ዘለግ ላለ ጊዜ፣ ሶስት ሰዓታት ተገናኝተው መነጋገራቸውን" ገልጸዋል።

ቢሊየነር፣ የሪል እስቴት አልሚ እና የትራምፕ ጓደኛ የሆኑት ዊትኮፍ ዕጸ ፋርስ በመያዛቸው ታስረው የነበሩ አሜሪካዊ መምህርን ለማስፈታት በዚህ ሳምንት በሞስኮ ተገኝተው ነበር።

ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የስልክ ጥሪ ካደረጉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትስ በሳዑዲ አረቢያ ከሩሲያ ተደራዳሪዎች ጋር ሊገናኙ ነው።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በትራምፕ እና በፑቲን የተደረገው የስልክ ጥሪ በሁለቱ አገራት መካካል ለሦስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት ያስጀመረ ነው።

አሜሪካ እና ሩሲያ የሚያቀርቡትን ማንኛውም የሰላም ስምምነት አገራቸው ካልተሳተፈችበት እንደማይቀበሉ የዪክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከዚህ ቀደም አስጠንቅቀዋል።

ዘለንስኪ ለአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንቢሲ እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ "ዩክሬንን አስመልክቶ በአሜሪካ እና በዩክሬን መካከል የተደረሰ ውሳኔ በፍጹም፣ጭራሽ በፍጹም አንቀበልም" ብለዋል።

ዊትኮፍ በበኩላቸው የአሜሪካ ባለስልጣናት ከዩክሬን ባለስልጣናት ጋር በተናጥል እየተነጋገሩ እንደሆነ እንዲሁም ዩክሬን "የውይይቱ አካል" እንደሆነች አስረድተዋል። ነገር ግን የዩክሬን ልዑካን በሳዑዲ አረቢያ ይገኛሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ምንንም አስተያየት አልሰጡም።

ትራምፕ በፍሎሪዳ በሚገኘው ፓልም ቢች መኖሪያቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዘለንስኪ በውይይቱ ላይ ይሳተፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸው እንዴት ይሳተፋሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የአውሮፓ አገራት ለዩክሬን የሚሆን የጦር መሳሪያ ከአሜሪካ እንዲገዙ እንደሚፈቅዱም ተናግረዋል።