ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ዲፕሎማቶቿን ከቱርክ ጠራች
እስራኤልና ቱርክ ከፍተኛ ወደሚባል የዲፕሎማሲ ፍጥጫ እየገቡ ነው።
ትናንት እስራኤል አምባሳደሯን ጨምሮ ሁሉም ዲፕሎማቶቿን ከቱርክ ጠርታለች።
ቴላቪቭ እርምጃውን የወሰደችው የቱርኩ ፕሬዝዳንት እስራኤልን ‘እንደ ጦር ወንጀለኛ እያደረጋት ነው’ ብለው መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ይህን ያሉት በኢስታንቡል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለፍልስጥኤም ያለውን አጋርነት ለመግለጽ አደባባይ በወጣበት ጊዜ ባደረጉት ንግግር ነው።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮሆን በቱርክ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ወደ ቴል አቪቭ እንዲመለሱ አዘዋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የእስራኤል ወታደሮችን በጋዛ እየፈጸሙ ያሉትን ነገር መተቸታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ ‘እስራኤል ያላት ሠራዊት ዓለም ላይ ካሉ ሠራዊቶች በሥነ ምግባር የታነጸው ነው’ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየሰነዘረች ባለችበት በዚህ ወቅት በመላው ዓለም ለፍልስጥኤም አጋርነታቸውን የሚገልጹ በርካታ የአደባባይ ሰልፎች እየተደረጉ ነው።
ሐማስ መብረቃዊ ጥቃት በመሰንዘር በደቡባዊ እስራኤል 1400 ሰዎችን ገድሎ 229 ሰዎችን ካገተ ከሦስት ሳምንት በኋላ እስራኤል ታንከኛ ሠራዊቷን ወደ ጋዛ አንቀሳቅሳለች።
በጋዛ ላይ የምታደርሰውን መጠነ ሰፊ ጥቃትም አጠናክራ ቀጥላለች። በዚህም በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር 7ሺህ 500 ፍልስጥኤማዊያን መገደላቸውን ገልጧል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፍልስጥኤም ደጋፊዎች በኢስታንቡል አደባባይ በተገኙበት ወቅት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ባደረጉት ንግግር ‘’በጋዛ ለሚደርሰው አሰቃቂ ግድያ ዋናው ተጠያቂ ምዕራባዊያን ናቸው’ ብለዋል።
ጨምረውም፣ “እስራኤል ለ22 ቀናት የጦር ወንጀል ስትፈጽም ነበር። ነገር ግን የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ሌላው ቀርቶ እስራኤል የጦር ማቆም ስምምነት እንኳ እንድታደርግ ለመጠየቅ አልደፈሩም። ” ሲሉ ከሰዋል።
ኤርዶዋን ከዚህም አልፈው እስራኤልን በጦር ወንጀለኝነት የከሰሱ ሲሆን "ፍልስጥኤማዊያንን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እየሞከረች ነው" ብለዋል።
“እርግጥ ነው ሁሉም አገር ራሱን የመከላከል መብት አለው። ነገር ግን የታል ፍትሕ፤ ፍትሕ የለም፤ የንጹሐን እልቂት ብቻ ነው በጋዛ እያየን ያለነው” ብለዋል ኤርዶዋን።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ከዚህ ንግግር ቀደም ብለው በኤክስ ሰለዴቻው “ንጹሐን በጋዛ እየተጨፈጨፉ ነው፤ ሁኔታው እየከረረ ነው፤ እስራኤል ይህን እብደት ማቆም አለባት” ብለው ጽፈው ነበር።
ኤርዶዋን ትናንት በአደባባይ እስራኤልን መክሰሳቸውን ተከትሎ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮህን በኤክስ ገጻቸው፣ “ከቱርክ በሰማነው ያልተገባ ንግግር የተነሳ ከአገሪቱ ጋር ያለንን ግንኙነት በድጋሚ ለማጤን ተገደናል፤ እዚያ የሚገኙ ዲፕሎማቶቻችንንም ጠርተናል።” ብለው ጽፈዋል።
ናታንያሁ የፕሬዝዳንት ኤርዶዋንን ክስ ተከትሎ "የኛ ሠራዊት በሥነ ምግባር የታነጸ ነው፤ ንጹሐንን ለመከላከል የሚቻለውን ጥንቃቄ እያደረግን ነው። ይልቅ ሐማስ ንጹሐንን ከለላ እያደረገ ወንጀል እየፈጸመ ነው” ብለዋል
ቱርክስ እስራኤል በታሪክ ዘለግ ላለ ጊዜ ያልጸና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው የነበራቸው።
በአንድ ወቅት ወዳጅ የነበሩት ሁለቱ አገሮች እንደ አውሮፓዊያኑ በ2010 ዓ/ም በተመሳሳይ ግንኙነታቸው ሻክሮ ነበር።
ምክንያቱ ደግሞ 10 የፍልስጥኤም ደጋፊዎች በእስራኤል ተጥሎ የነበረውን የሰብአዊ እርዳታ ክልከላ ቸል ብለው ረድኤር ለማድረስ ሲሞክሩ በእስራኤል ኮማንዶዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነበር።
ግንኙነታቸው በ2016 ዓ/ም ዳግም ተመልሶ ቆይቷል።
ይሁንና በድጋሚ በ2018 ዓ/ም እስራኤል በርካታ ፍልስጥኤማዊያንን በጋዛ ድንበር መግደሏን ከትሎ ግንኙነታችን አቋርጠዋል። አምባሳደሮቻቸውን ወደየአገሮቻቸው ጠርተው ነበር በወቅቱ።
ቱርክ ሐማስን አሸባሪ ድርጅት ብላ አልፈረጀችም። አሜሪካና ዩኬ ግን ድርጅቱን በአሸባሪነት ጽፈውታል።