የቱርክ ፓርላማ ስዊድን የኔቶ አባል እንድትሆን ድጋፉን ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ በቱርክ ፓርላማ አባለት ድጋፍ አገኘ።
ስዊድን እአአ በ2022 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል።
ስዊድን ለኩርድ ተገንጣዮች ድጋፍ ትሰጣለች በሚል ቱርክ ኅበረቱን የመቀላቀል ጥያቄዋን አዘግይታው ቆይታለች።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን በቀናት ውስጥ ውሳኔውን በፊርማቸው ያረጋግጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በኋላ ለስዊድን አባልነት ጥያቄ ምላሽ ያልሰጠች ብቸኛ የኔቶ አባል አገር ሃንጋሪ ትሆናለች።
የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር ኡልፍ ክሪስተርሰን በማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ “የኔቶ ሙሉ አባል ለመሆን የሚቀረን አንድ እርምጃ ነው” ብለዋል።
የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ የቱርክን ውሳኔ በደስታ ተቀብለው ሃንጋሪ በፍጥነት አዎንታዊ ምላሿን እንድትሰጥ ጠይቀዋል።
ሃንጋሪ ጠብ አጫሪ የሆነ አመለካከት አላት በማለት ስዊድንን ትከሳለች።
ስቶክሆልም በበኩሏ የሃንጋሪ መንግሥት የአውሮፓ ኅብረት ዲሞክራሲያዊ መርሆችን ወደ ኋላ አስቀርታለች ስትል ከሳለች።
የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ማክሰኞ ዕለት የስዊድን አቻቸውን በቡዳፔስት ለውይይት ጋብዘዋል። “የተጠናከረ ውይይት መተማመንን ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብለዋል።
የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቶቢያ ቢልስትሮም ከሃንጋሪ ጋር የሚያደራድረን "ምንም ምክንያት" የለም ብለዋል። ነገር ግን ሁለቱ አገራት "መነጋገር እና በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ መወያየታቸውን መቀጠል ይችላሉ" ሲሉ ገልጸዋል።
ቱርክ ከስዊድን ጋር ባለፈው ሐምሌ ከስምምነት እስክትደርስ ድረስ የስቶክሆልምን ጥያቄ ውድቅ አድርጋ ቆይታለች። ማክሰኞ ዕለት የአገሪቱ ሕግ አውጭዎች የስዊድን አባልነት 287 ለ 55 በሆነ ድምጽ ደግፈዋል። ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ሕጉን ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ስዊድን ለኩርድ ታጣቂዎች ከለላ እየሰጠች ነው ስትል ቱርክ ትከሳለች። በአሸባሪነት የፈረጀችውን እንደ ኩርዲስታን የሠራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ያሉ አማፂ ቡድኖችን ለመመከት የበለጠ መሥራት አለባትም ብላለች። የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካም ፒኬኬን በአሸባሪነት ፈርጀውታል።
እንደ 31ዱም የኔቶ አባል አገር ቱርክ አዳዲስ አገራት ወደ ቡድኑ እንዳይቀላቀሉ የማገድ ስልጣን አላት።
ስዊድን በሰኔ ወር ጠንከር ያለ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ አውጥታለች። አዲሱ ሕግ ለአሸባሪ ቡድኖች የገንዘብ እና የሎጂስቲክስ እርዳታ መስጠትን ህገወጥ አድርጎታል።
ስዊድን እና ጎረቤቷ ፊንላንድ በወታደራዊ መስክ ገለልተኛ ሆነው ቆይተዋል። ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ከበርካታ ወራት በኋላ ሁለቱም ኔቶን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል። ፊንላንድ በሚያዝያ ወር ኔቶን በይፋ ተቀላቅላለች። በዚህም ምክንያት ህብረቱ ከሩሲያ ጋር የሚጋራው ድንበር በእጥፍ ጨምሯል።












