ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን በተካሄደው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ሰልፍ 9 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆሰሉ
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲቋቋም ለመጠየቅ አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካቶች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ተናገሩ።
ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም በመላው አገሪቱ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ዘጠኝ ሰዎች እንደተገደሉና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዶክተሮች አሳውቀዋል።
ሱዳን ውስጥ ሕዝባዊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን በሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዳቸውን ተከትሎ ነው።
ትናንት ሐሙስ በተለይ በመላዋ አገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም ግዙፍ ሰልፎች ተካሂደዋል። እነዚህን ሰልፎች ለመበተን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ነው ተቃዋሚዎች የተገደሉት።
ተቃዋሚዎቹ ወታደራዊው መሪዎች ሥልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ መፈክሮችን ይዘው ወደ አደባባይ በመውጣት መንገዶችን መዝጋታቸው ተነግሯል።
የፀጥታ ኃይሎችም በተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ወሃ በመርጨት ለመበተን የሞከሩ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞች ካርቱም ውስጥ ወደ ሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤተመንግሥት እንዳያመሩ ለማገድ ጥይት መተኮሳቸው ተዘግቧል።
በዚህም ሳቢያ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ እዚያው ካርቱም ውስጥና በአቅራቢያ በምተገኘው ኦምዱርማን ከተማ ውስጥ በጥይት ቆስለው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
ከሐሙስ ጠዋት ጀምሮ ተቃዋሚዎች ስልክና ኢንተርኔትን ተጠቅመው ሰልፉን እንዳያስተባብሩ በሚል የሱዳን ባለሥልጣናት የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ አድርገዋል።
ሐሙስ ዕለት ሱዳን ውስጥ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በአገሪቱ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደበት ካለፈው ጥቅምት ወዲህ በእጅጉ በርካታ ሕዝብ የተሳተፈበት ግዙፍ እንደነበር የተለያዩ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
ሰልፉ የተዘጋጀው ከሦስት ዓመት በፊት አገሪቱን ለሰላሳ ዓመታት ያህል በፈላጭ ቆራጭነት የመሩትን ኦማር ሐሰን አልበሽርን በማስወገድ በወታደራዊና ሲቪል መሪዎች መካከል የሥልጣን ክፍፍል ያመጣውን ታላቁን የተቃውሞ ሰልፍ ለማሰብ ነው።
ሰልፈኞቹ በጄኔራል ቡርሐን የሚመራው ወታደራዊ መንግሥት ከአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እንዲወጣና ዴሞክራሲያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲመሰረት እየጠየቁ ነው።
የሱዳን ሕዝብ ከሦስት ዓመት በፊት አምባገናናዊውን አስተዳር በሕዝባዊ ተቃውሞ አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመስረት ያስችላል ብሎ የጠበቀው ለውጥ በወታደራዊ ኃይሉ በመቀልበሱ በተደጋጋሚ ቁጣውን ሲገልጽ ቆይቷል።
በአንድ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የተናገሩት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን፣ ሥልጣን በሕዝብ ለተመረጠ መንግሥት እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ተቃዋሚዎች በወታደራዊ መሪው ላይ እምነት ስለሌላቸው ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞቸውን በሚገልጹበት ወቅት በየጊዜው በርካታ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአገሪቱ ሐኪሞች አሳውቀዋል።
መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደበት ከጥቅምት ወር ወዲህ በተከታታይ በተደረጉ የተቃወሞ ሰልፎች ምክንያት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሱዳን ዶክተሮች ማኅበር ገልጿል።