ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳኑ ጄኔራል አል ቡርሐን ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለጹ
የሱዳን ጦር ኃይል አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ ለማድረግ ቦታውን እንደሚለቅ ወታደራዊው መሪ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ተናገሩ።
ጄነራሉ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በደረጉት ንግግር የአገሪቱ ጦር ኃይል ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ ለምታደርገው ሽግግር እንቅፋት እንደማይሆንና ምርጫ እንዲደረግ ወስኖ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጄኔራል አል ቡርሐን ጨምረውም በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማብቃት ከሲቪል ቡድኖች ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ጦር ሠራዊቱ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንደሚያቋርጥ አሳውቀዋል።
ነገር ግን አገሪቱ ውስጥ ምርጫ ስለሚደረግበት እንዲሁም ጦር ኃይሉ ሥልጣን ስለሚያስረክብበት ሂደት የጊዜ ሰሌዳ ምንም አላሉም።
በሱዳን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሰረት የሚጠይቁት ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሠራዊቱ ከፖለቲካው እንዲወጣ በመጠየቅ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይህ የአሁኑ የጄኔራሉ ውሳኔም ከሕዝቡ በገጠማቸው ተከታታይ ተቃውሞ የሰጡት ወሳኝ ምላሽ እንደሆነ ተነግሯል። በመላው አገሪቱ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ግዙፍ ሕዝባዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
የሽግግር መንግሥቱ አካል የነበሩት የሱዳን ጦር ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ባለፈው ጥቅምት ወር በሲቪሉ የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ፈጽመው ነበር ሥልጣን የተቆጣጠሩት።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ የሆኑት ጄኔራል አል ቡርሐን ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ በአገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ የተጀመረውን የሽግግር ሂደት በመቀልበስ መሪነቱን ጨብጠው ቆይተዋል።
ጄኔራል አል ቡርሐን ሠራዊቱ ከሚደረገው ድርድር ለመውጣት መወሰኑን ከማሳወቃቸው በፊት ባለሥልጣናት የተቃውሞ አንቀሳቃሽ ናቸው የተባሉ እና ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ የታሰሩ የታሰሩ 145 ሰዎችን ለቀዋል።
ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ ለወራት ያልተቆረጠ የተቃውሞ ሰለፎች ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል።
በዚህም ለተቃውሞ ሰልፍ ከወጡ ሱዳናውያን መካከል ከ100 የሚበልጡ ሰዎች ከጥቅምት ወር ወዲህ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የሱዳን ዶክተሮች ገልጸዋል።