ዶናልድ ትራምፕ በኒው ሐምፕሻየር ግዛት ድል ቀናቸው

ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ

ለአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመሆን በሚደረገው ትንቅንቅ ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ማክሰኞ በድጋሚ ድል ቀንቷቸዋል። ተፎካካሪያቸው አምባሳደር ኒኪ ሔሊ “እጅ አልሰጥም’’ ብለዋል።

ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት 70 ከመቶ ድምጽ የተቆጠረ ሲሆን ትራምፕ በከፍተኛ ድምጽ ኒኪ ሄሊን እየመሩ ነው። የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ድሉ የትራምፕ እንደሆነ ትንቢቱን አስቀምጧል።

ዶናልድ ትራምፕ በማክሰኞው የፓርቲ ምርጫ ሲያሸንፉ ከአዮዋ ቀጥሎ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ውድድሮች በኔቫዳ እና ሳውዝ ካሮላይና ግዛቶች ይደረጋሉ።

በተለይም በሳውዝ ካሮላይና ግዛት የሚደረገው ፉክክር ወሳኝ ይሆናል። ምክንያቱም ኒኪ ሔሊ የቀድሞ የግዛቱ አስተዳዳሪ ነበሩ።

ብቸኛዋ ሴት ተፎካካሪ ኒኪ በሳውዝ ካሮላይና የሚያገኙት ድምጽ ደካማ ሆነው የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው የመቀጠል ተስፋቸው ሊጨልም ይችላል።

የፍሎሪዳው ገዢ ዲ ሳንተስ ከሰሞኑ በበቃኝ ከምርጫው መውጣታቸው አይዘነጋም።

ዲ ሳንተስ ቀደም ባሉት ዓመታት ከትራምፕ የበለጠ ድጋፍ የነበራቸውና ምናልባትም ቀጣይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ተስፋ የተጣለባቸው ነበሩ።

ሆኖም በጊዜ ሂደት የድጋፍ መሠረታቸው ተሸርሽሮ የትራምፕ ደጋፊዎች አይለው መውጣታቸው ውድድሩን ባልተጠበቀ ፍጥነት እንዲያቋርጡ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

ሮን ዲ ሳንተስ በአዮዋ ከትራምፕ ቀጥሎ 2ኛውን ደረጃ ማግኘታቸው ያልተጠበቀ እና አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ምክንያቱም ሁለተኛ ሆነው ይጨርሳሉ ተብሎ ግምት የተሰጣቸው ኒኪ ሄሊ ስለነበሩ ነው።

ሆኖም ዲ ሳንተስ ‘ሩጫዬን ጨርሻለሁ’ የሚል የቪዲዮ መልዕክት ከኒው ሐምፕሻየር ውድድር ቀደም ብሎ አስተላልፈዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአዮዋ ግዛት የ23ሺ ሰዎችን ድምጽ ያገኙት ዲ ሳንተስ በግዛቱ ለምርጫ ቅስቀሳ ብቻ ያወጡት ገንዘብ 53 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ይህም ከፍተኛ ወጪ ሆኖ ተመዝግቧል።

ዲ ሳንተስ ከውድድሩ ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ደጋፊዎቻቸው ድምጻቸውን ለትራምፕ እንዲሰጡ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ ዲ ሳንተስን በማብጠልጠል ወራትን ያሳለፉ ሲሆን፣ አገረ ገዢው ከምርጫው ወጥተው ደጋፊዎቻቸው ድምጻቸውን ለትራምፕ እንዲሰጡ ከተናገሩ በኋላ ግን ‘ባለ ብሩህ አእምሮ’ ሲሉ አንቆለጳጵሰዋቸዋል።

እሳቸው ብቻ ሳይሆን የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመሆን ውድድር ውስጥ ገብተው የነበሩት ወጣቱ ቢሊየነር ቪቪክ ራምስዋሚ እና ብቸኛው ጥቁር ዕጩ የሆኑት የሳውዝ ካሮላይናው ሴናተር ቲም ስኮት ድጋፋቸውን ለትራምፕ ሰጥተዋል።

ከሰዓታት በፊት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ የቀድሞ ተቀናቃኞቻቸው (አሁን ሁሉም ደጋፊዎቻቸው ሆነዋል) ተከበው ባደረጉት ንግግር ብቸኛዋን ሴት ዕጩ ኒኪ ሄሊን ከፍ ዝቅ አድርገው ዘልፈዋቸዋል።

“ይቺ ሴትዮ ምንድነው የምታወራው? እንዳሸነፈ ሰው ነው የሚያደርጋት፣ ከንቱ’’ ብለዋታል።

ይህ ሳያንስ፣ ‘ሶሻል ትሩዝ’ በሚባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ሰሌዳቸው ላይ ኒኪ “ቀዥባራ ሴትዮ” ሲሉ ዘልፈዋቸዋል።

ኒኪ ሄሊ በበኩላቸው የኒው ሐምሻየርን ውጤት በፀጋ እንደሚቀበሉ ተናግረው፤ ትራምፕን እንኳን ደስ አለዎ ካሉ በኋላ “ነገር ግን እጅ አልሰጥም-ገና ምኑ ተነካና” የሚል ንግግር አድርገዋል።

“እኔ በቀላሉ እጅ የምሰጥ ሰው አይደለሁም፤ ኒው ሐምፕሻየር መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይሆንም” ብለዋል ለደጋፊዎቻቸው።

በኒው ሐምፕሻየር ምርጫ እስከአሁን ትራምፕ 12 ውክልና (ዴሊጌት) ሲያገኙ፣ ኒኪ ማግኘት የቻሉት ግን 9 ብቻ ነው። ኒው ሐምፕሻየር ግዛት ጠቅላላ ያለው የወኪል (ዴሊጌት) ብዛት 22 ነው።

አንድ የሪፐብሊካን ዕጩ ፓርቲውን ወክሎ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ከሁሉም ግዛቶች በድምሩ 1215 ወኪል ድምጽ ማግኘት አለበት።

ዶናልድ ትራምፕ በድል ማግስት ኒው ሐምፕሻየር ላይ ባደረጉት ንግግር እንደተለመደው ጆ ባይደንን አንጓጠዋል።

“ሁለት ዓረፍተ ነገር አሰካክቶ መጨረስ የማይችል የጃጀ ሽማግሌ” ሲሉ የ81 ዓመቱን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን አፊዘውባቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከጆ ባይደን በዕድሜ የሚያንሱት በአራት ዓመት ብቻ ነው።