እርዳታ ለማቅረብ 300 ተቀናቃኝ የታጠቁ ቡድኖችን ማናገር የሚያስፈልግባት አገር

ሄይቲ አስከ አፍንጫው በታጠቁ እና በጎራ በተከፋፈሉ ቡድኖች መናጥ ከጀመረች ሰነባብታለች።

ከአመጽ፣ ከሁከት እና ከታጠቁ የወሮበላ ቡድኖች ጋር ተያይዞ ስሟ እየተነሳ ይገኛል።

ለምሳሌ ያህል በአብዛኛው መዲናዋን የሚቆጣጠረው 'ጂ ናይን' የተባለው ታጣቂ የወሮበሎች ቡድን ነው።

መሪውም ጂሚ ቼሪዚየር ይሰኛል።

እርዳታ ለማድረስም በአገሪቷ እየተንቀሳቀሱ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተደራጁ ቡድኖችን ማናገር ግዴታ እንደሆነም የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታውቋል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሮበርት ማርዲኒ እንደተናገሩት በመቶዎች ከሚቆጠሩ የተደራጁ ቡድኖች ጋር በመቀናጀትም ነው እርዳታ መድረስ የሚችለው።

በሄይቲ ወደ 300 የሚጠጉ የተደራጁ የወሮበላ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ 80 በመቶው የሚሆኑት በዋና ከተማዋ ፖርት ኦ ፕሪንስ ይንቀሳቀሳሉ። በርካታ የአገሪቷን ግዛቶች የሚያስተዳድሩት እነዚህ ቡድኖች ናቸው።

የተደራጁ ቡድኖች በጎራ ተከፋፍለው በሚፈጠረው ሁከትም በርካታ የጤና ማዕከላት ሥራቸውን ለማቆም ተገደዋል።

የጤና ሠራተኞችም በርካታ ጊዜ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይገጥማቸዋል።

ዳይሬክተሩ በካሪቢያኗ አገር ሄይቲ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

“በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ባገለገልኩባቸው 27 ዓመታት ውስጥ ማኅበረሰብ በእንደዚህ ዓይነት መርዛማ እና በተደራረቡ አስከፊ ሁኔታዎች ሲኖር አላየሁም” ሲሉ ስለሁኔታው ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ጎዳናዋ በቆሻሻ ማስወገጃ ፍሳሽ የተጥለቀለቀችውን ሲቴ ሶሌይልን ከተማንም እንደ ማሳያ አድርገዋታል።

“የታጠቁ ቡድኖች የሚፈጽሙት ጥቃት መብዛቱን ተከትሎም በርካቶች መታገት እና ግጭት የየቀኑ ፍራቻቸው ሆኗል” ይላሉ።

በአገሪቱ ባለው የፀጥታ እጦት ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን፣ አብዛኛው ሕዝብም የጤና አገልግሎት በማያገኝበት ሁኔታም ለመኖር ተገዷል።

ዳይሬክተሩ በአንድ ክሊኒክ ውስጥ መሠረታዊ በሚባሉ የሕክምና መሳሪያዎች “ተዓምራትን እያደረገ” ከነበረ ወጣት ዶክተር ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

መዲናዋ በተለያየ የታጠቁ ቡድኖች ግዛትነት የተከፋፈለች ሲሆን፣ አንዱ የአንዱን መስመር ማለፍ አይችልም። ይህም ነዋሪዎች በሰፈሮቻቸው ውስጥ ብቻ እንዲወሰኑ አስገድዷቸዋል።

አንድ ግለሰብ ልትወልድ የደረሰችውን ነፍሰጡር ባለቤቱን በጎርፍ በተጥለቀለቁ ጎዳናዎች ላይ ለማሻገር በባሬላ ውስጥ አስገብቶ እንደሚገፋት እና ከዚያም በሞተር ሳይክል፣ በመጨረሻም በመኪና እንደሚጓዙ ለዳይሬክተሩ ነግሯቸዋል።

የመንግሥት ቁጥጥር በሌለበት እና የታጠቁ ቡድኖች በነጻነት ወደሚዘዋወሩባቸው አካባቢዎች ለመድረስም ቀይ መስቀል ከወሮበላ ቡድኖቹ ጋር “ቀጣይነት ያለው ውይይት” እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

“ውይይቱን ስልታዊ በሆነ መንገድ እናደርገዋለን። ከአንደኛው ዞን ወደሌላኛው ዞን በምንሸጋገርበት ወቅት። የተደራጁ ቡድኖች ቁጥር እጅግ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ከሁሉም ጋር ውይይት ማድረግም አንችልም” ሲሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ ተቋሙ የሄይቲን ሕዝብ ለመርዳት መሬት ላይ ባለው ማኅበረሰብ ተቀባይነት የተመሠረተም ነው ብለዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ተቋማቸው ከተደራጁ ቡድኖች ጋር ሌት ተቀን ውይይት ማድረግ እንዳለበትም አስረድተዋል።

“ለሰባት ወይም ለ10 ቀናት ውይይታችንን ካቆምን፣ ካቋረጥንበት የምንቀጥልበት ሁኔታ የለም። ምክንያቱም በቡድኖቹ ውስጥ ያለው ዕዝ ሰንሰለት ልቅ ከመሆኑ ጋር እና የሥልጣን ሽኩቻዎች በመኖራቸው አብዛኛውን ጊዜ ለውጦች ይኖራሉ” ሲሉም አስረድተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በሄይቲ ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት በማሻቀቡ ተቋማቸው በመጪው አውሮፓውያን ዓመት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንደሚጨምርም አስረድተዋል።

ባለው ሁከት እና አመጽ እየተጎዱ ያሉ ማኅበረሰቦችን የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲያገኙም ለማስቻል ቀይ መስቀል የአምቡላንስ አገልግሎቱን እንደሚያጠናክር እና ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውንም አገልግሎት ለማጠናከርም ዕቅድ አለው።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ሄይቲ እየሄደችበት ያለውን የቁልቁለት ጉዞ ጣልቃ በመግባት እንዲቀለብስም” ጥሪ አቅርበዋል።

“በሰብዓዊ እርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ያለ ሲሆን ለአገሪቱ የሚቀርበውን እርዳታ የመጨመር ሥነ ምግባራዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነት አለብን” ብለዋል።