ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወሮበሎች ያስጨነቋት ሄይቲ የውጭ አገራትን ወታደራዊ ድጋፍ ጠየቀች
ሄይቲ እያሽመደመዳት ያለው የወሮበሎች ጥቃት ለመመከት የውጭ ኃይሎች ወታደራዊ እርዳታ እንዲያደርጉላት ተማጸናለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርያል ሄንሪ አገራቸውን “ከተጋረጠባት ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ” ለመታደግ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እንዲጠይቁ የሄይቲ መንግሥት ፍቃድ ሰጥቷቸዋል።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ በሄይቲ ያለውን የደኅነት ችግር በመጠቀስ ዜጎቿ ከአገሪቱ ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች።
በሄይቲ እጅግ የተደረጁ የወሮበላ ቡድኖች ከሳምንታት በፊት የአገሪቱን ዋነኛ የነዳጅ ጣቢያ የዘጉ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ እንደ ውሃና ምግብ ያሉ የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎልን ፈጥሯል።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የውጭ ወታደራዊ እርዳታን ቢጠይቅም ጥያቄው ለማን እንደቀረበ እና እርዳታው በምን መልኩ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሄይቲ መንግሥት የደረሰው ይፋዊ ጥያቄ አለመኖሩን ገልጿል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በሄይቲ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉ ሲሆን፣ ሁኔታው በሄይቲ ሕዝብ ላይ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሄይቲ በሚያከናውነው የሰብአዊ እርዳታ ሥራ ላይ ተጽእኖ ማሳረፉን ጠቁመዋል።
አሜሪካም በሄይቲ የነዳጅ ስርጭትን ወደነበረበት ለመመለስ የቀረበላትን ጥያቄ እያጤነች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ገልጿል።
ሆኖም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ እርዳታውን የሚሰጡ የአሜሪካ ወታደሮች መነሻቸው ከየት እንደሆነ አልጠቀሰም።
በሄይቲ ቫርዩክስ የተባለው የነዳጅ ጣቢያ ከሳምንታት በፊት ነበር በተደረጁ የወርበላ ቡድኖች ጥምረት በቁጥጥር ስር ውሎ የተዘጋው።
ይህም የአገሪቱን እንቅስቃሴ የገታው ሲሆን የተወሰኑ ሆስፒታሎች ሥራ አቁመዋል። በሌላ በኩል ክስተቱን ተከትሎ የንግድ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ቆሟል።
የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ሰበብ የሆነውን የነዳጅ ድጎማ መቋራጥ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ አለመረጋጋት የሰፈነ ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ ተቃውሞ እና ዘረፋ እንዲበራከት አድርጓል።
በሄይቲ የመንግሥታቱ ድርጅት መልዕከተኛ እንደገለጹት ከሆነ የእርዳታ ምግብ መጋዘኖች ኢላማ ተደርገው በደረሰ ተደጋጋሚ ጥቃት 5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ተዘርፏል።
ይህም የሄይቲ መንግሥት ያቀረበው የውጭ ኃይሎች ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ጥያቄ በአገሪቱ ተሰማርቶ የነበረው እና ከአምስት ዓመታት በፊት ለቆ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ዳግም እንዲመለስ የቀረበ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች በሄይቲ የነበራቸው ቆይታ በበጎም በመጥፎ የሚነሳ ነው። በአገሪቱ ተቀስቅሶ 10 ሺህ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው የኮሌራ በሽታ መቀስቀስ ሰላም አስከባሪዎቹ በከፊል ኃላፊነት ወስደዋል።
የሄይቲ መንግሥት ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዕሁድ በኮሌራ ምክንያት ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ወሮበሎች ከጋረጡት ስጋት በተጨማሪም በሽታው የጤና ቀውስ እንዳይቀሰቅስ ተሰግቷል።
ወሮበላዎቹ የፈጠሩት የአቅርቦት መስተጓጎል ተጽእኖ ካሳረፈባቸው ውስጥ አንዱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ስርጭት ነው። ይህም በተበለከለ ውሃ ለሚዛመተው የኮሌራ በሽታ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ሄይቲ በዓለም ላይ ድሃ ከሚባሉ አገራት ውስጥ የምትመደብ ስትሆን በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች።
ከእነዚህም ውስጥም ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንቷ ከተገደሉ ከወር በኋላ 2200 ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው የመሬት መንቀጥቀጥ ተጣቃሽ ነው።
በሄይቲ ግድያ የሚደጋገም ወንጀል ሲሆን በ10 ቀናት ውስጥ ብቻ የወሮበላ ቡድን አባላት በዋና ከተማዋ ፖርት አዩ ፕሪንስ 10 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።