በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶችን ማኅበራዊ ሚዲያው እያባባሰ ይሆን?

ከጥቂት ወራት በፊት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የተቀረጸና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል በርካቶችን አስደንግጧል።

ምስሉ ላይ አንድ በሕይወት ያለ ግለሰብ በዙሪያው ሰዎች በተሰበሰቡበት ከሚነድ እሳት ውስጥ ሲጨመርና ይህንን የሚያበራታቱ ንግግሮች ተሰምተዋል።

ይህ ቪዲዮ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በስፋት ከተዘዋወረ በኋላ በርካቶች ድርጊቱን ሲያወግዙና መንግሥት በፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ሲጠይቁ ነበር።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ጥቃቱ በእኔ ወገን ላይ ነው የተፈጸመው የሚሉ ሰዎች ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በግልጽ ለበቀል እርምጃ ጥሪ ሲያቀርቡ፣ ሌሎች ደግሞ ድርጊቱን በማደናነቅ "ጠላት" በሚሉት ወገን ላይ ተመሳሳዩ እንዲፈጸም ሲያበረታቱ ታይተዋል።

እንዲህ አይነቶቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘቶችና መልዕክቶች ጥቃትንና ጥላቻን በማስፋፋት የማኅበረሰቦችን ደኅንነት ከማናጋት ባሻገር ሥነ ልቦናዊ ጫናቸውም የከፋ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሰል አሰቃቂ ምስሎችን በፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ሚድያዎች መመልከት የየዕለት አጋጣሚ ሆኗል።

የአዲስ አበባው ነዋሪው ወንድሜነህ እንግዳ "ፌስቡክ መጠቀም ካቆምኩ ሁለት ወር አለፈኝ" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

"በቃ ስገባ የሚታየው ምስልና ጽሁፍ ስለግድያ እና ሞት ነው። በተጨማሪም በጥቃት ሰለባዎች ላይ የሚያላግጡ መልዕክቶችም በስፋት ይነበባል። ታዲያ ይሄ አእምሮዬን ይረብሸው ጀመር" ሲል ከማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ራሱን ያራቀበትን ምክንያት ያስታውሳል።

ስለዚህም "ተመልሼ ፌስቡክ የምጠቀም አይመስለኝም" ይላል።

ቢቢሲ በፌስቡክና ትዊተር እንዲሁም ቴሌግራም በተሰኘው የመልዕክት ማስተላለፊያ መድረክ ላይ የተመለከታቸው ቪድዮዎችና ምስሎች አሰቃቂ መሆናቸውን መታዘብ ችሏል።

እኚህ ምስሎች አንዳንድ ጊዜ በጥቃት አድራሾቹ አሊያም በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎች የተቀረጹ መሆናቸውን መናገር ይቻላል።

ፌስቡክ፣ትዊተርና ዩቲዩብ የራሳቸው መተዳደሪያ መርኅ ያላቸውና ቢሊዮኖች የሚጠቀሟቸው ማኅበራዊ ሚድያዎች ናቸው።

ታድያ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራጩ መሰል ቪድዮዎች፣ ሐሰተኛ መረጃዎችና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን መቆጣጠር ለምን ተሳናቸው?

ይህ ጥያቄ በርካቶችን ሐሳብ ውስጥ የከተተ ይመስላል።

ማኅበራዊ ሚዲያ የደቀነው አደጋ

የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ባላቸው ሰፊ ተደራሽነትና ተሳትፎ ሳብያ በጎምሆኑ አሉታዊ መልዕክቶች በቀላሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩና በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች ለማዳረስ ያስችላሉ።

ይህም በሰዎች ላይ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ይዘቶች በቁጥጥር አድራጊ አካላት ዕይታ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በርካቶች ዘንድ ስለሚደርሱ አሉታዊ ውጤታቸው በአጭር ጊዜው ውስጥ ሊታይ ይችላል።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሚንጣቸው አገራት ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያን ለአሉታዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እጅግ በርካታ ናቸው።

በዚህም በግለሰቦች፣ በማኅበረሰቦች እና በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለውን ግንኙነት በማበላሸት ለግጭትና ለጥቃት መሳሪያ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው።

በቅርቡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የተፈጸሙ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ተከትሎ፣ መረጋጋትና ከአደገኛ ድርጊቶች ሁሉም እንዲቆጠብ ከሚጠይቁት በላይ ግጭቶችን የሚያባብሱ ግለሰቦች በተለያዩ መድረኮች ላይ ተስተውለዋል።

አሰቃቂ ድርጊቶቹን በተመለከተ በተለያዩ ጎራዎች የተሰለፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጥቃቶችን ሲያበረታቱ አሊያም ለበቀል እርምጃ ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖለቲከኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን እያሳሰበ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ እሥር ቤት የቆዩት ታዋቂው ፖለቲከኛ፣ ጃዋር መሐመድ፣ ይህ ሁኔታ ካሳሰባቸው ዜጎች መካከል አንዱ ናቸው።

ፖለቲከኛው በአውሮፓና በአሜሪካ ከደጋፊዎቻቸው ጋር እያደረጓቸው ባሉት ውይይቶች ላይ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው መገዳደልን ከመስበክ እንዲቆጠቡ ሲጠይቁ ተደምጠዋል።

አቶ ጃዋር አክለው “ኦሮሞ እየሞተ ከሆነ፤ አማራ እየሞተ ከሆነ፤ ትግሬው እየሞተ ከሆነ፤ ጉሙዝ እየሞተ ከሆነ፤ ማነው እየገደለ ያለው? እየተገዳደልን ነው ማለት ነው” ይላሉ።

ፖለቲከኛው "እያለቁ ያሉት ምንም የማያውቁ ሕፃናትና እናቶች ናቸው" በማለትም በውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን በዩቲዩብ በኩል ለሚያገኙት ሳንቲም ሲሉ ሕዝቡን ለጥቃት ከማነሳሳት እንዲቆጠቡ መክረዋል።

የማኅበራዊ ሚድያው ተጠያቂነት

የኢትዮጵያሕዝብ ቁጥር 120 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ ይገመታል።

ከአጠቃላይየሕዝብ ብዛት 24 በመቶ ያክሉ ከ13 እስካ 24 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።

ዳታሪፖርታልየተሰኘው ድረ ገጽ ባወጣው መረጃ መሠረት 30 ሚሊዮን ገደማአገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ናቸው።

ይህቁጥር በየዓመቱ በፍጥነት እየተመነደገ ነው።

ድረ-ገጹ አክሎም በፈረንጆቹ 2022 የኢትዮጵያ በይነ መረብ መስፋፋት 25 በመቶ እንደሆነ ይገልጣል።

እንደሮይተርስ ያሉ የዜና ወኪሎችን ጨምሮ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በጥናት አስደግፈው ይፋ የሚያደርጉ ገፆች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው ማኅበራዊ ሚድያ ፌስቡክ እንደሆነ ይፅፋሉ።

ባለፈውየፈረንጆቹ ዓመት የወጡ ዘገባዎች በኢትዮጵያ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 7 ሚሊዮን አካባቢ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ፌስቡክኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን የሚያበረታቱ መልዕክቶችን መቆጣጠር አልቻለም የሚል ከባድ ወቀሳ ይደርስበታል።

የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት የፌስቡክ ሠራተኞች ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ተመልክተው ለበላዮቻቸው ቢያሳውቁም ድርጅቱ እርምጃ አልወሰደም የሚል ይፋዊ ክስ ቀርቦበታል።

ፌስቡክ፤ኢትዮጵያን የግጭት አደጋ ካንዣበባቸው የዓለማችን አገራት መካከል ቢመድባትም የድርጅቱ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች መቆጣጠሪያ ክንፍ የድርሻውን አልተወጣም በሚል ተደጋጋሚ ትችት ይሰነዘርበታል።

ዎልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ መስከረም 2014 ባስነበበው ጽሑፍመመ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች ጭካኔ የተሞላቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ያለከልካይ ፌስቡክ ላይ ሲለጥፉ ነበር ብሏል።

ሜታ ለተሰኘው የፌስቡክ ባለቤት ኩባንያ ይሠሩ የነበሩት ፍራንሲስ ሃውግን ፌስቡክ እንደ ኢትዮጵያና ምያንማር ያሉ አገራትን እያፈራረሰ ነው ሲሉ መረጃ ማሾለካቸው ይታወሳል።

ለማርክዙከርበርግ ድርጅት ይሠሩት የነበሩት መረጃ አጋላጯ በአሜሪካ ሴኔት ፊት ቀርበው ነው ይህን ያሉት።

ይህ ዜና በበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከተዘገበ በኋላ ፌስቡክ እርምጃ መውሰድ ጀምርያለሁ ብሎነበር።

ለምሳሌ ድርጅቱ በወርሃ ኅዳር በለቀቀው ዘገባ ከ92 ሺህ በላይ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ይዘቶች ላይ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል።

አልፎም ባለፈው ሚያዚያ “መቀመጫቸውን ግብፅ አድርገው 'ኢትዮጵያ ላይ አነጣጥረዋል'” ያላቸውን ገፆች መዝጋቱን ገልጦ ነበር።

ነገር ግን የፌስቡክ እርምጃ በቂ አይደለም፤ አሁንም በርካታ ተጠቃሚዎች ግጭት ቀስቃሽ መልዕክት ያለከልካይ እያስተላለፉ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ።

ማኅበራዊ ሚድያዎች እርምጃ የሚወስዱት እንዴት ነው?

ሜታ እንደ ፌስቡክና ኢንስታግራም ባሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ተጠቃሚዎች ጎጂ መልዕክት እንዳያስተላልፉ እንደሚሠራ ይገልጣል።

ድርጅቱ ይህን ሥራ ራሱ በቀጠራቸው ሠራተኞች ጨምሮ በአጋር ድርጅቶች አማካኝነት ያከናውናል።

መቀመጫውን በኬንያ መዲና ናይሮቢ ያደረገ ሳማ ሶርስ የተባለ ድርጅት በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የይዘት ቁጥጥር [content moderation] ያደርጋል።

ለዚህ ድርጅት የሚሠሩ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሠራተኛ በተለይ ከትግራይ ጦርነት በኋላ በፌስቡክ የሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮች ጨምረዋል ይላሉ።

"ቁጥጥር ከምናደርግበትይዘት 80 በመቶ የሚሆነው ግጭት ቀስቃሽ መልዕክትና የጥላቻ ንግግር ያዘለ መልዕክት ነው" ይላሉ።

ፌስቡክ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ይዘት ቁጥጥር የሚያደርጉለት ድርጅቶች ቢኖሩትም በሦስቱ ቋንቋዎች የሚሠራው ሳማ ይዘትን የመቆጣጠር አቅም እንደሌለው ይናገራሉ።

ፌስቡክ የይዘት ቁጥጥር የሚያደርገው ተጠቃሚዎች ‘ሪፖርት’ ሲያደርጉ እንደሆነ ይገልጣል።

በሌላ በኩል ተጠቃሚዎች ግጭት ቀስቃሽ መልዕክት እንዲለቁ ይፈቅዳል ተብሎ የሚወቀሰው በጉግል የሚተዳደረው ዩቲዩብ የተሰኘው የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋርያ ድር ነው።

በርካታ ተጠቃሚዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በዩቲዩብ ገፆች ሲያስተላልፉ ቢቢሲ መታዘብ ችሏል።

ዩቲዩብ ለዚህ ወቀሳ ምላሽ እንዲሰጥ ቢቢሲ ናይሮቢ ለሚገኘው የጉግል ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ቢደውልም መልስ ማግኘት አልቻለም።

መንግሥት ምን እየሠራ ነው?

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ለዚህጥያቄ ምላሽ አላቸው።

ዳይሬክተሩ፤ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ዲጂታል ማኅበረሰብ አባል እንደመሆንዋ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ከሚሠራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ማምለጥ አትችልም ይላሉ።

የኢንሳ ዳይሬክተር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚከሰቱ ግጭቶችና ለሚያደርሱት መፈናቀል እንዲሁም ለሰው ነፍስ መጥፋት የማኅበራዊ ሚድያው ሚና ቀላል አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።

"ይህ ኢትዮጵያን ያሰጋታል" የሚሉት ዳይሬክተሩ ይህንን ‘አደጋ’ ለመግታት መሥሪያ ቤታቸው እንቅስቃሴ እንደ ጀመረ ይገልጣሉ።

ምንም እንኳ መንግሥት በነፃነት ሐሳባቸውን የሚያቀርቡ ሰዎችን ድምጽ እያፈነ ነው ተብሎ ቢወቀስም፤ ኃላፊው መሥሪያ ቤታቸው ከዚህ በፊት ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ያሠራጩ ሰዎችን ለሕግ ማቅረቡን ያወሳሉ።

“ሐሰተኛ አካውንቶች ስለሚበዙ ማኅበራዊ ሚድያዎች በሚገዙበት መርኅ መሠረት እንዲዘጉ አሊያም እንዲታገዱ ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች [ፌስቡክና ጉግል] ጋር እንሠራለን" ይላሉ።

"ማኅበራዊ ሚድያውየሚከፍላቸው አሉ [ለምሳሌ ዩቲዩብ]። እነዚህ ሰዎች ስለትግሬ መራብ፣ ስለኦሮሞ መጎሳቆል፣ ስለ አማራ ሞት አይገዳቸውም። ሕዝቡን አጋጭተው ስለሚያገኙት ገንዘብ ነው የሚጨነቁት። ሕብረተሰቡ ይህን እንዲያውቅና በጥንቃቄ እንዲጠቀም እንመክራለን።"

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ማኅበራዊ የትስስር ድረ ገጾችን ለሐሰተኛ መረጃና ለጥላቻ ንግግር ማስተላለፊያነት የሚጠቀሙ ሰዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ ማውጣቷ የሚዘነጋ አይደለም።

በአዋጁ ከተካተቱ ሕግጋት መካከል የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ወይንም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎችን በመጠቀም ያስተላለፈ እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራትና በ100 ሺህ ብር ይቀጣል የሚል ይገኝበታል።

በተላለፈው የጥላቻ ንግግር ምክንያት በግለሰብ አሊያም በቡድን ላይ ጥቃት ከደረሰ አልፎም መረጃው ከ5 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት ገጽ ከተላለፈ ቅጣቱ እስከ 5 ዓመት ሊደርስ እንደሚችል አዋጁ ያትታል።

ብዙዎች ይህ ሕግ፣ መንግሥት የማኅበረሰብ አንቂዎችን ያለጥፋታቸው ወደ እሥር ቤት እንዲልክ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ይሰጋሉ።

መንግሥት በቅርቡ በአማራ ክልል በወሰደው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በርካታ ጋዜጠኞች እና የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ይታወሳል።

አቶ ሹመቴ በአዲሱ አዋጅ መሠረት ግጭት ቀስቃሽና የተሳሳቱ መረጃዎችን በፌስቡክ፣ በትዊተርና በዩቲዩብ የሚያሠራጩ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ይላሉ።

በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተማረችው ነገር ግን በሕግ ሙያ ላይ የተሰማራችው ወ/ሮ ነጻነት ወልደገብርኤል፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰራጩ መልዕክቶችና ምስሎች ከሚያሳስቧቸው መካከል ናት።

ለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ አደረጃጀትና ያለው የተካረረ ፖለቲካዊ አመለካከት ሰፊ ድርሻ እንዳለው በማንሳት "ፖለቲከኞች እንዲህ ያሉትን ጥላቻና ጥቃትን የሚያበረታቱ መልዕክቶች በይፋበመቃወምና በማውገዝ ሚና አላቸው" ትላለች።

አንዳንዶች መንግሥት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ ሲከፋም እንዲዘጋ የሚጠይቁ ቢኖሩም ወ/ሮ ነጻነት ግን፣ ከዚህ ይልቅ መድረኩን ለበጎ ተግባራት የሚጠቀሙትን በማበረታታት "ለክፋት የሚያውሉትን ማዳከም ይቻላል" በማለት ታስባለች።

ከራሷተሞክሮ በመነሳትም "ለአእምሯዊ ጤናዬ ስል ጥላቻንና ጥቃትን የሚያበረታቱ ገጾችንና ግለሰቦች አልከተልም፤ በእግረ መንገድ የሚያጋጥሙኝን ይዘቶችንም አልመለከትም" ብላለች።