ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ግዛቷ በተከሰተው የጎሳ ግጭት 60 ሰዎች ተገደሉ

ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰነው የብሉ ናይል ግዛት በመሬት ይገባኝል ምክንያት በጎሳዎች መካከል በተነሳው የጎሳዎች ግጭት 60 ሰዎች መገደላቸውን የሱዳን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በበርቲ እና ሐውሳ ጎሳዎች መካከል ከአንድ ሳምንት በፊት በተቀሰቀሰው ግጭት ከተገደሉት በተጨማሪ በርካቶች ላይ ጉዳት በመድረሱ፣ በአካባቢው ያሉ ሆስፒታሎች ለደም ለጋሾች ጥሪ አቅርበዋል።

በተከሰተው የጎሳዎች ግጭት በርካታ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ መንግሥት ባለሥልጣናት ብሉ ናይል ግዛት ውስጥ የምሽት የሰዓት እላፊ ገደብ ጥለዋል።

ለበርካቶች ሞት ምክንያት በሆነውና በደቡብ ምሥራቅ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰነው የብሉ ናይል ግዛት ውስጥ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰተው ግጭት ለቀናት መቆየቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

ባለፈው ረቡዕ አንድ አርሶ አደር ከተገደለ በኋላ የተቀሰቀሰው ግጭት የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብተው በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው በፊት ወደ በርካታ አካባቢዎች መዛመቱን ከብሉ ናይል ግዛት አስተዳደር የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

አስተዳደሩ ጨምሮም በግጭቱ ምክንያት ከሞቱት ሰዎች ባሻገር ከ40 በላይ ሰዎች ሲቆስሉ 16 ሱቆች ወድመዋል። ይህንንም ተከትሎ በዳማዚን እና ሮሳይሪስ ከተሞች ውስጥ የምሽት የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል።

ነገር ግን ነዋሪዎች ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በጎሳዎች መካከል የተከሰተው ግጭት የፀጥታ ኃይሎች ባልተሰማሩባቸው በርካታ የግዛቲቱ አካባቢዎች ውስጥ ቅዳሜ ዕለትም ግጭቶች ቀጥለዋል ብለዋል።

የሱዳን ዶክተሮች ማኅበር በክስተቱ ዙሪያ ባወጣው መግለጫም ተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ዳማዚን እና ሮሳይሪስ ሆስፒታሎች ቅዳሜ ዕለት ጭምር ሲመጡ እንደነበር አመልክተዋል።

ማኅበሩ ጨምሮም ሆስፒታሎቹ በቂ የሕክምና መሳሪያ ስለሌላቸው የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲያቀርብና የተጎዱ ሰዎችን በአየር ወደ ሌላ ቦታ እንዲወሰዱ ጠይቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በአማጺ ቡድኖች መካከል አገር አቀፍ የሰላም ስምምነት ቢፈረምም ምሥራቃዊውን የባሕር ዳርቻ አካባቢንና ምዕራብ ዳርፉርን ጨምሮ በበርካታ የሱዳን ግዛቶች ውስጥ ተመሳሳይ ግጭቶች አልፎ አልፎ ሲከሰቱ ቆይተዋል።

ትናንሽ ተፎካካሪ አንጃዎች የሰላም ስምምነቱን ሲፈርሙ በደቡብ ኮርዶፋን እና አሁን ግጭት በተከሰተበት የብሉናይል ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው በአገሪቱ ኃያል የሚባለው የሰሜን ሱዳን ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ የተባለው አማጺ አንጃ ግን ስምምነቱን አልፈረመም።

አሁን ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግጭት በብሉ ናይል ግዛት ውስጥ በሚገኙት የሃውሳ እና የበርቲ ጎሳዎች መካከል በይዞታ ይገባኛል መካከል መሆኑን የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል።

በሱዳን ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በግዛቱ ግጭት ቆሞ መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ እያደረጉ ሲሆን፣ በጄኔራል አልቡርሐን የሚመራው ወታደራዊ አስተዳደር ግን አስካሁን ስለግጭቱ በይፋ ያለው ነገር የለም።

ባለፈው ጥቅምት ወር በሽግግር መንግሥቱ አስተዳደር ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ የፀጥታ ጥበቃ ክፍተት መፈጠሩን የጠቆመው ኤኤፍፒ፣ በዚህም ሳቢያ በመሬት ይገባኛል ሰበብ፣ በከብቶች፣ እነዲሁም በውሃና በግጦች ምክንያት ደም አፋሳሽ የሆኑ የጎሳዎች ግጭት ተስፋፍቷል ብሏል።

በጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የተመራው ወታደራዊ ኃይል በመፈንቅለ መንግሥት ከሽግግር አስተዳደሩ ሥልጣን ከነጠቀ በኋላ ላለፉት ስምንት ወራት ያልተቋረጠ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱበት ይገኛል።