ማንቸስተር ዩናይትድ በርካታ ታዳሚዎች ያሉት ክለብ ሆኗል፤ አርሰናል እና ሲቲስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማንቸስተር ዩናይትድ በ2023 – 24 የውድድር ዘመን ከአውሮፓ ክለቦች በመላቅ በድምሩ ከፍተኛ ተመልካች ስታዲየም ገብቶ የተመለከተው ቡድን መሆኑን የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ይፋ አድርጓል።
ሐሙስ ይፋ በተደረገው በዚህ ሪፓርት መሠረት በሀገር ውስጥ ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድን 1 ሚሊዮን 397 ሺህ 138 ታዳሚዎች በሜዳው ተገኝተው ተመልክተውታል።
ባለፈው የውድድር ዘመን ዩናይትድ በታሪክ ዝቅተኛ በሆነ ውጤት ስምንተኛ ደረጃ ይዞ ቢያጠናቅቅም በተመልካች ቁጥር ግን ከአውሮፓ የሀገር ውስጥ ሊጎች ከየትኛውም ክለብ የላቀ ታዳሚ ያገኘ ቡድን መሆን ችሏል።
የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርቱመንድ ከእንግሊዝ፣ ስፔን እና ጣልያን ክለቦች በሁለት ጨዋታ ያነሰ የውድድር ዓመት ቢያሳልፍም በሜዳው በእያንዳንዱ ጨዋታ 81 ሺህ 305 ተመልካቾች በማግኘት በቡደስሊጋው ከፍተኛ ታዳሚ ያገኘ ሆኗል።
በሁሉም ውድድሮች ዶርቱመንድ 1 ሚሊዮን 951 ሺህ 745 ታዳሚዎች በማግኘት በአውሮፓ ከፍተኛ ተመልካች ያገኘ ቡድን ነው።
ባለ ጥቁርና ቢጫ ማሊያዎቹ ዶርቱመንዶች ይህንን ከፍተኛ ቁጥር ለማግኘት ባለፈው የውድድር ዘመን በሜዳቸው ያደረጓቸው 6 የሻምፒዮንስሊግ ዋንጫ ጨዋታዎች አግዘዋቸዋል።
ዶርቱመንድ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለፍጻሜ ቢደርስም በሪያል ማድሪድ ተሸንፎ ዋንጫውን ማጣቱ አይዘነጋም።
ዩናይትድ በሁሉም ውድድሮች ከፍተኛ ተመልካቾችን በማግኘት ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።
ዩናይትድን በሁሉም ውድድሮች 1 ሚሊዮን 834 ሺህ 291 ታደሚዎች የተመለከቱት ሲሆን የጣልያኑ ኤሲ ሚላን 1 ሚሊዮን 860 ሺህ 964 ተመልካች በማግኘት በአውሮፓ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
በአጠቃላይ በአውሮፓ 16 ክለቦች በሀገራቸው ሊጎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ታዳሚ አግኝተዋል። ይህም ዌስትሃም፣ ቶተንሃም፣ አርሰናል፣ ማንችስተር ሲትና ሊቨርፑልን ይጨምራል።
በሁሉም ሊጎች ከፍተኛ ውድድር በማግኘት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዟል።ይህንን ውድድር በአጠቃላይ 14.7 ሚሊዮን ተመልካች በአካል ታድሞታል።ይህ ቁጥር ከ2023 – 24 የውድድር ዓመት አንጻር 4 በመቶ ቀንሷል።
ባለፈው የውድድር ዘመን የስታዲየሞች የመያዝ አቅም 5 በመቶ ቀንሷል።
ባርሴሎና እና ሊዮን የተገናኙበት ጨዋታ በአውሮፓው ከፍተኛ ተመልካች የታደመበት 5ኛው ጨዋታ ሲሆን፣ 50 ሺህ 827 ታዳሚ አግኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማካይ በእያንዳንዱ ጨዋታ 23 ሺህ ተመልካቾች የነበረው የእንግሊዝ ሁለተኛ ሊግ የሆነው የሻምፒዮንሺፕ ውድድር ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ከፍተኛ ተመልካች በማግኘት 7ኛ ነው።
በሴቶች የሊግ ውድድር የተመልካች ቁጥር በድምሩ ወደ 2.6 ሚሊዮን ተመልካች ያደገ ሲሆን ይህም ከባለፈው የውድድር ዘመን በ38 በመቶ ያደገ ሆኗል።
በዚህ ውድድር የእንግሊዝ የሴት ቡድኖች ከፍተኛ ተመልካች በማግኘት ቀዳሚ ሆነዋል።
የአርሰናል የሴቶች ቡድን በሜዳዋ ባለፈው የውድድር ዓመት 329 ሺህ 986 ተመልካቾች ያገኘች ሲሆን ይህም ከየትኛውም የአውሮፓ ሊግ ከ200 ሺህ በላይ የሚልቅ ነው።
ማንችስተር ዩናይትድ፣ ባርሴሎና እና ቸልሲ ሌሎቹ የእንግሊዝ ከፍተኛ ተመልካች ያላቸው የሴቶች ቡድን ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ከ100 ሺህ በላይ ተመልካች ታድሟቸዋል።
የባርሴሎና የሴቶች ቡድን በሁሉም ውድድሮች ከፍተኛ ተመልካች ያገኘ የሴቶች ቡድን ሲሆን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከ100 ሺህ በላይ ታዳሚ ያገኘ ብቸኛው ቡድን ሆኗል።
የአውሮፓ ክለቦች አንደኛው የገቢ ምንጫቸው ከታዳሚዎች ቲኬት ሽያጭ የሚገኝ ነው።












