ደቡብ አፍሪካ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የማይልኩ ወላጆች እስር ይጠብቃቸዋል አለች

ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የማይልኩ ወላጆችን ዘብጥያ እንዲወርዱ የሚፈቅድ ሕግ አረቀቀ።

ደቡብ አፍሪካ ያረቀቀችው አዲሱ የትምህርት ሕግ አንድ ተማሪ ትምህርት ቢያቋርጥ ወይም ተማሪው ዕድሜው ለትምህርት ደርሶ ትምህርት ቤት ካልገባ ወላጆች እስከ 12 ወራት በእስር እንዲቀጡ ያዛል።

ይህ አዲሱ ሕግ በትምህርት ቤቶች አካላዊ ቅጣቶችንም ይከለክላል።

ረቂቅ ሕጉ በአገሪቱ ፓርላማ አባላት በ223 ድጋፍ እና 83 ተቃውሞ ጸድቋል።

ደቡብ አፍሪካን እያስተዳደረው የሚገኘው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፓርቲ “ሕጉ አሁናዊ እና ታሪካዊ ፈተናዎችን በመሻር የትምህርት ስርዓቱን ያዘምናል” ብሏል።

ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ግን ፓርላማው ያጸደቀውን ሕግ ተችቷል።

እንደ ፓርቲው ከሆነ ይህ የሕግ አዋጅ መንግሥት በትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲኖሩት አድርጎ የትምህርት ሰርዓት እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።

የትምህርት ባለሙያዎች የደቡብ አፍሪካ የትምህርት ስርዓት ቀውስ ውስጥ ነው ያለው ይላሉ።

በደቡብ አፍሪካ ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም።

የአገሪቱ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በ2022 ባወጣው አሃዝ ላይ ዕድሜያቸው 15 ዓመት ከሆናቸው ተማሪዎች 3 በመቶ እንዲሁም ዕድሜያቸው 17 ከሆኑ 9 በመቶ ያክሉ እአአ 2021 ላይ ትምህርት አቋርጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሪዲንግ ሊትረሲ ስተዲ ዓለም አቀፍ ተቋም በሰራው ጥናት ለማንበብ የሚቸገሩ በርካታ ተማሪዎች ከሚገኙባቸው አገራት መካከል አንዷ ደቡብ አፍሪካ መሆኗን አሳይቶ ነበር።

በዚህ ዓመት የተደረገ ጥናት ዕድሜያቸው 10 ከሆኑ 10 ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎች 8 ያክሉ ለማንበብ ይቸገራሉ።